8 ግቦች በዘነቡበት የማለዳው ፀሀያማ ጨዋታ በግብ ጠባቂው ጭምር ግብ ያስቆጠረው መከላከያ ሲዳማ ቡናን 5-3 አሸንፎ ደረጃውን አሻሽሏል።
ሲዳማ ቡና ከፋሲል ከነማው ሽንፈት መልስ በዛሬው አሰላለፉ ምንተስኖት ከበደን አምስት ቢጫ ካርድ ባለበት ጊት ጋትኩት ምትክ እንዲሁም ክሪዚስቶም ንታምቢን በፍሬው ሰለሞን ቦታ ተጠቅሟል። ክሌመንት ቦዬን ጉዳት በገጠመው ሙሴ ገብረኪዳን ቦታ ወደ አሰላለፍ የመለሱት መከላከያዎች ደግሞ ሀዲያ ሆሳዕናን ከረቱበት ጨዋታ መልስ በተመሳሳይ በጉዳት ምክንያት ኢብራሂም ሁሴንን በአሚን ነስሩ ተክተዋል።
ዛሬም እንደትናንቱ በጨዋታው ፈጣን ጎል ስንመለከት በተከታታይ የሲዳማን መርብ ያገኙት መከላከያዎች በጊዜ 2-0 መምራት ችለዋል። 2ኛው ደቂቃ ከጥልቅ ከቀኝ መስመር ከግሩም ሀጎስ በረጅሙ የተላከውን ኳስ ተስፋዬ በቀለ በግንባር ለማራቅ ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ሳጥን ውስጥ ያገኘው ቢኒያም በላይ በደረቱ ተቆጣጥሮ አጋጣሚውን ወደ ጎልነት ቀይሮታል። ከሁለት ደቂቃ በኋላ ደግሞ ዳዊት ማሞ በግራ መስመር ጥፋት የሰራ በሚመስል እንቅስቃሴ ከደግፌ ዓለሙ ያስጣለውን ኳስ ከቢኒያም በላይ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ሲያሻግርለት ተሾመ በላቸው በተመሳሳይ ሳጥን ውስጥ በደረቱ አብርዶ ሁለተኛ ግብ አድርጎታል።
ሲዳማዎች ኳስ ተቆጣጥረው ወደ ጨዋታው ምት ለመግባት የሞከሩባቸው ቀጣይ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ እየታየባቸው ሲቀጥሉ የክሪዚስቶም ንታንቢ እና የምንተስኖት አዳነ የሳጥን ውጪ ሙከራዎች ወደ ሁለቱ ግቦች ተሞክረዋል። ቀስ በቀስ እያደገ የመጣው የሲዳማ የኳስ ቁጥጥር ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል እየተጠጋ ሄዶ ተፈላጊውን ውጤት አምጥቷል። 18ኛው ደቂቃ ላይ የቡድኑ ኳስ ቅብብል በግራ በኩል ሳጥን ውስጥ ደርሶ ይገዙ ቦጋለ ያዘጋጀውን ከመሀል ሮጦ የደረሰው ዳዊት ተፈራ በቀጥታ በመምታት ሲዳማ ቡናን ወደ ጨዋታው መልሷል።
በዚህ ግብ የተነሳሱት ሲዳማዎች ጫናቸው ይበልጥ ተጠናክሮ ሲቀጥል ቅርፃቸው የተበተነው መከላከያዎች በመስመሮች መካከል ሰፋፊ ክፈተቶችን በመተው የሲዳማን አማካዮችን መቆጣጠር ተስኗቸው ታይተዋል። በተለይ ሲዳማዎች 21ኛው ደቂቃ ላይ አሚን ነስሩ እና ግሩም ሀጎስ ሳጥን ውስጥ ከይገዙ ያስጣሉትን ኳስ ሳያርቁት ዳዊት ተፈራ ሌላ ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር።
25ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር በድንገት የተገኘው ምንተስኖት ተጫዋች በማለፍ ጭምር ወደ ሳጥኑ መግቢያ ላይ ጥሩ ዕድል ቢፈጥርም አዲሱ አቱላ ወደ ውጪ የሰደደበት አጋጣሚ ጦሩ ከቆይታ በኋላ በመልሶ ማጥቃት ወደ ግብ የቀረበበት ቅፅበት ነበር። መከላከያ ከእዚህ ሙከራ በኋላ ያገኘውን የውሃ ዕረፍት በአግባቡ መጠቀም ችሏል።
ከውሀ ዕረፍቱ መልስ ሲዳማዎች በኳስ ቁጥጥሩ ቢገፉበትም የተረጋጋው እና ወደ ጥሩ አደረጃጀቱ የተመለሰው መከላከያ አደጋ እንዳይፈጥሩ አግዳቸዋል። በዚህ መነሻነት መልሶ የፈጣን ጥቃቱን ስለት ያገኘው መከላከያ ከዕረፍት በፊት ሌላ ጎል አክሏል። በዚህም ሲዳማዎች በአጋማሻቸው መግቢያ ላይ ከተቀሙት ኳስ በተነሳው የጦሩ ጥቃት እስራኤል እሸቱ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ሳጥን ውስጥ በማድረስ ለአዲሱ አቱላ አሳልፎለት እሱ ያዘጋጀለትን ተሾመ በላቸው እንደደረሰ በቀጥታ መትቶ 41ኛው ደቂቃ ላይ ድንቅ ግብ አስቆጥሯል።
ከዕረፍት መልስ ፍሬው ሰለሞንን ያስገቡት ሲዳማዎች ከፍ ባለ ማጥቃት ለመጀመር ጥረት ቢያደርጉም ከጦሩም ተመሳሳይ ምላሽ ተሰጥቷቸዋል። በዚህ ሂደት ወደ ሁለቱ ሳጥኖች ጥሩ የማጥቃት ምልልስ የታየበት እንቅስቃሴ 54ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ ግብ አስመልክቶናል። ቢኒያም በላይ ከግራ እያጠበበ የመጣበትን እንቅስቃሴ እስራኤል እሸቱ ተቀብሎ ሲያሳልፍለት አዲሱ አቱላ ከሳጥን ውጪ መትቶ በማስቆጠር ልዩነቱን አስፍቷል። አዲሱ ደስታውን ባለመግለፅ ለቀድሞው ክለቡ ያለውን ክብር ገልጿል። ከዚህ በኋላም ግሩም ሀጎስ ከቅጣት ምት ቢኒያም በላይ ከሳጥን ውስጥ ተጨማሪ የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል።
የሲዳማን የኳስ ቁጥጥር እንዲሁም ልደቱ ጌታቸውን ቀይሮ ያስገባው የመከላከያን ጥንቃቄ እያስመለከተን የቀጠለው ጨዋታ የተለየ አጋጣሚ ተከስቶበታል። በዚህም 68ኛው ደቂቃ ላይ የጦሩ ግብ ጠባቂ ክሌመንት ቦዬ በረጅሙ የለጋው ኳስ በሌላኛው ግብ ደጃፍ ደርሶ በእስራኤል እሸቱ ጫና ውስጥ የገባው ተክለማሪያም ሻንቆ ማቆጣጠር ሳይችል ኳስ እና መረብ ተገናኝተዋል። አጋጣሚው ቦዬን ሚያዚያ 24 2009 ድሬዳዋ ላይ ወልዲያ ድሬዳዋ ከተማን 2-0 ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ ካሜሩናዊው ቤሊንጋ ኢኖህ ከረጅም ርቀት ግብ ካስቆጠረ በኋላ የታየ ባለታሪክ የግብ ዘብ አድርጎታል።
በኳስ ቁጥጥራቸው የቀጠሉት ሲዳማ ቡናዎች ከአምስት ደቂቃ በኋላ ቅብብሎቻቸው ወደ ሳጥን ቀርቦ ጎል አስገኝቶላቸዋል። ሀብታሙ ገዛኸኝ ከፍሬው ሰለሞን የደረሰውን ኳስ የተቀበለው ይገዙ ቦጋለ ደግሞ ግብ አስቆጣሪው ነበር።
በቀሪ ደቂቃዎች ሲዳማዎች ኳሱን ይዘው ጫና ለመፍጠር ቢጥሩም ከማፈግፈግ ይልቅ ኳስ ነጥቀው ይወጡ የነበሩት መከላከያዎች ጨዋታውን መቆጣጠር ችለው ቆይተው በጭማሪ ደቂቃ ሌላ ግብ አስተናግደዋል። ተቀይሮ የገባው አቤኔዘር አስፋው ከግራ ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ሙከራ ኤሌክስ ተሰማ ሲደረብ አግኝቶ ይገዙ ጎል አድርጎታል። በቀጣዩ ደቂቃ አጥቂው ሌላም ግብ ሊያስቆጥር ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካለት ሲዳማም ጊዜ ቀድሞት ጨዋታው በመከላከያ 5-3 አሸናፊነት ተቋጭቷል።
በውጤቱ ነጥቡን 30 ያደረሰው መከላከያ 7ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ሲዳማ ቡና በ34 ነጥቦች በነበረበት 5ኛ ደረጃ ላይ ቀርቷል።