ባህር ዳር ከተማ ቅጣት ተላልፎበታል

የሊጉ የበላይ አካል በ23ኛ ሳምንት ተከስተዋል ባላቸው የዲሲፕሊን ግድፈቶች ላይ ውሳኔ አሳልፏል።

የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ከሳምንት በፊት በባህር ዳር ከተማ መደረግ እንደጀመረ ይታወቃል። በከተማው የሚደረገው ሁለተኛ ሳምንት (23ኛ የጨዋታ ሳምንት) ከትናንት በስትያ ከተገባደደ በኋላ የውድድሩ የበላይ አካል አክሲዮን ማኅበር በዲሲፕሊን ግድፈቶች ላይ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

አክሲዮን ማኅበሩ ከደቂቃዎች በፊት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት ባህርዳር ከተማ ከፋሲል ከነማ ጋር ሲጫወት የውድድር አመራሮችን አፀያፊ ስድብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት የቀረበበት ሲሆን የክለቡ ደጋፊዎች በፈፀሙት ጥፋት ክለቡ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ብር 50000 /ሃምሳ ሺህ/ እንዲከፍል ውሳኔ ተላልፏል ።

በቡድን አመራሮች አቶ አሸብር አሰፋ (ሲዳማ ቡና የቡድን መሪ) ክለባቸው ከፋሲል ከነማ ጋር በነበረው የ22ኛ ሳምንት ቅድመ ጨዋታ ስብሰባ ወቅትና የዕለቱ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ ፀብን የሚያነሳሳ ንግግር ስለመናገራቸው እንዲሁም ውድድሩ ከተጠናቀቀ በኋላ በእለቱ ዋና ዳኛ ላይ በሃሰት የተመሰረተ ትችት ስለመስጠታቸው ሪፖርት የቀረበባቸውና እና በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡ በኮምንኬ ቁጥር 22 ጥሪ ቢደረግላቸውም በጥሪው ዕለት ቦታና ያልተገኙ ላጠፉት ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 3/ሶስት/ ወር እንዲታገዱና ብር 10000 /አስር ሺህ / እንዲከፍሉ ተወስኗል። በተጨማሪም አቶ አዳሙ ኑመሮ (ሃዋሳ ከተማ) የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ) ክለባቸው አዲስ አበባ ከተማ ጋር በነበረው የ23ኛ ሳምንት እግር ኳስ ጨዋታ ዳኛን አፀያፊ ስደብ ተሳድበው በቀይ ካርድ ከሜዳ ስለመወገዳቸው ሪፖርት የቀረበባቸው አሰልጣኙ ባጠፉት ጥፋት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድርና ስነስርዓት ደንብ መሰረት 3 ጨዋታ እንዲታገዱና ብር 10000 /አስር ሺህ / እንዲከፍሉ ተወስኗል።