በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የተጫዋች ተገቢነት ጋር ክስ አቅርቦ የነበረው ወላይታ ድቻ ክሱ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡
በተጠናቀቀው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ23ኛ የጨዋታ ሳምንት ወላይታ ድቻ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተጫውቶ ያለ ግብ ካጠናቀቀ በኋላ በተጋጣሚው ላይ ክስ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ክለቡ በክሱ “ቅዱስ ጊዮርጊስ በጨዋታው ላይ በሦስት ጊዜ አምስት ተጫዋቾችን ሦስቱ በአረንጓዴ ቴሴራ ሁለቱን በቢጫ ቴሴራ መቀየር ሲችል ክለቡ ይሄን ህግ በመጣስ ከእረፍት በፊት ከነዐን ማርክነህን በሀይደር ሸረፋ ፣ ከእረፍት መልስ ደስታ ደሙን በሱለይማን ሰሚድ ፣ ቡልቻ ሹራን በዳግማዊ አርአያ እና ጋቶች ፓኖምን በናትናኤል ዘለቀ የቀየረበት አራት ቅያሪ ከተቀመጠው ደንብ ውጪ በመሆኑ የጨዋታው ውጤት ይገባናል።” በማለት ክለቡ አቤቱታውን ማቅረቡን በዘገባችን ጠቅሰን ነበር፡፡
የፕሪምየር ሊጉ የበላይ አካል ለወላይታ ድቻ በዝርዝር እንዳስረዳሁ ከሆነ “ጨዋታ እየተደረገ እያለ አምስት ተጫዋቾችን ሁለቱን በቢጫ ፣ ሶስቱን ደግሞ በአረንጓዴ ቴሴራ በሦስት አጋጣሚዎች መቀየር ይቻላል፡፡ ይሄ የሆነበት በቅያሪ ሰዓት ጨዋታ መቆም ያለበት ሶስት ጊዜ ብቻ ሲሆን ነገር ግን በእረፍት ሰዓት በሚደረጉ ቅያሬዎች ከተቀመጠው የቁጥር ገደብ ውጪ መፈፀም ስለሚቻል እና የተቀመጠው ደንብ ስለሚፈቅድ እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ በእረፍት ወቅት ቀይሮ ያስገባው ዳግማዊ አርዓያ ቢጫ ቴሴራ ተጠቃሚ የሆነ በመሆኑ ከተቀመጠው የቅያሪ ቁጥር ውጪ መሆኑን በመግለፅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ምንም የፈፀመው የህግ ስህተት የለም” በማለት የድቻ ክስ ተቀባይነት ሳያገኝ ውድቅ ሆኗል፡፡