የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 1-0 ባህር ዳር ከተማ

ፋሲል ከነማ በፍቃዱ ዓለሙ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ባህር ዳርን ካሸነፈበት ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ – ፋሲል ከነማ

ስለውጤቱ አስፈላጊነት

መጀመሪያ እንደገለፅኩት ለእኛም ፣ ለእነርሱም ወሳኝ ነው ጨዋታው፡፡ ውጥረት የበዛበት ጨዋታ ነበር፡፡ በምንም አድርገን አሸንፈናል፡፡

ጨዋታው ኃይል የተቀላቀለበት ስለመሆኑ

እንደውም በዚህ ጨዋታ ኃይል የተቀላቀለበት ጨዋታ አልነበረም ማለት እችላለሁ በእኔ፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩት ጨዋታዎች በጣም አግሬሲቭ ነበሩ፡፡ እንደውም ዛሬ ጥሩ ኳስ ነው የነበረው፡፡ ስለዚህ በውጥረት እንዲህ አይነት ነገሮች ይመጣሉ፡፡

ስለ ቅያሪ ስኬት

ቅያሬዎቻችን ፣ ባለፈውም ሙሉ ጨዋታ ስለ ተጫዋቱ እነ ሽመክት ፣ ትንሽ ጉልበት ማነስ ነበር፡፡ ጨዋታው እንደነገርኩህ ውጥረትም ስለነበረው፡፡ ኳስ ከአዕምሮ ጋር የተያዘዘ ነው፡፡ ስለዚህ ተጨማሪ ኃይል ያለው ሰው ያስፈልገን ነበር፡፡ ቀይረን የተሻለ ነገር አግኝተናል ብዬ አስባለሁ፡፡

ስለ ዋንጫ ፉክክሩ

አዎ፡፡ ግን እኛ ስለዛ ሳይሆን ዋናው ዓላማችን ከፊት ለፊት የምናገኛቸውን ተጋጣሚዎች እያሸነፍክ መሄድ ነው፡፡

አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ – ባሀህርዳር ከተማ

ስለጨዋታው ዕቅድ

ከመጀመሪያው አርባ አምስት ይልቅ ሁለተኛው አርባ አምስት ላይ በምንፈልገው መልኩ ተጫውተናል ማለት እችላለሁ፡፡ ያገኘናቸውንም ኳሶች መጠቀም አለመቻላችን ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ ከዚህ ውጪ በሁለታችንም በኩል ጥሩ ፉክክር የታየበት ጨዋታ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ፣ እግር ኳስ ብዙ ሞክረህ ዕድልም ከአንተ ጋር ካልሆነ ውጤት አጥተህ ትወጣለህ፡፡ በተረፈ ግን በዘጠናው ደቂቃ በዚህ ከባድ ጨዋታ ፣ ተጫዋቾቼ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ደጋፊዎቻችንን ማስደሰት ባለመቻላችን አሁንም በድጋሚ ይቅርታ ነው የምጠይቀው፡፡ በቀጣዩ ጨዋታ ደግሞ የነበሩትን ድክመቶች አርመን የተሻለ እንሰራለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ስለ ፍፁም ዓለሙ ቀይ ካርድ እና ተፅዕኖው

ትክክል ነው፡፡ ፍፁም በመጀመሪያው አርባ አምሰት እያለ የማጥቃት ባላንሳችን ጥሩ ነበር፡፡ ሁለተኛ ፍፁም በማጥቃቱ ብቻ ሳይሆን እየተመለሰም የኛን የተከላካይ አማካይ በማገዝ ረገድ የተሻለ ሥራ ይሰራ ነበር፡፡ የፍፁም መውጣት ቁልፍ ተጫዋች እንደ መሆኑ መጠን ጎድቶናል፡፡ ያም ሆኖ ግን ተክተው የገቡትም ልጆች የሚችሉት ሁሉ አድርገዋል፡፡

ስለመውረድ ስጋት

ትልቁ ነገር አሁንም ሜዳ ላይ የምናሳየው እንቅስቃሴ  መጥፎ አይደለም፡፡ አሁንም በሥነ-ልቦናው ላይ ሰርተን ተጫዋቾቻችን ወደ አሸናፊነት ሊመለሱ የሚችሉበትን መንገድ መፈለግ ብቻ ነው ያለን አማራጭ። ካለው ጭንቀት ውስጥ ለመውጣት፡፡