ቅድመ ዳሰሳ | የ23ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች

የ23ኛ ሳምንት የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ በሚከተለው መልኩ ተሰናድቷል።

ሲዳማ ቡና ከ መከላከያ

በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ከ12 ጨዋታዎች ያለ መሸነፍ ግስጋሴ በኋላ ሽንፈት ካስተናገደ ወዲህ ከተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያስመዘገበው ሲዳማ ቡና ከበላዩ ከሚገኙት አራት ክለቦች ጋር ያለውን ልዩነት አጥቦ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የሚያሳድገውን ሦስት ነጥብ ለማግኘት እንደሚጥር ይጠበቃል። ያለፉትን አራት ጨዋታዎች ያልተረታው እና ወቅታዊ ብቃቱ ምርጥ የሆነው መከላከያ በበኩሉ በውድድር ዓመቱ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ድል ለማድረግ እና ከአስጊው ቀጠና በአስተማማኝ ሁኔታ ርቆ በደረጃ ሰንጠረዡ የፊተኛው ገፅ ለመገኘት እታትራል።

ወደ ዋንጫ ፉክክሩ የተጠጋበትን ሂደት በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ባስመዘገበው ውጤት ወደ ኋላ የጎተተው ሲዳማ ቡና ነገም ቀላል ጨዋታ አይጠብቀውም። በእርግጥ ቡድኑ መከላከያን ሲገጥም በፋሲል ከነማው ጨዋታ እንዳየንበት ሙሉ ለሙሉ የመልሶ ማጥቃት ባህሪን ተላብሶ ወደ ሜዳ ላይገባ ይችላል። በዚህም የተከላካይ መስመሩን ቢያንስ በራሱ ግብ ክልል እና በመሀል ሜዳው አማካይ ላይ አቁሞ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን በመውሰድ በቅብብሎች እንደሚወጣ ይገመታል። ይህንን ለማድረግ የሚረዱ ፈጣሪ አማካዮች ያሉት መሆኑ በመሀል ሜዳው ፉክክር እንደሚረዳው ቢታመንም ከኳስ ውጪ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድረው ተጋጣሚውን ባልተዛነፉ ቅብብሎች ማለፍ እና ከሰሞኑ ተዳክሞ የታየውን ዕድሎችን የመጨረስ ብቃቱን አሻሽሎ መቅረብ ለሲዳማ ቡና እጅግ ወሳኝ ይሆናል።

መከላከያ በተከታታይ ጨዋታዎች ራሱን እንደቡድን ሊገልፅ የሚችልበትን ባህሪ ተላብሶ ታይቷል። ከኳስ ውጪ ታታሪነትን በመጨመር ተጋጣሚውን ምቾት መንሳት ፤ ከኳስ ጋር ሲሆን ደግሞ ጥራታቸውን የጠበቁ ፈጣን ቅብብሎችን በማድረግ ወደ ግብ ደርሶ ማስቆጠር የሰሞኑ የጦሩ ልዩ ብቃት ሆነው ታይተዋል። በግለሰብ ደረጃም እንደቢኒያም በላይ እና አዲሱ አቱላ ቡድኑን ውጤታማ ባደረገው በዚህ አቀራረብ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ከፍ ማለቱ ለነገው ጨዋታም የሚተርፍ ነው። ጦሩ ሲዳማን ሲገጥም እነዚህን ጠንካራ ጎኖች ማስቀጠል ሲኖርበት በተለይም ከሲዳማ ቡና የኋላ መስመር ጥምረት አንፃር ግብ የማግኛ አማራጮቹን ማስፋት እና የቡድኑ ዋነኛ የግብ ምንጭ የሆነው ቢኒያም በላይን የአንድ ለአንድ ግንኙነቶች መቀነስ አስፈላጊው ይሆናል።

በጨዋታው መከላከያ ሙሴ ገብረኪዳን፣ ግሩም ሀጎስ እና ኢብራሂም ሁሴንን በጉዳት ሲያጣ ባሳለፍነው ሳምንት ዕረፍት ተሰጥቶት የነበረው ክሌመንት ቦዬ ግን ለጨዋታው ዝግጁ እንደሆነ ተገልጿል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ሲዳማ እና መከላከያ በሊጉ 21 ጊዜያት ተገናኝተው ሲዳማ 7 መከላከያ ደግሞ 6 ጊዜ አሸንፈዋል። በቀሪዎቹ 7 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ወጥተዋል። በ21ዱ ግንኙነት በቅደም ተከተል 19 እና 18 ጎሎችን አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሲዳማ ቡና (4-2-3-1)

ተክለማርያም ሻንቆ

አማኑኤል እንዳለ – ጊት ጋትኩት – ያኩቡ መሐመድ – ሰለሞንሀብቴ

ዳዊት ተፈራ – ሙሉዓለም መስፍን

ሀብታሙ ገዛኸኝ – ፍሬው ሰለሞን – ይገዙ ቦጋለ

ሳላዲን ሰዒድ

መከላከያ (4-2-3-1)

ክሌመንት ቦዬ

ገናናው ረጋሳ – አሌክስ ተሰማ – ልደቱ ጌታቸው – ዳዊት ማሞ

ኢማኑኤል ላርዬ – ምንተስኖት አዳነ

ተሾመ በላቸው – አዲሱ አቱላ – ቢኒያም በላይ

እስራኤል እሸቱ

ሀዋሳ ከተማ ከ አዲስ አበባ ከተማ

ቀስ በቀስ ከዋንጫ ፉክክሩ እየራቀ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ዳግም ከድል ጋር ታርቆ ወላይታ ድቻ የተረከበውን የሦስተኝነት ቦታ ለመቆናጠጥ እና በደረጃ ሰንጠረዡ የላይኛው ፉክክር ለመዝለቅ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ዕሙን ሲሆን በወራጅ ቀጠናው የሚገኘው እና ያለፉትን አራት ጨዋታዎች ተመሳሳይ የአቻ ውጤት ያስመዘገበው አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ በወልቂጤው እና ሀዲያው ጨዋታ በእጁ የገባውን ሦስት ነጥብ አሳልፎ በሰጠበትን ሂደት እየተቆጨ ከባዱን ያለ መውረድ ፈተና ለመጋፈጥ ጨዋታውን እንደሚቀርብ መናገር ይቻላል።

እምብዛም በማይቀያየር ወጥ ቀዳሚ አሰላለፍ ተረጋግተው በውድድር ዓመቱ ከዘለቁ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ሀዋሳ ከተማ የቁልፍ ተጫዋቾቹ ጉዳት እና ቅጣት መደራረብ ያሉትን ጠንካራ ጎኖች አሳጥቶት ታይቷል። ዋና ቀማሪው ወንድምአገኝን ፣ የመስመር ጥቃቱ መነሻ የሆነው መድኃኔን እንዲሁም ከፊት አስፈሪነትን የሚያላብሱትን መስፍን እና ብሩክን ማጣት በሊጉ ግርጌ የሚገኘው ሰበታን እንኳን በአግባቡ መቋቋም እንዲከብደው አድርጎት ነበር። በነገው ፍልሚያ ሁሉንም ባይሆን የተወሰኑትን ተጫዋቾች መልሶ ማግኘቱ ግን በሥነ ልቦናም ሆነ በታክቲካዊ አቀራረብ ረገድ የተሻሻለ ሀዋሳ ከተማን እንድንጠብቅ ያደርገናል። በመሆኑም ኃይቆቹ ከሚቋረጡ ኳሶች በመስመር ተኮር ጥቃት የፊት አጥቂዎቻቸውን የማግኘት ዕቅድ ይዘው እንሰሚገቡ ሲጠበቅ በቅርብ ጨዋታዎች አለመረጋጋት የሚታይበት የኋላ መስመር ግን በሪችሜንድ ኦዶንጎ ከሚመራውን የአዲስ አበባ የፊት መስመር ከበድ ያለ ፈተና የሚያገኘው ይመስላል።

በውድድር ዓመቱ በሰባት ጨዋታዎች ቀድሞ ግብ አስቆጥሮ ውጤት ማስጠበቅ ባለመቻሉ 16 ነጥቦችን ያጣው አዲስ አበባ ከተማ ጥሩ እየተጫወተ ነጥብ ግን እየሰጠ እንደዘበት ጊዜ ሊቀድመው እየተቃረበ ነው። ከበላዩ ያለው ድሬዳዋ ከተማ ማሸነፍ ደግሞ የዚህን ጨዋታ ውጤት አጥብቆ እንዲፈልግ ያደርገዋል። አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው በዚህ ውጤት የመፈለግ ጫና ውስጥ የሚገኘው ቡድናቸውን በጥሩ አቋማቸው ወቅት በመጨረሻ ደቂቃ ውጤት ሲቀይሩ ከታዩት ሀዋሳዎች ጋር ሲገናኝ ገራገርነቱ በድጋሚ እንዳይነፀባረቅ ማድረግ ዋነኛ የቤት ሥራቸው ነው። በዚህም በየደቂቃው የቡድኑን ትኩረት ከፍ ማድረግ እና በየሳምንቱ ስህተት የማያጣው ጭራሽ በጉዳት እና ቅጣት የሳሳው የኋላ ክፍል ሀዋሳን የሚቋቋምበትን መላ ማግኘት ከአዲሶቹ አሰልጣኞች ይጠበቃል። በመጨረሻው ጨዋታ የተሻለ ጥንካሬው በነበረው የወገብ በላይ መዋቅሩ በጥሩ ሁኔታ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ደርሶ ሀሳብ ሲያጥረው መታየቱም የአዲስ አበባ ነገ ተሻሽሎ መቅረብ ያለበት ሌላው ችግሩ ነው።

ሀዋሳ ከተማ መሐመድ ሙንታሪ፣ መስፍን ታፈሰ ፣ ፀጋሰው ድማሙ እና ላውረንስ ላርቴን በጉዳት መድሐኔ ብርሃኔን ደግሞ በቅጣት የሚያጣ ሲሆን ብሩክ በየነ እና አዲስዓለም ተስፋዬ ከቅጣት እንደሚመለሱ እንዲሁም ወንድማገኝ ኃይሉም ከጉዳቱ በማገገሙ ለጨዋታው ዝግጁ እንደሆነ ተጠቁሟል። አዲስ አበባ በበኩሉ ቴዎድሮስ ሀሙን ነገ እንደማያገኝ ሲረጋገጥ ሌላኛው ተከላካይ ዘሪሁን አንሼቦ ደግሞ በዛሬው የልምምድ መርሐ-ግብር መጠነኛ ጉዳት በማስተናገዱ መሰለፉ እርግጥ አይደለም ተብሏል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሀዋሳ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ 3 ጊዜ ተገናኝተው አንድ አንድ ተሸናንፈው አንድ ጊዜ አቻ ወጥተዋል። በሦስቱ ጨዋታዎች አዲስ አበባ ሦስት ሀዋሳ ደግሞ ሁለት ግቦችን በስማቸው አስመዝግበዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዋሳ ከተማ (3-4-3)

ዳግም ተፈራ

ካሎንጂ ሞንዲያ -አብዱልባሲጥ ከማል – አዲስዓለም ተስፋዬ

ዳንኤል ደርቤ – ወንድምአገኝ ኃይሉ – በቃሉ ገነነ – መድኃኔ ብርሀኔ

ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ – ተባረክ ሄፋሞ

አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)

ዳንኤል ተሾመ

አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ሳሙኤል አስፈሪ- አዩብ በቀታ – ሮቤል ግርማ

ሙሉቀን አዲሱ – ቻርለስ ሩባኑ – ኤሊያስ አህመድ

እንዳለ ከበደ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ፍፁም ጥላሁን

ፋሲል ከነማ ከ ባህር ዳር ከተማ

የዕለቱ ተጠባቂ ጨዋታ የሆነው የዐፄዎቹ እና የጣና ሞገዶቹ ጨዋታ በደማቅ የደጋፊዎች ድባብ ታጅቦ እንደሚከወን ጥርጥር የለውም። የወቅቱ የሊጉ ዋንጫ ባለቤት ፋሲል ከነማ ያለፉትን አምስት ጨዋታዎች ሳይሸነፍ የሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለውን ልዩነት ለማጥበብ እየጣረ ይገኛል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ዛሬ ነጥብ ስለጣለ የአስር ነጥቡን ስፋት ወደ ስምንት ለማጥበብ የነገው ተጋጣሚን ማሸነፍ የግድ ይለዋል። ካለፉት አስር ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ያሸነፈው (በፎርፌ መሆኑ ልብ ይሏል) ባህር ዳር ከተማ በበኩሉ በመቀመጫ ከተማው ከድል ጋር ለመገናኘት የነገው ሦስት ነጥብ እጅግ ያስፈልገዋል። ሳይጠበቅ ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ደረጃ ብቻ ከፍ ብሎ የተቀመጠው ቡድኑ እስከ ሰባተኛ ደረጃ የሚያስመነድገውን ነጥብ ለማግኘት ታትሮ መጫወቱ አይቀሬ ነው።

የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ ደረጃ ላይ የሚገኘው ፋሲል ከነማ ባለፉት ጨዋታዎች ያሳካቸው ተከታታይ ድሎች በፈተናዎች ውስጥ የተገኙም ነበሩ። ተጋጣሚዎቹ ከነበራቸው የመከላከል ጥንካሬ አንፃር ቡድኑ ግቦችን ለማግኘት የሚጠቀማቸው መንገዶች በጨዋታዎቹ እንዲመዘኑ ዕድል የሰጠው ነበር ማለት ይቻላል። በዋናነት የኳስ ቁጥጥር ላይ ተመስርቶ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር የሚንቀሳቀስው ፋሲል አልፎ አልፎ አጨዋወቱ ከሚፈልገው ትዕግስት የመውጣት እና የመጣደፍ ሁኔታ ቢታይበትም በየጨዋታዎቹ ግብ ሳያስቆጥር ለመውጣት አለመገደዱ ለነገው ጨዋታ ስንቅ የሚሆነው ነው። በእርግጥ ከነገ ተጋጣሚው አንፃር የመልሶ ማጥቃት ባህር ሊነፀባረቅበት እና ፈጣን የማጥቃት ሽግግሮችን ሊያስመለክተን የሚችልበት ዕድልም ይኖራል። በሌላ ጎኑ በሲዳማ ቡናው ጨዋታ ላይ እንደተመለከትነው ቡድኑ ከተከላካይ ጀርባ የሚተወው ክፍተት ለተጋጣሚው ያለቀላቸውን ዕድሎች መፍቀዱ ለጣና ሞገዶቹ ሊያጋልጠው የሚችለው ድክመቱ ነው ማለት ይቻላል።

ትላልቅ ጨዋታዎች ደካማ የውድድር ጉዞን የሚቀይሩበት አጋጣሚ ሲፈጠር መታየቱ ለባህር ዳር ከተማ የነገውን ጨዋታ ለቀሪው ጊዜ መነሳሻ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። እንደቡድን በርካታ ድክመቶች ያሉበት ባህር ዳር ከነገው ጨዋታ ተጠባቂ ግለት አንፃር የሳሳው የጨዋታ ተነሳሽነቱ በተሻለ ከፍታ እንደሚመለስ ይጠበቃል። በሚያስፈልገው ልክ የመስመር ተከላካዮቹን በመጠቀም የሜዳውን ስፋት ያገናዘበ የኳስ ፍሰትን እስከመጨረሻው ተግብሮ ዕድሎችን መፍጠርን የሚጠይቀው የቡድኑ አጨዋወት በአግባቡ እየተተገበረ ነው ለማለት አያስደፍርም። አሁንም ቢሆን በፍፁም ዓለሙ ላይ ያመዘነው የቡድኑ የግብ መንገድ መፍጠሪያ ስታራቴጂ ነገ አዳዲስ ነገሮችን አካቶ ተጠባቂነቱን ቀንሶ ወደ ሜዳ እንደዲገባ ያስፈልገዋል። ከኳስ ቁጥጥር ባለፈም የአጥቂዎቹን ፍጥነት ከግምት ውስጥ ያስገባ ቀጥተኝነትን መቀላቀል ፋሲልን ለመፈተን ሊረዳው ቢችልም በቡድኖቹ መካከል በወቅታዊ አቋም ደረጃ ያለው ሰፊ ልዩነት ጨዋታው ለጣና ሞገዶቹ በርከት ያሉ የቤት ስራዎችን እንደሚሰጥ ዕሙን ነው።

ፋሲል ከነማ ከነማ ሙጂብ ቃሲም ወደ ልምምድ የተመለሰለት ሲሆን ባህር ዳር ከተማ በበኩሉ በቅጣት ላይ ከሚገኘው ኦሴ ማውሊ ውጪ የሚያጣው ተጫዋች የለም።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ፋሲል እና ባህርዳር 5 ጊዜ ተገናኝተው ፋሲል አንድ አሸንፎ በቀሪዎቹ አራት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ጎሎችን በማስቆጠርም ፋሲል በስድስት ጎሎች ቀዳሚ ሲሆን ባህር ዳር ሁለት አስቆጥሯል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ፋሲል ከነማ (4-1-4-1)

ሚኬል ሳማኪ

ዓለምብርሃን ይግዛው – አስቻለው ታመነ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

ሀብታሙ ተከስተ

ሽመክት ጉግሳ – በዛብህ መለዮ – ሱራፌል ዳኛቸው – በረከት ደስታ

ኦኪኪ አፎላቢ

ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

ፋሲል ገብረሚካኤል

ሣለአምላክ ተገኘ – ፈቱዲን ጀማል – ሰለሞን ወዴሳ – አህመድ ረሺድ

ፍፁም ዓለሙ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – አብዱልከሪም ኒኪማ

ተመስገን ደረሰ – ዓሊ ሱሌይማን – ግርማ ዲሳሳ

ያጋሩ