ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | 23ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት በተደረጉት ጨዋታዎች ላይ ጥሩ ብቃት ያሳዩ ተጫዋቾች እና ዋና አሰልጣኝን በተከታዩ ምርጥ ቡድን ውስጥ አካተናል።

አሰላለፍ 4-4-2 ዳይመንድ

ግብ ጠባቂ

ዳግም ተፈራ – ሀዋሳ ከተማ

ምንም እንኳን ሁለት ግቦችን ቢያስተናግድም በቦታው ሌላው ድንቅ ሳምንት ካሳለፈው የወላይታ ድቻው ቢኒያም ገነቱ ጋር የተፎካከረው ዳግም እንዳለፈው ሳምንት ሁሉ ዛሬም ተመራጭ ግብ ጠባቂያችን ሆኗል። በጨዋታው በእንቅስቃሴ ካዳናቸው ኳሶች በዘለለ የሪችሞንድ ኦዶንጎን ፍፁም ቅጣት ምት በሦስት ሙከራዎች ወደ ግብነት እንዳይቀየር ያደረገው ጥረት ለሀዋሳ አንድ ነጥብ አስገኝቷል።

ተከላካዮች

ጌቱ ኃይለማሪያም – ሰበታ ከታማ

ጌቱም እንደ ዳግም ሁሉ በተከታታይ ሳምንታት የምርጥ ቡድናችን አባል መሆን ችሏል። ከድሬዳዋ ከተማው እንየው ካሳሁን ጋር ለምርጫው የተወዳደረው ተጫዋቹ በተደጋጋሚ ለሰበታ የቀኝ መስመር ጥቃት መነሻ ሆኖ የተመለከትነው ሲሆን ከፈጠራቸው የግብ ዕድሎች ውስጥም አንዷ በንስባምቢ አማካይነት ወደ ግብነት ተቀይራለች።

ደጉ ደበበ – ወላይታ ድቻ

የጦና ንቦቹ ቅዱስ ጊዮርጊስን በተደራጀ መከላከል ነጥብ ማስጣል ሲችሉ የቀድሞው ክለቡን የገጠመው ደጉ አሁንም አስፈላጊ ተጫዋች መሆኑን አሳይቷል። በአየር እና በቅብብል የሚመጡ ጥቃቶችን ከማስጣል ባለፈ እንደቡድን የተቀመረውን የቡድኑን የመከላከል መዋቅር ተረጋግቶ በመምራት የአንጋፋው ተከላካይ ልምድ ጠቃሚ ነበር።

በረከት ሳሙኤል – ሰበታ ከተማ

በርካታ ግቦች በተቆጠሩበት የጨዋታ ሳምንት ተከላካዮችን መምረጥ ቀላል ያልነበረ ቢሆንም የሰበታውን በረከት የደጉ አጣማሪ አድርገነዋል። ተጫዋቹ በዋናነት ጥራታቸውን የጠበቁ ሸርተቴዎቹ የጅማ ተጫዋቾችን የማጥቃት ሩጫዎች ይገታበት የነበረበት መንገድ ሰበታ ተጨማሪ ግቦች አስተናግዶ ከቆይታ በኋላ ያገኘውን ሦስት ነጥብ እንዳያጣ በማስቻሉ ተመርጧል።

አስራት ቱንጆ – ኢትዮጵያ ቡና

ኢትዮጵያ ቡና አስደናቂ ገድል በፈፀመበት ጨዋታ የአምናውን የግራ ወገን አስፈሪነቱን መልሶ ሲያገኝ የአስራት ቱንጆ ሚና ወሳኝ ነበር። በመስመር ተከላካይነት እና አጥቂነት መጫወት የሚችለው አስራት ከፊት በግራ ተሰልፎ ቡድኑ በዚያ መስመር ተደጋጋሚ ጫና እንዲፈጥር ምክንያት ከመሆን ባለፈ የፍፁም ቅጣት ምት እንዲያገኝ ከማስቻሉ ባሻገር ቡድኑን አሸናፊ ያደረገችውን ግብም ራሱ ማስቆጠር ችሏል።

አማካዮች

ቻርለስ ሪባኑ – አዲስ አበባ ከተማ

የተረጋጋው የተከላካይ አማካይ በዚህም ሳምንት በቦታው ያሳየው እንቅስቃሴ ለአዲስ አበባ ተጨማሪ የማጥቃት ጉልበት ሆኖ ነበር። ለተከላካይ መስመር ሽፋን ከመስጠት ባለፈ ተጫዋቹ ከጥልቅ በቀጥታ ኳሶችን በመላክ አደጋዎችን ከመፍጠር በተጨማሪ በቅብብሎች ወደ ፊት ይሄድ የነበረበት መንገድ ማጥቃቱን በእጅጉ ያገዘ ሲሆን የሪችሞንድ ኦዶንጎ ግብ ስትቆጠር አመቻችቶ የማቀበል ድርሻውም የእርሱ ነበር።

ቢኒያም በላይ – መከላከያ

መከላከያ አምስት ግቦችን ባስቆጠረበት ጨዋታ ቢኒያም እንደሰሞኑ ሁሉ ከኳስ ውጪ የቡድኑን የመከላከል መዋቅር በትጋት በማገዝ የማጥቃቱ ደግሞ ዋና ሰው በመሆን አሳልፏል። ቀዳሚውን ግብ ራሱ ሲያስቆጥር በሁለተኛው ግብ ሂደት ላይ አስተዋፅዖ ያደረገው ቢኒያም የጦሩ የመሀል ክፍል በፈጣን ጥቃት ደጋግሞ ወደ ግብ የመድረሱ ምክንያት ነበር።

ተሾመ በላቸው – መከላከያ

ከቀኝ መስመር በመነሳት የጦሩን ፈጣን ጥቃቶች ሲያግዝ የነበረው ወጣቱ ተሾመ በአጥቂነት ባህሪው ሳጥን ውስጥ በመገኘት ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። ከዚህ ውጪ እንደ ቢኒያም ሁሉ መከላከሉን በታታሪነት በማገዝ እና የቅብብል አማራጮችን በመፍጠር ጨዋታው ጦሩ ባሰበበት መንገድ እንዲዘልቅ ወሳኝ ሚና ነበረው።

አብዱርሀማን ሙባረክ – ድሬዳዋ ከተማ

ከግብ አስቆጣሪነቱ በላይ የአማካይነት ሚና እየተሰጠው የቡድኑን የጨዋታ አቀጣጣይነት ሚና ሲወጣ የምንመለከተው አብዱርሀማን ድንቅ ሳምንትን በማሳለፉ የዳይመንዳችን የፊተኛው ጫፍ አድርገነዋል። ተጫዋቹ በጨዋታው ሁለት ግቦችን ከማስቆጠሩ በላይ ኳስ እየነዳ በመግባት የድሬዳዋን የመጨረሻ ዕድሎች በመፍጠሩ በኩል ትልቅ ሚና የተወጣ ሲሆን የሄኖክን የመጀመሪያ ግብም ማመቻቸት ችሏል።

አጥቂዎች

አቡበከር ናስር – ኢትዮጵያ ቡና

የወልቂጤው ድል አቡበከር አሁንም የኢትዮጵያ ቡና ሁሉ ነገር መሆኑን ያሳየበት ነበር። በጨዋታ እና በፍፁም ቅጣት ምት ግቦችን ያስቆጠረው አቡበከር ቡና ወደ ግራ አድልቶ በፈጠረው ጫና ውስጥ ዋነኛው የቅብብል ማዕከል ሆኖ በመዋል ቀሪዎቹን ሁለት ግቦችም ማመቻቸት ችሏል።

ሄኖክ አየለ – ድሬዳዋ ከተማ

በብርቱካናማዎቹ ማንሰራራት ውስጥ የቡድኑን የፊት መስመር በአግባቡ በመምራት ላይ የሚገኘው ሄኖክ አየለ ሀዲያ ሆሳዕና ላይ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር ለቡድኑ ድል ቀጥተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል። በወሳኝ ጊዜ እና ቦታ ሳጥን ውስጥ ይገኝ የነበረው አጥቂው የተረጋጋ የአጨራረስ መንገዱ ያገኛቸውን ዕድሎች እንዲጠቀም አድርጎት ተመልክተናል።

አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ – ድሬዳዋ ከተማ

ለሳምንቱ ምርጥነት ከአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ጋር የተፎካከሩት አሰልጣኝ ሳምሶን በመጨረሻም በአብላጫ ድምፅ ተመራጭ ሆነዋል። ወደ ምስራቁ ክለብ ከደረሱበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ዕቅዶችን እየተገበሩ የቆዩት አሰልጣኝ ሳምሶን አሁን ላይ ቡድናቸውን ወደሚፈልጉት መንገድ እየወሰዱት ይመስላል። ፈጣን ጥቃት ላይ የተመሰረተ እና በጥሩ መከላከል ጭምር የታገዘ የነበረው የዚህ ሳምንት ስትራቴጂያቸው ሀዲያ ሆሳዕና ላይ ተደጋጋሚ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲያስችላቸው ጨዋታውንም በሰፊ ልዩነት አሸንፈዋል።

ተጠባባቂዎች

ቢኒያም ገነቱ – ወላይታ ድቻ
አሌክስ ተሰማ – መከላከያ
እንየው ካሳሁን – ድሬዳዋ ከተማ
አብነት ደምሴ – ኢትዮጵያ ቡና
አዲሱ አቱላ – መከላከያ
ሱራፌል ዳኛቸው – ፋሲል ከነማ
ጌታነህ ከበደ – ወልቂጤ ከተማ
ብሩክ በየነ – ሀዋሳ ከተማ