የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 3-5 መከላከያ

የረፋዱን ጨዋታ በከፍተኛ መሻሻል ላይ የሚገኘው መከላከያ ድል ካደረገ በኋላ አሰልጣኞቹ አስተያየት ሰጥተዋል።

ምክትል አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ – መከላከያ

ውጤቱ የጠበቁት ስለመሆኑ

“አምስት እናገባለን ብዬ ባልጠብቅም ፤ እናሸንፋለን የሚል ስሜት ግን ውስጥ ነበርን። የሚገባንን ነገር አግኝተናል ብዬ ነው የማምነው። ለዚህም ትልቁ ሥራ ደግሞ የልጆቹ ነው። ቡድኑ እዚህ ቦታ መቆየት የለበትም። የእኛ ደረጃ እዚህ አይደለም። በሚል በአንድ ሀሳብ ፣ አስተሳሰብ ቃል በገቡት መሠረት ቡድኑን ወደ ላይ ከፍ እያደረጉት ነው። ስለዚህ ልጆቹ ላይ ያለ መነቃቃት ፣ መነሳሳት የሚባሉትን ነገር ሜዳ ላይ በተግባር ለማድረግ ያላቸው ተነሳሽነት በመሆኑ ልጆቹ ሊመሰገኑ ይገባል።

ስለ ጎል ሙከራዎች

“ ትልቁ ነገር በማጥቃት እና በመከላከል እንቅስቃሴ ላይ በህብረት መስራት ነው። ሁለተኛ ነገር ደግሞ በልምምድ የተሰጠውን ተግባራዊ ማድረግ ነው። በሚገባ ቁርጠኝነት ያንን ሜዳ ላይ ተግብረውታል። ስለዚህ ውጤቱ ይሄ ነው።

ስለተሾመ በላቸው ማዕረግ ዕድገት

“ያውን እንግዲህ ጎል ማግባቱን ከቀጠለ ከፍ እያለ ይሄዳል። ስለዚህ ወጣት ልጅ ነው
ከዚህ በላይ ይጠበቅበታል። እንዳውም እኛ እንደምንፈልገው እየሆነልን አይደለም። ከዚህ የበለጠ ማደግ የሚችል ልጅ ነው። ወደ ፊት ጥሩ ነገር ይሰራል ብለን እንጠብቃለን።”

አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ – ሲዳማ ቡና

ስለጨዋታው

“መጥፎ ጨዋታ ነው። ለእኛ በእንደዚህ ያለ ደረጃ መሸነፍ ትልቅ ሽንፈት ነው። እስከዛሬ በአሰልጣኝነት ዘመኔ እንዲህ ያለ ጎል ተቆጥሮብኝ አያውቅም። ጥንቃቄ የጎደለው ጨዋታ ነበር። ከመጀመርያው ደቂቃ ጀምሮ ስንገባ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን ተነጋግረን ነበር። ግን ተግባራዊ በማድረጉ ላይ በጣም ደካማ ነበርን ፤ ተከላካዮቻችን ዝኑጉዎች ነበሩ። ለማንኛውም ኃላፊነቱን የምወስደው እኔ ነኝ፣ ብዙ ለውጦች አድርጌያለሁ ፤ ለውጦቹ አልጠቀሙንም። ለወደፊቱ ማየት የሚገባን ነገሮች እንዳሉ ነው የሚያሳዩን።

ስለዘገዩት ሦስት ጎሎች

“የዘገየ ነው። መጀመርያ ሦስት ለአንድ የሆንበት ጎል ነበር በጣም ወሳኝ የነበረው። ሁለት ለአንድ እያለን ጎል እንዳይገባብን በጥንቃቄ ተጫውተን ከቆየን ማግባት እና ማሸነፍ እንደምንችል ነበር የነገርኳቸው። ነገር ግን ሦስት ለአንድ የሆንበት ጎል በጣም እኛን አውርዶናል። ከዛ እንደገና ተክለማርያም የተሳሳተው ደግሞ ሌላ ስህተት ተጨመረበት። ከዚህ በተረፈ እንደ አጥቂ ማግባቱ ጥሩ ነው። ሊያገቡም ይገባችዋልም ፤ ማግባትም አለባቸው። ነገር ግን ዝም ብሎ የበለው በለው ዓይነት ነው የሚሆነው። በአጠቃላይ በውጤቱ ደስተኛ አይደለሁም።”

ያጋሩ