“የሀገር ጥሪ ከመጣ ከእግርኳሱ ውትድርናን አስቀድማለሁ” ተሾመ በላቸው

👉 “በሥነምግባሩ በጣም ትልቅ ትምህርት አግኝቻለው…

👉 “ውትድርናው እና እግርኳሱ የሆነ የሚያመሳስላቸው ነገር አለ…

👉 “አንድ ጎል ባገባው ቁጥር አንድ ማዕረግ እንደሚሰጠኝ ቃል ተገብቶልኛል…

በዘንድሮው የውድድር ዓመት ደምቀው እየታዩ ካሉ ወጣት ተጫዋቾች መካከል አንዱ ከሆነው የመከላከያው ተሾመ በላቸው ጋር ቆይታ አድርገናል።

ባሳለፍነው የፕሪምየር ሊጉ የጨዋታ ሳምንት መከላከያ ሲዳማ ቡናን 5-3 ያሸነፈበት ጨዋታ ትኩረትን የሚስብ ነበር። የመከላከያ የሰሞኑ ድንቅ አቋም የታወቀ ቢሆንም አምስት ግቦችን አስቆጥሮ ሲዳማ ቡናን ይረታል ብሎ የጠበቀ ሰው ይኖራል ብሎ መገመት ያስቸግራል። በዚህ ጨዋታ ላይ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው የጦሩ ወጣት ተጫዋች ብቃት ግን የጨዋታውን ውጤት ያህል ብዙ ላያስገርም ይችላል። ምክንያቱም ስሙ በእግርኳሱ ቤተሰብ ዘንድ ከታወቀ ጊዜ ጀምሮ ቡድኑ ውጤት ይቅናውም አይቅናውም ሜዳ ላይ የሚችለውን ሁሉ ሲያደርግ ይታያል ፤ በአሁኑ የመከላከያ ስብስብ ውስጥ ብቸኛው ከወታደር ቡድን የተገኘው ተጫዋች ተሾመ በላቸው።

ትውልድ እና ዕድገቱ በሆለታ መስመር ኢንጪኒ በምትባል አካባቢ ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ እግርኳስ ተጫዋች የመሆን ህልም የነበረው ተሾመ ይህን ለማሳካት ከሰፈር ጀምሮ በፕሮጀክት በመታቀፍ ጭምር ሥልጠና አግኝቶ አሳልፏል። የፕሮጀክት ህይወቱ 2009 ላይ አንቦ ጎል ፕሮጀክትን በመቀላቀል ለሁለት ዓመታት የዘለቀ ነበር። እስከ 2011ድረስ በፕሮጀክቱ ቆይቶ በውሰት ወደ መከላከያ ተስፋ ቡድን መምጣት ችሏል። በተስፋ ቡድኑ እና በመከላከያ የወታደር ቡድን በአጠቃላይ ለሁለት ዓመታት ሲጫወት የቆየ ሲሆን በመቀጠልም ዘንድሮ በተስፋ ቡድኑ በነበረው መልካም እንቅስቃሴ ቢሸፍቱ ከዋናው ቡድን ጋር ለአስራ አምስት ቀን ሙከራ ካደረገ በኋላ ወደ ዋናው ቡድን ማደግ ችሏል።

የቀድሞው የመከላከያ አጥቂ ምንይሉ ወንድሙ አድናቂ የሆነው ተሾመ ከዚህ የተጨዋችነት መንገዱ ጎን ለጎን በዚህ ዓመት መስከረም ወር አካባቢ ወደ ውትድርናው ህይወት ገብቷል። በውርሶ የውትድርና ማሰልጠኛ የሁለት ወር ቆይታ ያደረገው ተጫዋቹ ሥልጠናውን በአግባቡ አጠናቆ ጨርሷል። ወደ ውትድርናው ዓለም የገባበትን ምክንያት ሲናገርም “በመከላከያ ተስፋ ቡድን በነበረኝ የሁለት ዓመት ቆይታ ከወታደሮች ጋር አብሮ የመኖር ዕድል ባገኘሁበት አጋጣሚ ያላቸው ፍቅር እና ዲሲፒሊን ውትድርናን እንድወደው ስላደረገኝ ‘ገብቼ መሰልጠን አለብኝ’ በማለት ነው መከላከያን መቀላቀል የቻልኩት” ይላል።

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሣህሌ የዘንድሮው ቡድናቸው መከላከያ በሁለት ድሎች ጥሩ አጀማመር ማድረግ ችሎ የነበረ ቢሆንም አምስተኛ ሳምንት ላይ ቡድናቸው ባህር ዳርን 2-0 ከረታ በኋላ ለአምስት ጨዋታዎች ድልም ሆነ ግብ እርቋቸው ሰንብተዋል። ለወጣቶች ዕድል በመስጠት የማይታሙት አሰልጣኙ በስድስተኛው ጨዋታ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ወጣቱን ተሾመ በላቸውን ፊት መስመር ላይ ከብሩክ ሰሙ ጋር አጣምረው ጀመሩ። ይህ ስሌት ሰምሮላቸው ጨዋታውን 3-1 ሲያሸንፉ ተሾመ የመከላከያን የግብ ጥም የቆረጠችውን እና እሱም አካዉንቱን የከፈተባትን ጎል አስቆጠረ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በአጥቂነት እንዲሁም ከቀኝ በሚናሳ አማካይነት ሚና ተሾመን በመከላከያ አሰላለፍ ውስጥ መመልከት የሁል ጊዜ ልማድ ሆኖ ቀጥሏል።

ዕድልን አግኝቶ ከመጠቀም ባለፈ በወጥነት ዕምነት እንዲጣልበት ማድረግ ለአንድ ወጣት ተጫዋች ቀላል አይደለም። “ ትልቁ ነገር ፍላጎት ነው። እግርኳስን ከልጅነቴ ጀምሮ ነው የምወደው። እዚህ ደረጃ መድረስ በጣም እፈልግ ነበር። አሰልጣኞቼም የሚሰጡኝ ነገር ተጨምሮ ይሄን ለማሳየት የቻልኩ ይመስለኛል።” የሚለው ተሾመ ግን አሁን ላይ ከመከላከያ ቁልፍ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ሆኗል። እስካሁን አራት ግቦችን አስቆጥሮ አንድ ግብ የሆነ ኳስ ያመቻቸው ተጫዋቹ ከፍ ያለ ትጋት በሚጠይቀው የቡድኑ ሰሞናዊ የጨዋታ ዕቅድ ውስጥ በመከላከል ሽግግር የተሰለፈበትን መስመር ለማገዝ ያለው ተነሳሽነት እና ቀጥተኛ የመከላከል ተሳትፎው ከግብ አግቢነት በዘለለ ጠንካራ ሰራተኝነቱን ያሳየ ሂደት ነው። ለዚህም ይመስላል ከወልቂጤው ጨዋታ አንስቶ እስካሁን ያለማቋረጥ በ13 ጨዋታዎች ላይ ጀምሮ ለ1015 ደቂቃዎች ሜዳ ላይ ተመልክተነዋል።

ለአብዛኞቹ ተጫዋቾቻችን ባዳ የሆነው ወጥነት እዚህ ወጣት ጋር የመገኘቱ ሚስጥር ብዙ ሊሆን ይችላል። ራስን መጠበቅ እና ጠንክሮ መስራት ግን ከምክንያቶቹ ውስጥ መካተታቸው የሚቀር አይሆንም። ይህ እንዲሆን ደግሞ የተሾመ የውትድርና ህይወት አስተዋፅዖ እንዳለው እሱም ያምንበታል። “በውትድርና ሥልጠና ለሁለት ወር ነው የቆየሁት ያም ቢሆን እጅግ ትልቅ ጠቀሜታ በሁሉም መልኩ አግኝቼበታለው ፤ በአካል ብቃቱም በአዕምሮም። የሀገር ፍቅርንም ተምሬበታለሁ። በውትድርና በተለይ በሥነ ምግባሩ በጣም ትልቅ ትምህርት አግኝቻለው።” ይላል።

ተጫዋቾችን በሥነምግባር ፣ በአዕምሮ እና በአካልብቃት ከመቅረፅ ባለፈም ውትድርና እና እግርኳስ ከዝግጅት ጀምሮ እስከአተገባበር ድረስ በርካታ መመሳሰሎች አሏቸው። በዚህ ዕድሜው ሁለቱንም አብሮ እያስኬደ ያለው ተሾመ ይህን ቁርኝታቸውን በአግባቡ ተረድቶታል። “ ውትድርናው እና እግርኳሱ የሆነ የሚያመሳስላቸው ነገር አለ። በጦርነት ጠላትን ምሽግ ይዘህ ቀስ በቀስ እንዴት ማጥቃት ፣ መከላከል እንዳለብህ ትሰለጥናለህ። በእግርኳሱም በተመሳሳይ እንዴት ኳስ መሸፈን እንዳለብህ ፣ ኳሱን እንዴት አድርገህ ወደ ጎልነት እንደምትቀይር ፣ በህብረት እንዴት ማጥቃት እና መከላከል እንዳለብህ የተለያዩ ታክቲኮችን ትሰለጥናለህ። እነኚህ ሁለቱን የሚያመሳስላቸው ነገሮች ናቸው። ” በማለት የሰጠን ቅልብጭ ያለ ገለፃ የተጨዋቹን ብስለት የሚያሳይም ነው።

ለተሾመ ጎሎችን ማስቆጠር በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ዝርዝር ውስጥ ከመገኘት ያለፈ ትርጉም አለው። ይኸውም ጎል ሲያገባ ቃል ከተገባለት የማዕረግ ዕድገት ጋር ይያያዛል። አራት ግቦች ላይ የደረሰው ተጫዋቹ ሁኔታውን ሲያብራራ “ ከላይ ያሉ የበላይ አካሎች የተላለፈ ሀሳብ ነው። ያው አንድ ጎል ባገባው ቁጥር አንድ ማዕረግ እንደሚሰጠኝ ቃል ተገብቶልኛል። ይህ እንደማበረታቻ የሚሰጠኝ ነው። በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ ፤ ይሄን የማይፈልግ የለም። ከዚህ በኋላም የማዕረግ ዕድገቱን ለማግኘት የተሻለ ነገር ለመስራት አስባለው።” ይላል። በዚህ ሳምንት አራተኛ የሊግ ጎሉን ያስቆጠረው ተሾመ የሀምሳ ዓለቃ ማዕረግ ላይ የደረሰ ሲሆን ከፊቱ ባሉት ጨዋታዎች የማዕረግ ዕድገቱን ስለማስቀጠል በማለም ላይ ይገኛል።

የተጫዋቹ ልባምነት ግን ከዚህም አለፍ ይላል። የማዕረግ ዕድገቱን ለመጠሪያነት ብቻ አይደለም የሚፈልገው። ይህንን ያረጋገጠልን “አሁን ላይ በቋሚነት እየተጫወትክ ባለበት ሰዓት በድንገት ሀገራዊ ጥሪ ቢመጣ እና ለውትድርና ብትጠራ ምላሽህ ምን ይሆናል ?” ብለን ለጠየቅነው ጥያቄ የሰጠን መልስ ነው። ተሾመ በምላሹ እንዲህ ብሏል ” እንዴ ጥሪው ከመጣ መጀመርያማ ሥራዬ መከላከያ ነው። እግርኳሱ ሊቀር ይችላል። ጥሪውን ተቀብዬ ወደ ሠራዊቱ ነው የምቀላቀለው። የሀገር ጥሪ ከመጣ ከእግርኳሱ ውትድርናን አስቀድማለሁ”

በእግርኳሱም ገና ጀማሪ መሆኑን እና ከዚህ በላይ ብዙ ሰርቶ ማደግን እንደሚያስብ የነገረን ተሾመ ስለደስታ አገላለፁም ነግሮናል። ግብ ካስቆጠረ በኋላ አንድም ወታደራዊ ሰላምታ በመስጠት ሁለትም እጁን በማቆላለፍ ደስታውን ስለሚገልፅባቸው መንገዶች ጠይቀነው “ ወታደራዊ ሰላምታው ግልፅ ነው ለሁሉም የሠራዊት አባላት ያለኝን አክብሮት እና ፍቅር ለመግለፅ ነው። እጄን የማቆላልፍበትን ምክንያት ግን ብዙ ሰው ይጠይቀኛል። ግን ምንም የተለየ ምክንያት የለኝም። ያው ራሴ የምለይበት የደስታ አገላለፅ ለመፍጠር እንጂ ሌላ ሚስጢር የለውም።” ሲል ተናግሯል።

የዚህ ፅሁፍ መቋጫ የሚሆነው እና ተጫዋቹ ሀገራዊ ስሜቱን የሚያሳይ መልስ የሰጠበት ጥያቄያችን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ ስለመጫወት ያለውን ህልም በተመለከተ ነበር። መልሱ…

“ ምንም ነገር አልፈልግም ፤ ብዙ ማለት አልችልም። ካለኝ ጉጉት እና ፍቅር የሀገሬን ብሔራዊ ቡድን ማልያውን አንድ ቀን መልበስ ብቻ ነው የምፈልገው። “