ሪፖርት | ሀዋሳ እና አዲስ አበባ ነጥብ ተጋርተዋል

የሀዋሳው ከተማው ግብ ጠባቂ ዳግም ተፈራ በደመቀበት የምሳ ሰዓቱ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ 2-2 ተለያይተዋል።

ሀዋሳ ከተማዎች ከሰበታ ከተማ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ አራት ለውጦችን ሲያደርጉ በዚህም ላውረንስ ላርቴ ፣ አቤኔዘር ኦቴ ፣ ሄኖክ ድልቢ እና አብዱልባሲጥ ከማልን አስወጥተው በምትካቸው አዲስዓለም ተስፋዬ ፣ ዳዊት ታደሰ ፣ ወንድማገኝ ኃይሉ እና ብሩክ በየነን በመጀመሪያ ተሰላፊነት አስጀምረዋል።

በአንፃሩ ከወልቂጤ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው የተመለሱት አዲስ አበባ ከተማዎች ደግሞ ሦስት ለውጥ ያደረጉ ሲሆን አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ፣ ዘሪሁን አንሼቦ እና ሮቤል ግርማ አስወጥተው በምትካቸው ሳሙኤል አስፈሪ ፣ ልመንህ ታደሰ እና ፍራኦል መንግሥቱን በማስገባት የዛሬው ጨዋታ አድርገዋል።

እምብዛም ሳቢ ያልነበረው ጨዋታ ገና ከጅምሩ ነበር የመጀመሪያውን ግብ ያስተናገደው። በ7ኛው ደቂቃ ላይ ፍራኦል መንግሥቱ ከመሀል ሜዳው አካባቢ በረጅሙ ያሻማውን ኳስ የሀዋሳው የመሀል ተከላካይ ካሉንጂ ሙንዲያ ለግብ ጠባቂው አቀብላለሁ ብሎ የገጨው ኳስ ዳግም ተፈራ ግቡን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ከመረብ ተዋህዳ አዲስ አበባን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ይበልጥ ተነቃቅተው ማጥቃታቸውን የቀጠሉት አዲስ አበባ ከተማዎች ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ጥረት አድርገዋል። በዚህም በተለይ ሪችሞንድ አዶንጎ በሁለት አጋጣሚዎች ያገኛቸውን አደገኛ አጋጣሚዎች መጠቀም ሳይችል ቀርቷል። 22ኛው ደቂቃ ላይ በሀዋሳ ከተማዎች በኩል በራሱ ግብ ላይ ግብ ያስቆጠረውን ካሎጂ ሞንዲያ በአቤነዘር ኦቴ ተክተው በማስወጣት አደራደራቸው ላይ ለውጥ በማድረግ በተሻለ መልኩ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት አድርገዋል።
ከአደራደር ለውጥ በኋላ በተወሰነ መልኩ ወደ ጨዋታው ለመግባት ጥረት ማድረግ የጀመሩት ሀዋሳ ከተማዎች በ31ኛው ደቂቃ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቷል።
ወንድማገኝ ኃይሉ ላይ በተሰራ ጥፋት ሀዋሳ ከተማዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ተጠቅሞ ብሩክ በየነ ሀዋሳ ከተማን ወደ ጨዋታው የመለሰች ግብ ከፍፁም ቅጣት ምት ማስቆጠር ችሏል።

በአጋማሹ 38ኛው ደቂቃ ላይ በመስመር በኩል በተለይ የአዲስ አበባን ማጥቃት ሲያሳልጥ የነበረው ፍፁም ጥላሁን ከፀጋአብ ዮሐንስ ጋር የጋራ ኳስን ለማሸነፍ ጥረት ባደረገበት ወቅት ባጋጠመው ጉዳት በመሐመድ አበራ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል።

በመጠኑም ቢሆን በሁለቱም ቡድኖች በኩል በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የተሻሉ ሙከራዎችን የማድረግ ጥረት የተመለከትንበት ነበር። በ42ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አሻሞ ከግቡ ትይዩ ያገኘውን የቅጣት ምት ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ የላካት እና ዳንኤል ተሾመ በግሩም ሁኔታ ያዳነበት እንዲሁም በ43ኛው ደቂቃ ላይ ዳግም ተፈራ በግሩም ሁኔታ ከመሐመድ አበራ ላይ ያዳናት ኳስ አደገኛ ሙከራዎች ነበሩ።

ሁለተኛውን አጋማሽ የመጀመሪያውን በጨረሱበት መንገድ ከፍ ብለው ለመጀመር ጥረት ያደረጉት ሀዋሳ ከተማዎች በ48ኛው ደቂቃ በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ዳንኤል ደርቤ ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ያሻማውን ኳስ ብሩክ በየነ በግሩም ሁኔታ በመግጨት ዳግም መሪ መሆን ችለዋል።

ነገር ግን የሀዋሳ ከተማ መሪነት የዘለቀው ለ7 ያክል ደቂቃዎች ነበር። 55ኛው ደቂቃ ቻርልስ ሪባኑ በግል ጥረቱ የተቀበለውን ኳስ እየነዳ አንስቶ ወደ ሳጥን ውስጥ ከደረሰ በኋላ አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ ሪችሞንድ አዶንጎ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

በጨዋታው ምንም እንኳን በአዲስ አበባ ደረጃ ተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ባይደርሱም በመልሶ ማጥቃት ግን በአጋማሹ አደገኛ አጋጣሚዎችን ፈጥረዋል። በተለይም በ59ኛው ደቂቃ በሀዋሳ ከተማ በኩል ወንድማገኝ ኃይሉ ከተከላካይ ጀርባ ያደረሰውን ኳስ ብሩክ በየነ አፈትልኮ በመውጣት አስቆጥሮ ሲባል ያገኘውን አጋጣሚ በአስገራሚ መልኩ ያመከናት ኳስ እንዲሁም በ68ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አሻሞ ከግራ የሳጥን ጠርዝ ወደ ውስጥ ያቀበለውን ኳስ ወንድማገኝ ከግቡ አናት በላይ የላካት ኳስ ጥሩ አስቆጭ ዕድሎች ነበሩ።

ውጤን በመፈለግ በተደጋጋሚ ለማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት አዲስ አበባ ከተማዎች በጨዋታው በተለይ የሀዋሳ ከተማ ተከላካዮች ይሰሯቸው እንደነበሩ ስህተቶች በርከት ያለ ግቦችን ማስቆጠር በቻሉ ነበር። ነገር ግን የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ዳግም ተፈራ ቡድኑን ከጉድ ታድጓል።

በ72ኛው ደቂቃ ላይ ሪችሞንድ አዶንጎ የተሰጠውን ኳስ ሸፍኖ ሊያስቆጠር ጥረት ቢያደርግም ዳግም ተፈራ ሊያድንበት ችሏል። በተመሳሳይ በ76ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ አበባ ከተማዎች ሪችሞንድ አዶንጎ ላይ አዲስዓለም ተስፋዬ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ሪችሞንድ ቢመታም ድንቅ ብቃቱን በጨዋታው ሲያሳይ የነበረው ዳግም ተፈራ በሁለት አጋጣሚዎች በግሩም ቅልጥፍና ሊያድንበት ችሏል።

ከፍፁም ቅጣቱ ምቱ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ አለመግባባትም የሀዋሳ ከተማው የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ አዳሙ ኑሞሮ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።
በዚህ ያላበቃው ወጣቱ ግብ ጠባቂ በ87ኛው ደቂቃም እንዲሁ ተቀይሮ የገባው ቢኒያም ጌታቸው ከሳጥን ውጭ ያደረገውን ግሩም ሙከራ አድኖበታል።

ጨዋታው በሁለት አቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ በ36 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ሲገኙ አዲስ አበባ ከተማዎች በ23 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ቀጥለዋል።