ሪፖርት | ዐፄዎቹ ተከታታይ ድላቸውን አስቀጥለው በፉክክሩ ገፍተውበታል

የፍቃዱ ዓለሙ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ፋሲል ባህር ዳርን 1-0 አሸንፎ ከመሪው ጋር ያለውን ልዩነት እንዲያጠብ አድርጓል።

ፋሲሎች ሲዳማ ቡናን አንድ ለምንም ከረቱበት ስብስባቸው አስቻለው ታመነ ፣ ሰዒድ ሁሴን እና ሀብታሙ ተከስተን በአምሳሉ ጥላሁን ፣ ከድር ኩሊባሊ እና ይሁን እንደሻው በመተካት ለውጥ ሲያደርጉ የጣና ሞገዶቹ ከጦና ንቦቹ ጋር ያለ ጎል ካጠናቀቁበት ጨዋታ አለለኝ አዘነ ፣ በረከት ጥጋቡ እና አደም አባስን በማሳረፍ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ ፣ ፉዓድ ፈረጃ እና ተመስገን ደረሰን አስጀምረዋል።

ጨዋታው እጅግ ባማረ የደጋፊ ድባብ ታጅቦ ሲጀምር በጣና ሞገደቹ በኩል በመጀመርያው ደቂቃ ከርቀት ዓሊ ሱሌማን ለጎል የቀረበ ሙከራ በማድረግ ጨዋታውን በጥሩ ፉክክር መንፈስ አስጀመረው ቢባልም ተጨማሪ ጠንካራ የጎል ሙከራ ለማየት ረጅም ደቂቃ መጠበቅ ግድ ብሏል። ተረጋግተው ኳሱን ተቆጣጥረው ወደ ባህር ዳር የሜዳ ክፍል የሚሄዱት አፄዎቹ ቅብብላቸው ሳይቀጥል በመቅረቱ አደጋ ሳይፈጥሩ ሲመለሱ በአንፃሩ ባህር ዳሮች የመልሶ ማጥቃት ሽግግራቸው የተሳካ ባለመሆኑ እስከ ውሃ ዕረፍት ድረስ ጠንካራ የጎል ሙከራ መመልከት ሳይቻል ቀርቷል።

26ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲሎች በራሳቸው ሜዳ ለመውጣት ሲሞክሩ ከሽመክት ጉግሳ ያቀባበል ስህተት ምክንያት የተገኘውን ኳስ በፈጣን እንቅስቃሴ ፍፁም ዓለሙ በጥሩ ሁኔታ ያቀበለውን ዓሊ ሱለይማን ተረጋግቶ ኳሱን ካለመጠቀም የተነሳ የተገኘውን ግልፅ የጎል አጋጣሚ ሳይጠቀም ቀርቷል። በተወሰነ መልኩ መነቃቃት የታየበት ጨዋታው በ31ኛው ደቂቃ ዐፄዎቹ በኦኪኪ አፎላቢ የቅጣት ምት ኳስ ለጎል የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። ብዙም ሳይቆይ ሱራፌል ከአህመድ ረሺድ ጀርባ ከርቀት የጣለለትን በረከት ደስታ ተቆጣጥሮ ሳጥን ውስጥ በመግባት በጠንካራ ምቱ ወደ ጎል ቢልከውም አቡበከር ኑሪ ወደ ውጪ ያወጣበት ፋሲሎችን መሪ ማድረግ የምትችል ግልፅ የጎል አጋጣሚ ነበረች።

በውጥረት ተሞልቶበት በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች በሚሰሩ ጥፋቶች ታጅቦ የቀጠለው ጨዋታ 45ኛው ደቂቃ ላይ መንፈሱን የሚቀይር ክስተት አስተናግዷል። በዚህም በደቂቃዎች ልዩነት ፍፁም ዓለሙ በሰራቸው ሁለት ጥፋቶች በሁለተኛ ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወጣ ሆኗል።

በሁለተኛው አጋማሽ አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በቁጥር የተወሰደባቸውን ብልጫ በታክቲክ ለውጥ ለማሸጋሸግ ዓሊ ሱሌማንን በአብዱልከሪም ኒኪማ በመተካት ለውጥ ቢያደርጉም 49ኛው ደቂቃ ያሬድ ባየህ ተመገስን ደረሰ ላይ በሰራው ጥፋት በሁለተኛ ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ በመውጣቱ ቡድኖቹ ዳግም በቁጥር ተመጣጥነዋል። በሌላው የፋሲል ዕጦት ደግሞ ወዲያው በዛብህ መለዮ በጉዳት ምክንያት ጨዋታውን መቀጠል ሳይችል ተቀይሮ ወጥቷል።

ሁለቱ ክስተቶች የፋሲልን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያሳሱት በአጋጣሚው የተነቃቁት ባህር ዳሮች በክፍት ጨዋታ ጎል ለማግኘት እየተቸገሩ የውሃ ዕረፍት ደርሷል። 75ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን መልሶ ማጥቃት በቀኝ መስመር የገቡት የጣና ሞገዶቹ በአብዱልከሪም ኒኪማ የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ተመስገን ደረሰ በጎሉ ቅርበት ተቆጣጥሮ ሲመታ ዓለምብርሀን እንደምንም ተደርቦ ያወጣበት ለቡድኑ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር።

በፋሲሎች በኩል በ80ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት አምሳሉ ጥላሁን የሞከረው እና አቡበከር በቀላሉ የያዘው ሙከራ ይጠቀሳል። ፋሲሎች የማጥቃት ግለቱን ከባህር ዳር በመውሰድ ወደ ጎል ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት ሲቀጥል 87ኛው ደቂቃ ላይ ወሳኝ የሆነ ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። ናትናኤል ከሳጥን ውጪ የመታውን ኳስ መናፍ ዐወል በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምትም ፍቃዱ ዓለሙ ከመረብ በማገናኘት የጨዋታውን ብቸኛ እና የዐፄዎቹን የዋንጫ ፉክክር ያስቀጠለች ጎል አስቆጥሯል። ፋሲሎች መጨረሻ ላይም ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበት ዕድል በናትናኤል አማካኝነት ቢፈጥሩም አቡበከር ኑሪ አድኖባቸው ጨዋታው በ1-0 ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ፋሲሎች ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ ስምንት ሲያጠቡ ባህር ዳር ባለበት 13ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገዷል።

ያጋሩ