ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

ሁለተኛው የዓበይት ጉዳዮች ፅሁፋችን በጨዋታ ሳምንቱ ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾችን የዳሰስንበት ነው።

👉 ግቦቹን ለወሳኝ ጨዋታ የሚያስቀምጠው ፍቃዱ ዓለሙ

በጨዋታ ሳምንቱ እጅግ ተጠባቂ በነበረው ጨዋታ ፋሲል ከነማ ባህር ዳር ከተማን ሲረታ በጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ የነበረው ፍቃዱ ዓለሙ ነበር።

በውድድር ዘመኑ በ17 ጨዋታዎች መሳተፍ የቻለው ፍቃዱ ለ10ኛ ጨዋታ በ67ኛው ደቂቃ ኦኪኪ አፎላቢን በመተካት ከተጠባባቂ ወንበር ትነስቶ በ87ኛው ደቂቃ ቡድኑ ያገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ተጠቅሞ ባስቆጠራት ግብ ፋሲል ከነማ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለውን ልዩነት ወደ 8 ነጥብ ያጠበበትን ወሳኝ ድል አስገኝቷል።

በተመሳሳይ ባለፈው የጨዋታ ሳምንትም እንዲሁ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ፍቃዱ ዓለሙ በተመሳሳይ በ75ኛው ደቂቃ የቡድኑን ወሳኝ የማሸነፊያ ግብ በማስቆጠር ዐፄዎቹ ባለድል ማድረጉ አይዘነጋም። በዘንድሮ የውድድር ዘመን ቀዳሚውን ሐት-ትሪክ መስራት የቻለው እና በድምሩ ሰባት ግቦችን ማስቆጠር የቻለው አጥቂው ሦስቱን ግቦች ከተጠባባቂነት በመነሳት ያስቆጠራቸው ሲሆን በተለይ የመጨረሻ ሁለቱ ግቦቹ ግን ዋጋቸው እጅግ ከፍ ያሉ ናቸው።

ፋሲል በተቸገረባቸው ጨዋታዎች ከተጠባባቂ ወንበር በመነሳት ቡድኑን መታደግ ልማዱ ያደረገው ፍቃዱ ዓለሙ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመንም ዐፄዎቹ የሊጉ አሸናፊ ሲሆኑ የውድድር ዘመኑን ከወሰኑት ጨዋታ አንዱ በነበረው እና በ19ኛ ሳምንት ድሬዳዋ ላይ ሲዳማ ቡናን በገጠሙበት ጨዋታም እንዲሁ ተቀይሮ በመግባት ወሳኟን የማሸነፊያ ግብ በ87ኛው ደቂቃ ላይ ማስቆጠሩ አይዘነጋም።

👉 ግብ ያስቆጠረው ግብ ጠባቂ

በአስገራሚ ክስተቶች የተሞላው የጨዋታ ሳምንት ካስመለከቱን ያልተለመዱ አጋጣሚዎች መካከል ግብ ጠባቂ ግብ ያስቆጠረበት አጋጣሚ አንዱ ነበር።

በመጨረሻው የጨዋታ ዕለት መከላከያ ሲዳማ ቡናን 5-3 ሲረታ በመከላከያ የግብ አግቢዎች ዝርዝር ውስጥ የጋናዊው ግብ ጠባቂ ክሌመንት ቦዬ ስም ይገኝበታል። በ68ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው ግብ ጠባቂ ክሌመንት ቦዬ ከራሱ የግብ ክልል በቀጥታ ወደ ሲዳማ ሳጥን የላከው ኳስ ተክለማርያም ሻንቆ በእስራኤል እሸቱ መጠነኛ ጫና በደረሰበት ወቅት ኳሱን ለመያዝ አለመቻሉን ተከትሎ ግቧ ተቆጥራለች።

ይህም ከዚህ ቀደም በ2009 የውድድር ዘመን ድሬዳዋ ላይ ወልዲያ ድሬዳዋ ከተማን 2-0 ባሸነፈበት ጨዋታ ላይ ካሜሩናዊው ቤሊንጋ ኢኖህ ከረጅም ርቀት በ14ኛው ደቂቃ ግብ ካስቆጠረ በኋላ በሊጉ ግብ ያስቆጠረ ግብ ጠባቂ ያደርገዋል።

👉 ሀዋሳን የታደገው ወጣቱ የግብ ዘብ

ሀዋሳ ከተማ ሁለት ነጥብ ባሳካባቸው የመጨረሻ ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ላይ የወጣቱ ግብ ጠባቂ ዳግም ተፈራ አስዋፅኦ የላቀ ነበር።

በሰበታው ጨዋታ ጥሩ ጥሩ ኳሶችን በማዳን ቡድኑ ፍፁም ደካማ በነበረበት ጨዋታ ያለ ግብ አቻ እንዲለያይ ሲያስችል በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ቡድኑ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ሁለት አቻ በተለያየበት ጨዋታ በመከላከሉ ረገድ ፍፁም ደካማ የነበረውን ቡድን ከጨዋታው ነጥብ እንዲጋራ ማድረግ ችሏል።

በሁለቱም አጋማሾች ጥሩ ጥሩ አጋጣሚዎችን በንቃት ማምከን የቻለው ግብ ጠባቂው በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ አዲስ አበባ ከተማዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ከሪችሞንድ አዶንጎ ላይ ያዳነበት ሲሆን የተፋውን ኳስ ደግሞ ሪችሞንድ ለማስቆጠር ያደረገውን ጥረት በግሩም ቅልጥፍና መልሶ የመለሰበት መንገድ በብዙዎች ዘንድ ያስደነቀው አጋጣሚ ነበር።

የቡድኑ ተቀዳሚ ግብ ጠባቂ የሆነው መሀመድ ሙንታሪ አለመኖርን እንደ ትልቅ አጋጣሚ እየተጠቀመ የሚገኘው ወጣቱ ግብ ጠባቂ በአሰልጣኝ ዘርዓይ የግብ ጠባቂዎች የምርጫ ቅደም ተከትል ላይ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችልን ብቃት እያሳየ ይገኛል።

በውድድር ዘመኑ ለዘጠነኛ ጨዋታ የቡድኑን ግብ መጠበቅ የቻለው ወጣቱ ግብ ጠባቂ ዳግም ተፈራ ከሰሞኑ በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች እያሳየ በሚገኘው አስደናቂ ብቃት በቀጣዩ የብሔራዊ ቡድን ምርጫ ውስጥ መካተት ይገባዋል የሚሉ ሀሳቦች ከወዲሁ እየተንሸራሸሩ ይገኛል።

👉 አብዱራህማን ሙባረክ የደመቀበት ጨዋታ

ድሬዳዋ ከተማ ሀዲያ ሆሳዕናን ሲረታ በጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ በኩል ድንቅ የጨዋታ ዕለት ያሳለፈው አብዱራህማን ሙባረክ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። በጨዋታው ሁለት ግቦች ከማስቆጠር ባለፈ አንድ ኳስም አመቻችቶ መስጠት ችሏል።

በክረምቱ የውድድር ዘመን ወልቂጤ ከተማን ለቆ ወደ ድሬዳዋ ከተማ ያመራው አብዱራህማን ሙባረክ ምናልባት ከጨዋታ ደቂቃ አንፃር ካለፉት ዓመታት በተሻለ ከጉዳት የፀዳ የውድድር ዓመትን በድሬዳዋ ከተማ እያሳለፈ ይገኛል። በውድድር ዘመኑ 19ኛ ጨዋታው ላይ ተሳትፎ ማድረግ የቻለው ተጫዋቹ በ12 ጨዋታዎች በቋሚነት ሲጀምር በተቀሩት 7 ጨዋታዎች ደግሞ ከተጠባባቂነት በመነሳት በድምሩ 1101 ደቂቃዎች ተሰልፎ ተጫውቷል።

በአዲሱ አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ እምብዛም የመሰለፍ ዕድልን እያገኘ ያልነበረው አብዱረህማን ለሦስተኛ ጊዜ የመሰለፍ ዕድልን ባገኘበት ጨዋታ ያሳየው አስደናቂ ብቃት አሰልጣኙ በቀጣይ በሚሰይሟቸው የመጀመሪያ 11 ተመራጭ ዝርዝር ውስጥ እንዲገባ የሚያስገድድ ነበር።

በጨዋታው በሦስት ግቦች ላይ ተሳትፎ ከማድረግ ባለፈ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ጥሩ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ቢያገኝም መጠቀም ሳይችል ቀረ እንጂ በአጠቃላይ በጨዋታው በተለይ በቡድኑ ማጥቃት ውስጥ የነበረው ተሳትፎ ድንቅ የሚባል ነበር። እንደቀደሙት ጊዜያት ተጫዋቹ ከፍ ባለ የራስ መተማመን ኃላፊነት ወስዶ ኳሶችን እየነዳ ተጫዋቾችን እየቀነሰ ለመሄድ የነበረው ድፍረትም አስደናቂ ነበር።

👉 የሚገባውን ግብ ያገኘው ዴሪክ ንሲባምቢ

ከአጋማሹ የዝውውር መስኮት አስቀድሞ ክለብ አልባ የነበረው ዴሪክ ንሲምባቢ ከ13ኛ የጨዋታ ሳምንት አንስቶ በሰበታ ከተማ እየተጫወተ ይገኛል። ዩጋንዳዊው አጥቂ በብዙዎች ዘንድ በሚፈለገው ደረጃ ቡድኑን እያገለገለ አይገኝም በሚል ተደጋጋሚ ወቀሳዎችን እያስተናገደ ይገኛል።

እርግጥ ቡድኑ በወቅቱ ከነበረበት ከፍተኛ የአጥቂ መስመር ተሰላፊ ተጫዋቾች እጥረት መነሻነት ተጫዋቹ ሲፈርም ከአጥቂዎቹ በቂ ግልጋሎት እያገኘ ላልነበረው ሰበታ የተሻለ አበርክቶ ይኖረዋል በሚል ነበር። ነገር ግን የተጫዋቹን አበርክቶ በግብ አንፃር ከመዘነው በ11 ጨዋታዎች ጅማ ላይ ያስቆጠረውን ግብ ጨምሮ ሁለት ግቦችን ብቻ ማስቆጠሩ በዚህ ረገድ የቡድኑን ችግር በበቂ ሁኔታ ምላሽ አልሰጠም ለሚለው ወቀሳ በምክንያትነት ይቀርባል።

የተጫዋቹን አበርክቶ ከግብ ውጪ ባሉ መመዘኛዎች ከተመለከትነው ግን ጥሩ የሚባል ነው። በተለይ ተጫዋቹ በጥልቀት ወደ ኋላ ተስቦ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚሳተፍበት መንገድ እንዲሁም በእንቅስቃሴ እየዋለለ ወደ ቀኝ እና ግራ እየወጣ የሚያደርገው ጥረት ጥሩ የሚባል ነው። ነገር ግን የቡድኑ የጨዋታ መንገድ በትዕግስት እንቅስቃሴን አስቀጥሎ ሳጥን ውስጥ በዝቶ ከመድረስ ይልቅ ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ ተጫዋቾች ወደ ሳጥን ኳሶች ሲሻሙ ሳጥን ውስጥ አይኖርም አልያም በአየር ላይ ኳሶች ላይ ያለው ብቃት ቡድኑ እንደሚፈልገው ዓይነት ገዘፍ ያለ የሳጥን አጥቂ ባለመሆኑ እምብዛም ፍሬያማ ለመሆን ተቸግሯል።

በመሆኑም በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ ያለመሆኑን ሂደት በተናጠል በተጫዋቹ ላይ አንጠልጥሎ ከመመልከት ከጥቅል የቡድኑ የጨዋታ አቀራረብ ጋር መመልከት ተገቢ ይሆናል።

👉 ጋብርኤል አህመድ ዳግም እይታ ውስጥ ገብቷል

በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ከሚልኒየሙ ወዲህ ከተመለከትናቸው ድንቅ የውጪ ሀገር ዜግነት ካላቸው ተጫዋቾቹ አንዱ የነበረው ጋብርኤል አህመድ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን ክለብ ከመቀያየር በዘለለ ሜዳ ላይ ፍፁም የወረደ ብቃትን እያሳየ ይገኛል።

በዘንድሮ የውድድር አጋማሽ ላይ ካልተሳካ የግማሽ የውድድር ዘመን የአዲስ አበባ ከተማ ቆይታ በኋላ ሰበታ ከተማን የተቀላቀለው ተጫዋቹ በመጨረሻዎቹ አራት ተከታታይ ጨዋታዎች በመጀመሪያ ተሰላፊነት በመጀመር ከጨዋታ ጨዋታ የመሻሻል ፍንጮችን እየሰጠ ይገኛል።

በተለይም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ከጅማ አባ ጅፋር ወሳኝ ሦስት ነጥብ ሲወስድ እጅግ ድንቅ ጊዜያትን አሳልፏል። በተለይም ወደ መሀል ሜዳ ተጠግተው ለመከላከል ይሞክሩ ከነበሩት የጅማ አባ ጅፋር ተከላካዮች ጀርባ የነበረውን ሰፊ ክፍተት በመረዳት በፍጥነት ይልካቸው የነበሩ የተመጠኑ ኳሶች የቡድኑ አጋሮቹ በፍጥነት ይህን ክፍተት እንዲጠቀሙ በማስቻል ረገድ የተዋጣላቸው ነበሩ። ከዚህም ባለፈ በተወሰኑ ቅፅበቶች በመካለከሉም ረገድ እንዲሁ አቅሙን በሚገባ አሳይቷል።

ምንም እንኳን ተጫዋቹ ከዚህ ቀደም በነበረባቸው ክለቦች ካሳየን የሜዳ ላይ ብቃት አንፃር ገና ሰፊ መንገድ ቢቀረውም በሰበታ ከተማ እያሳየን የሚገኘው የመሻሻል ፍንጭ ግን ተጫዋቹ ምናልባት ወደ ቀደመው ብቃት ይመልስ ይሆን ብለን ይበልጥ ተስፋ እንድናረግ የሚያስገድድ ነው።

👉 ሮበርት ኦዶንካራ ?

ለአምስት ያህል ጊዜያት የሊጉ ምርጥ ግብ ጠባቂ የተሰኘው ዩጋንዳዊው የግብ ዘብ ወደ ኢትዮጵያ ዳግም ከተመለሰ ወዲህ ያ የቀደመ ከግብ ፊት ያለው አስፈሪነት አብሮት ያለ አይመስልም። በዚህም በቀላሉ ግቦችን እያስተናገደ ይገኛል።

በተለይም ቡድኑ በእጁ የገባውን ሦሰት ነጥብ በተነጠቀበት የኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ግቦቹ ላይ የነበረው የውሳኔ አሰጣጥ እንዲሁም በጨዋታው አንዳንድ ቅፅበቶች የነበረው ንቃት እና ቅልጦፍና ጥያቄ የሚነሳበት ነበር።

ከሰባት ለሚልቁ ዓመታት በቅዱስ ጊዮርጊስ አስደናቂ ጊዜያትን ያሳለፈው ሮበርት በ2011 የውድድር ዘመን በአዳማ ከተማ ቆይታ ካደረገ ወዲህ ከሀገራችን የእግር ኳስ ተመልካች ዕይታ ርቆ ቆይቶ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ የሚመልሰውን ዝውውር ከፈፀመ ወዲህ ከዓመታት በፊት የማናውቀውን ሮበርትን እየተመለከትን አንገኛለን።

በእርግጥ በጊዮርጊስ ከነበሩት የመጨረሻዎቹ ዓመታት አንስቶ በተወሰነ መልኩ የብቃት መውረድ አጋጥሞት የነበረው ሮበርት የሚመዘነው ከቀደመው ማንነቱ ጋር እንደመሆኑ አሁን ላይ ያለው ብቃት አመርቂ አልሆነም። ግብ ጠባቂዎችን እያፈራረቁ በመጠቀም ላይ በሚገኙት ወልቂጤ ከተማዎች ቤት አራተኛ ጨዋታውን በዚህ ሳምንት ያደረገው ግብ ጠባቂው አራት ግቦችን ያስተናገደ ሲሆን ከዚህ ቀደም በተሰለፈባቸው ጨዋታዎችም እንዲሁ እንቅስቃሴው ብዙም አሳማኝ አልነበረም።

👉 የጫላ ተሺታ የውድድር ዘመኑ ፈጣን ግብ

ኢትዮጵያ ቡና ከወልቂጤ ያደረጉት አስገራሚ ክስተቶች የተሞላው ጨዋታ ማስገረሙን የጀመረው ገና ከጅምሩ ነበር።

ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የመሩት አልቢትር እያሱ ፈንቴ የጨዋታውን መጀመር ያበሰረውን ፊሽካ ማሰማታቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡናዎች በአቡበከር ናስር አማካኝነት ያስጀመሩትን ኳስ የተከላካይ አማካዩ አብነት ደምሴ ጋር ትደርሳለች እሱም ኳሷን ለኃይሌ ገ/ተንሳይ ያቀብላል ኃይሌም ለአማካዩ ታፈሰ ያደርሳል በዚህ ወቅትም በወልቂጤ ከተማ ተጫዋቾች መከበቡን የተረዳው ታፈሰ ሰለሞን በተቃራኒ የሜዳ አቅጣጫ ለሚገኘው የቡድን አጋሩ አበበ ጥላሁን ያደረገውን ኳስ ያቋረጠው ጫላ ተሺታ ቡድኑን መሪ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችሏል። ታድያ ይህ ሁሉ ሲሆን የፈጀው 12 ሰከንድ ያህል ብቻ ነው። ይህም ጎሏን በዘንድሮው የውድድር ዘመን የተቆጠረች ፈጣን ግብ ያደርጋታል።

👉 የፍፁም ዓለሙ ያልተገባ ምግባር

በባህር ዳር ከተማዎች በኩል የቡድኑ እጅግ ወሳኝ ተጫዋች የሆነው ፍፁም ዓለሙ በሜዳ ላይ በሥነ ምግባር ረገድ ከተመሰገኑ ተጫዋቾች የሚመደብ ቢሆንም በዚህኛው ሳምንት ግን ባልተለመደ መልኩ ራሱን ለመቆጣጠር ተቸግሮ ተመልክተነዋል።

በ22 ሳምንት የሊጉ ጉዞ ውስጥ በአብዛኛው ተሰልፎ መጫወት የቻለው ፍፁም እስከ ፋሲል ከነማው ጨዋታ ድረስ ሦስት የቢጫ ካርዶችን ብቻ የተመለከተ ቢሆንም በደርቢው ጨዋታ ባልተለመደ መልኩ ፍፁም ስሜታዊ ሆኖ ተመልክተነዋል።

በጨዋታው በመጀመሪያ አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ መሀል ሜዳ አካባቢ የፋሲል ከነማው በዛብህ መለዮን ለጉዳት የዳረገ እጅግ አደገኛ ጥፋትን የሰራው ተጫዋቹ ለሰራው ጥፋት አልቢትር ለሚ ንጉሴ ቢጫ ካርድ ሲያሳዩት ለያዥ ለገላጋይ አስቸግሮ ከዳኛው ጋር ለፀብ ሲጋበዝ የተመለከትነው ሲሆን በዚህ ሳያበቃ ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላም እንዲሁ በራሱ የሜዳ አጋማሽ ሽመክት ጉግሳ ላይ እጅግ አደገኛ ጥፋት በመስራቱ በሁለተኛ ቢጫ ከሜዳ ለመወገድ በቅቷል።

ምንም እንኳን ከቀይ ካርዱ በኋላ በተወሰነ መልኩ ወደ ቀልቡ የተመለሰው ተጫዋቹ ከሜዳው ሲወጣ ዓይኖቹ እምባ አዝለው ተመልክተናል። የደርቢ ጨዋታዎች በስሜት ደረጃ ከሌሎች ጨዋታዎች አንፃር የተጋጋሉ እንደሚሆኑ ቢገመትም በፍፁም ደረጃ ግን ባልተለመደ መልኩ በስሜት የመነዳት ሂደት ቡድን ላይ ከሚያስከትለው መዘዝ አንፃር ተጫዋቾች ልብ ሊሉት ይገባል።

👉 ድንቅ የነበረው ቢኒያም ገነቱ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ወላይታ ድቻን በገጠመበት እና ያለ ግብ በተጠናቀቀው ጨዋታ ሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ በወላይታ ድቻ በኩል ደምቀው ከዋሉ ተጫዋቾች መካከል ወጣቱ የግብ ዘብ ቢኒያም ገነቱ ይገኝበታል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን የዳንኤል አጃይ እና መክብብ ደገፉ ቀጥሎ ሦስተኛ ግብ ጠባቂ በመሆን የውድድር ዘመኑን ያጠናቀቀው ግብ ጠባቂው ዘንድሮ ደግሞ ከፅዮን መርዕድ እና ወንድወሰን አሸናፊ ቀጥሎ ሦስተኛ ግብ ጠባቂ ሆኖ ቢቆይም በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ተሰላፊ በሆነበት የመጀመሪያ ጨዋታው አስደናቂ ብቃቱን አሳይቷል።

በጨዋታው ጥሩ የሚባል ብቃትን ያሳየው ግብ ጠባቂው በጨዋታው አራት አስደናቂ ኳሶችን ማዳን የቻለ ሲሆን በተለይ በ55ኛው ደቂቃ የአማኑኤል ገ/ሚካኤልን የግንባር ኳስ ያዳነበት እንዲሁም በ85ኛው ደቂቃ ከዳግማዊ ዓርዓያ ላይ በግሩም ቅልጥፍና ያዳነበት ኳስ የግብ ጠባቂውን ብቃት ያጎሉ አጋጣሚዎች ነበሩ።

ምንም እንኳን በተጠባባቂነት ረጅም ጊዜያትን ቢያሳልፍም የመጀመሪያውን ጨዋታ ያውም የቅዱስ ጊዮርጊስ ዓይነት በሊጉ ጠንካራ ከሆነ ተጋጣሚ ጋር በዚህ መልኩ ማሳየቱ የሚያስደንቅ ነው።