የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት የመጀመርያ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ ሀዋሳ ከተማ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዲያ ሆሳዕና ድል ቀንቷቸዋል።
ረፋድ አምስት ሰዓት መከላከያ እና የምድቡ መሪ ሀዋሳ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በሀዋሳ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በመጀመርያው አጋማሽ ብዙም ፉክክር ያልተመለከትንበት ሲሆን የአየር ላይ ኳሶች ተደጋጋሚ በዝተው ጨዋታውን አሰልቺ አድርገውት አርወፍደዋል። በጥንቃቄ እየተጫወቱ በሚገኙ ክፍተቶች ጎል ለማስቆጠር ያሰቡት ሀዋሳዎች የመጀመርያ ጎላቸውን በ10ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ከተከላካይ ጀርባ ከርቀት የተላከለትን ኳስ ፈጣኑ አጥቂ ዮርዳኖስ ፀጋዬ ተከላካዮችን አምልጦ በመውጣት የግብ ክልሉን ለቆ ኳሱን ለማምከን የወጣው ግብ ጠባቂው አናት ላይ በመላክ ድንቅ ጎል አስቆጥሯል። በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻሉ የነበሩት መከላክያዎች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን የአቻነት ጎል አጥቂው ጳውሎስ መርጋ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም በአግባቡ ሳይጠቀምበት የቀረው አጋጣሚ አስቆጪ ነበር። መረጋጋት ተስኗቸው የቆዮት የመከላከያ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ ዮርዳኖስ ፀጋዬ ብቻውን ከግብ ጠባቂው ጋር ቢገናኝም ሳይጠቀምበት የቀረው ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ጎል መሆን ሳይችል ቀርቷል።
በሁለተኛው አጋማሽ መከላከያ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ጨዋታውን ለመቆጣጠር እና የአቻነት ጎል ፍለጋ ጥረት ለማድረግ ባሰቡበት አጋጣሚ 47ኛው ደቂቃ ጎል ሊቆጠርባቸው ችሏል። በዚህም ከመዓዘን ምት የተሻገረውን የቀኝ መስመር ተከላካዩ በረከት ካሌብ በግንባሩ በመግጨት በአስቆጠረው ጎል መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ተጭነው የተጫወቱት መከላከያዎች የሀዋሳን ተከላካዮች ማስከፈት ተስኗቸው በተደጋጋሚ ከሳጥን ውጪ ሙከራ ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን ለዚህም ማሳያ በሁለት አጋጣሚ አማካዩ ጳውሎስ መርጋ እና ተከላካዩ አብዱራህማን ከርቀት የመቱትን ኳስ ንቁ የነበረው የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ንብረት ዘንባባ አድኖባቸዋል።
ከተወሰደባቸው ብልጫ ቀስ በቀስ በመውጣት በመልሶ ማጥቃታት መሪነታቸውን ለማስፋት የተንቀሳቀሱት ሀዋሳዎች በ75ኛው ደቂቃ ብሩክ ታደለ ከርቀት መቶ የመከላከያ ግብጠባቂ አሚን ከድር በግሩም ሁኔታ ከአዳነበት ጊዜ ጀምሮ ተነቃቅተው መጫወት ቀጥለው በ80ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን ወደ ሦስት ከፍ ያድጉበትን ጎል አስቆጥረዋል። ጎሉንም በዛሬው ጨዋታ የመከላከያ ተከላካዮችን ሲረብሽ የዋለው እና ወደ ፊት ጥሩ አጥቂ ለመሆን እየተንደረደረ የሚገኘው ፈጣኑ አጥቂ ዮርዳኖስ ፀጋዬ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አድርጎታል። ጨዋታውም ምንም የተለየ ነገር ሳያስመለክተን በሀዋሳ ከተማ 3–0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ የምድቡ አሸናፊ ለመሆን የሚያደርገውን ግስጋሴ ሲያጠናክር ነገ አዲስ አበባ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና አሸናፊነት የሚጠናቀቅ ከሆነ አልያም ጨዋታው በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ ሀዋሳ ከተማ አንድ ጨዋታ እየቀረው የምድቡ አሸናፊ መሆኑን ያረጋግጣል።
ቀትር ላይ በቀጠለው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጨዋታ ብልጫ ጋር ከመመራት ተነስቶ ድሬዳዋ ከተማን በሀብቶም ገ/እግዚአብሔር ሦስት ጎሎች አሸንፎ ሊወጣ ችሏል።
ቀዝቀዝ ብሎ በጀመረው በዚህ ጨዋታ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ወደ ጎል በመድረስ ረገድ ፈረሰኞቹ የተሻሉ ነበር። በተለይ በመጀመርያው አጋማሽ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አጥቂው ሔኖክ ዮሐንስ አንድ ለአንድ ከግብጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ያልተጠቀመበት አጋጣሚ የሚያስቆጭ ነበር። መከላከልን ምርጫቸው አድርገው በመልሶ ማጥቃት የጎል ዕድል ለመፍጠር ያሰቡት ድሬዳዋዎች በአንድ የጎል ሙከራ ጎል ማስቆጠር ችለዋል። 43ኛው ደቂቃ ከራሳቸው የሜዳ ክፍል በቀጥታ ተከላካዩ ዱጉምሳ አብደላ ወደ ፊት የመታው ኳስ መሬት ነጥሮ ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኑን ቀዳሚ በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ጨዋታው ለመመለስ በተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት ፈረሰኞቹ ውጤቱን መቀልበስ የሚችሉበትን ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል። በዕለቱ ድንቅ ጊዜ ያሳለፈው ሀብቶም ገ/እግዚአብሔር በጥሩ ቅብብል ወደ ፊት በማምራት የተቀበለውን ኳስ ከሳጥን ውጭ በመምታ ግሩም ጎል በ60ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል። ከአቻነቱ ጎል በኋላ በተደጋጋሚ የድሬዳዎችን ግብ የፈተሹት ቅዱስ ጊዮርጊሶች መሪ የሆኑበትን ጎል 66ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። በዚህም የተገኘውን የመዓዘን ምት ሀብቶም ገ/እግዚአብሔር ከረጃጅሞቹ የድሬዳዎቹ ተከላካዮች መሐል ሾልኮ ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር ፈረሰኞቹ መሪ መሆን ቻሉ።
አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር እንደ ቡድን የተደራጀ እንቅስቃሴ ያላስመለከቱን ድሬዳዋዎች ሌላ ሦስተኛ ጎል በ73ኛው ደቂቃ ተቆጥሮባቸዋል። የዛሬው የጨዋታው ኮከብ እና ወደፊት ጥሩ አጥቂ እንደሚወጣው ማሳየት የቻለው ሀብቶም ከተከላካዮች መሐል ሾልኮ በመውጣት ተረጋግቶ የግብጠባቂውን አቋቋም በማየት ለቡድኑ ሦስተኛ ለራሱ ሐት ትሪክ የሰራበትን ጎል አስቆጥሯል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር የሚችሉበት አጋጣሚ ቢፈጠርም ሳይጠቀሙበት ቀርተው ጨዋታውን ከመመራት ተነስተው ደካማውን ድሬዳዋ ከተማን 3-1 አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል።
ውጤቱን ተከትሎ ፈረሰኞቹ የዘንድሮ ዓመት ውድድራቸውን በአራተኛ ደረጃ አጠናቀው ከአሰላ ወደ አዲስ አበባ ነገ የሚያቀኑ ሲሆን ድሬዎች ባሉበት ደረጃ የሚቀመጡ ይሆናል።
ባቱ ላይ እየተደረገ በሚገኘው የምድብ ሀ ውድድር ዛሬ አንድ ጨዋታ ተደርጎ ሀዲያ ሆሳዕና በሹሊ ያዕቆብ እና ተመስገን ደነቀ ጎሎች ባህር ዳር ከተማ 2-0 ማሸነፍ ችሏል።
በዚሁ ምድብ ሊካሄዱ የነበሩት የአርባምንጭ ከተማ እና ሀላባ ከተማ እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሰበታ ከተማ ጨዋታ ሀላባ እና ሰበታ ባለመቅረባቸው አርባምንጭ እና ንግድ ባንክ የ3-0 ፎርፌ አሸናፊ ሆነዋል።