ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

በጨዋታ ሳምንቱ ትኩረት የሳቡ አሰልጣኞች ላይ ያተኮሩ ጉዳዮች የተከታዩ ፅሁፋችን አካል ናቸው።

👉 አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ እና ሲዳማ ተለያይተዋል

በጨዋታ ሳምንቱ በመከላከያ ያልተጠበቀ የ5-3 ሽንፈት ያስተናገዱት ሲዳማ ቡናዎች ከጨዋታው መጠናቀቅ ሰዓታት በኋላ ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር ስለመለያየታቸው ይፋ ተደርጓል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አጋማሽ ላይ ባልተለመደ መልኩ ሲንገዳገድ የነበረውን ሲዳማ ቡናን ተረክበው በሊጉ ማቆየት የቻሉት አሰልጣኙ ዘንድሮ ደግሞ ቡድኑን በሊጉ ወደ ቀደመው ተፎካካሪነቱ ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ምንም እንኳን የውድድር ዘመኑን የጀመረበት መንገድ መጠነኛ መንገራገጮች የነበሩት ቢሆንም በተለይ በ7ኛ የጨዋታ ሳምንት በፋሲል ከነማ የ4-0 ሽንፈት ካስተናገዱ ወዲህ ሲዳማ ጥሩ የሚባልን እምርታ በማሳየት ከጥቂት ሳምንታት በፊት በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ራሱን ማካተት ችሎ ነበር።

በድንገት ግን በብዙ መልኩ እየጎለበተ ስለመምጣቱ ስናወራለት የነበረው ቡድን በተለይ በመጨረሻዎቹ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ያጋጠሙት ሽንፈቶች የቡድኑ የአፍሪካ ውድድሮች ህልም እያደበዘዙት ይገኛል። ታድያ በእነዚህ ውጤቶች ደስተኛ ያልሆኑት የክለቡ አመራሮች ከአሰልጣኙ ጋር የተለያዩ ሲሆን በምትካቸውም ረዳታቸው በመሆን ሲያገለግል የነበረው የቀድሞው የቡድኑ ከ20 ዓመት በታች አሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመን ሲዳማን በቀሪ ጨዋታዎች እንዲመራ ሾመውታል።

👉 አነጋጋሪው አሰልጣኝ አሁንም በአነጋጋሪ አስተያየት ተመልሰዋል

አስገራሚ አስተያየቶችን በመስጠት የሚታወቁት የአሁኑ የአዲስ አበባ ከተማ አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ዳግም ወደ ሜዳ በተመለሱበት እና ቡድናቸው ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ ጅማሮ እና መጠናቀቅ በኋላ አስገራሚ አስተያየትን ሲሰጡ ተደምጠዋል።

በአስተያየታቸው አሰልጣኙ ሲናገሩ በአዲሱ ቡድናቸው ዋነኛ ስራቸው የሚሆነው ‘ቡድን ማነሳሳት እንጂ ማሰልጠን አይደለም’ የሚልን ሀሳብ ሲሰጡ ይህን ቡድን በሊጉ በማቆየት በሊጉ አዲስ ታሪክ ለመፃፍ ስለማሰባቸው ተናግረዋል።

በተጨማሪም በንግግራቸው ፤

“የኳስ ነገር የማይታወቅ በመሆኑ እንጂ በእርግጠኝነት የምናገረው አዲስ አበባ ይወርዳል ብሎ መናገር ሞኝነት ነው።” የሚል ድፍረት የተሞላበትን ሀሳብ ሰጥተዋል።

ሊጠናቀቅ ሰባት የጨዋታ ሳምንት በቀረው የሊግ ውድድር አሰልጣኝ ጳውሎስ እንዳሉት ቡድኑን በሊጉ ማቆየት ይቻላቸው ይሆን የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

በሊጉ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በመጀመሪያው ዙር የድሬዳዋ ከተማ አሰልጣኝ የነበሩት አሰልጣኝ ፍሰሀ ጥዑመልሳን እንዲሁ በተመሳሳይ በሚሰጧቸው አስተያየቶች ርዕሰ ዜናን ይፈጥሩ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ ባለተራው አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ይመስላሉ።

👉 ቡድናቸውን የተገነዘቡት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም

ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ ካደረጉት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በነበረው ድህረ ጨዋታ ቃለ መጠይቅ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ካነሷቸው ሀሳቦች መካከል

“ ከወላይታ ዲቻ አቅም አንፃር ስናየው ይህንን ነጥብ ለማግኘት የተከተልነው አቅጣጫ ጥሩ ነበር ማለት እችላለው።

“…..ሲጠቃለል ግን ከራሳችን ጋር ስናነፃፅረው፣ በአቅማችን ልክ ሜዳ ላይ የተገበርነው አዋጪ ነበር።”

“ እኔ ደስተኛ ነኝ ፤ ምክንያቱም ሊጉ እየተጠናቀቀ ነው። ስለዚህ ከትልቅ ቡድን አንድ ነጥብ ማግኘት ቀላል አይደለም።

“ይህን ታሳቢ አድርገን ይህን ነጥብ ማግኘታችን ጥሩ ነው። ከተጋጣሚያችን አንፃር አቅማችን ይሄ ነው። በአቅማችን ልክ ነው ያቀድነው አቻ መሆኑ ተገቢ ነው።” የሚሉት ትኩረት የሚስቡ ሀሳቦች ነበሩ።

ከሌሎች በሰንጠረዡ አናት ከሚገኙ ቡድኖች አንፃር በአነስተኛ የዝውውር በጀት በአማካይ የጥራት ደረጃ ላይ በሚገኙ ተጫዋቾች የተሞላውን ስብስብ እየመሩ የሚገኙት አሰልጣኝ ፀጋዬ እስከ አሁን ከዕቅድ በላይ እየፈፀሙ ይገኛል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን አሰልጣኝ ፀጋዬ ገና ከውድድሩ ጅማሮ አንስቶ በጊዜያዊ ውጤቶች ሳይታለሉ በአቅማቸው ልክ በማቀድ አንገቱን ደፍቶ የሚጥር ቡድንን ገንብተው እያሳዩ ይገኛል።

ታድያ ይህ በአቅም ልክ የማሰብ ነገር በሀገራችን እግርኳስ እምብዛም የተለመደ ባይሆንም አሰልጣኝ ፀጋዬ እና ቡድናቸው ይህን በተግባር እያሳዩን ይገኛሉ። ነገን የተሻለ ለማድረግ አሁናዊ ሁኔታን ገምግሞ መረዳት አስፈላጊ እንደመሆኑ የአሰልጣኝ ፀጋዬ ይህ አቅም በአግባቡ የመረዳት ነገር ብዙዎች ትምህርት ሊወስዱበት የሚገባ አስተሳሰብ ነው።

👉 የባህር ዳር መሻሻል ከወዴት ነህ ?

በ12ኛ የጨዋታ ሳምንት ሀዋሳ ከተማን ከረቱ ወዲህ የመጀመሪያ ድላቸውን ለማስመዝገብ የተቸገሩት ባህር ዳር ከተማዎች የጨዋታ ሳምንቱን በወራጅ ቀጠናው ቀርበው በ26 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

በ11 ጨዋታዎች ላይ ማሸነፍ ያልቻለውን ባህር ዳር ግብ ካስቆጠረም እንዲሁ 270 የጨዋታ ደቂቃዎች ተቆጥረዋል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚገኘውን ቡድንን እየመሩ የሚገኙት አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ እጅግ ከፍ ያለ ጫና ውስጥ ይገኛሉ።

ከውድድር ዘመኑ ጅማሮ አንስቶ ቡድኑ ከፍ ባለ ደረጃ ቢጠበቅም በሚጠበቅበት ደረጃ ላይ ለመገኘት ግን ፈፅሞ ተቸግሯል። ይባስ ብሎ አሁን ላይ ሊጉ ሊጠናቀቅ እየተቃረበ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ከወራጅ ቀጠናው በ3 ነጥብ ርቀው 13ኛ ደረጃ ላይ የመገኘታቸው ነገር ሁኔታውን አስከፊ ያደርገዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ ግን አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ሁሌም ቢሆን ከጨዋታዎች መጠናቀቅ በኋላ በሚሰጡት አስተያየት ቡድኑን በአዕምሮ ረገድ ስለማሻሻል እንዲሁም ይቀሩናል በሚሏቸው ጉዳዮች ላይ ስራዎችን በመስራት ወደ ተፎካካሪነት የመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው ሲናገሩ ቢደመጥም ባህር ዳር ግን ሜዳ ላይ በሚታይ ደረጃ እምርታዎችን ለማሳየት ተቸግሯል።

በተለይም አሰልጣኙም ደጋግመው እንደሚያነሱት የቡድኑ የማጥቃት አቅም እንዳሉት አማራጮች ፍሬ ማስገኘት ሳይችል ቀጥሏል። ለአብነት ይህን አነሳን እንጂ ሌሎቹም የቡድኑ ችግሮች መፈታት ያለመቻላቸው ጉዳይ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው ፤ ስለመሻሻል ቢወራም ችግሮቹ የመቀጠላቸው ጉዳይ ትኩረት የሚሻ ነው።

ይህ ሂደት በቅድሚያ ተጠያቂ የሚያደርገው አሰልጣኙን እንደመሆኑ ተጠባቂዎቹን መሻሻሎች ቡድኑ ሜዳ ላይ ማስመልከት ካልቻለ አሰልጣኙ እየተናጠ ከሚገኘው መንበራቸው ላይ የመቆየታቸው ነገር አጠራጣሪ ሆኗል።

ያጋሩ