የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ተካሂዷል

ከረፋድ አንስቶ ካዛንቺስ በሚገኘው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ ሲካሄድ የዋለው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ከሰዓታት በፊት ተጠናቋል።

ይጀመራል ከተባለበት ጊዜ በተወሰነ ደቂቃ ዘግይቶ የጀመረው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤው በዋና ፀሀፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን አማካኝነት ምልዓተ ገለባኤው መሞላቱ መረጋጠጉን ተከትሎ የፊደሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ መድረኩን ተረክበዋል።

ፕሬዘዳንቱ በመክፈቻ ንግግራቸው ይህ ጉባኤ መጋቢት ወር ላይ ለማድረግ ታቅዶ የነበረ መሆኑን እና በተለያየ ምክንያት መዘግይቱን ገልፀው በዛሬው ጉባኤ የመተዳደርያ ደንቦች ለማሻሻል ከፊፋ ከመጣች ባለሙያ ጋር በጋራ በመሆን ሰፊ ጊዜ በመውሰድ የተዋቀረው የጥናት ኮሚቴ የተለያዩ ሦስት ሰነዶች የተዘጋጁ ስለመሆናቸው ጠቅሰው በዚህም ከጉባኤው በፊት በባለድርሻ አካላት እንዲዳብር ስለመደረጉም አንስተዋል። በዋነኝነት በንግግራቸው ያነሱት ሀሳብ ከፊፋ በቀረበው ሀሳብ መሰረት የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ቁጥር በዝቷል የሚል ሀሳብ የቀረበ ሲሆን ይህንምም ለማሻሻል ሁለት አማራጮች ስለመቅረባቸውም እንዲሁ አንስተዋል።

በመቀጠል ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት ደግሞ የኢፌዲሪ የባህል እና ስፖርት ሚንስቴር ሚንስትር የተከበሩ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ነበሩ ፤ እሳቸውም በንግግራቸው ጅማሮ ለጠቅላላ ጉባኤ መብቃት በራሱ ብዙ ውጣ ውረዶች ያሉት እንደመሆኑ “ለዚህ በመብቃታችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ” በማለት ንግግራቸውን የጀመሩ ሲሆን በዋነኝነትም በሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በአዲስ መልክ በተዘጋጀው የስፖርት ማህበራት ማቋቋሚያ አዋጅ መነሻነት ትኩረት ሊሰጥባቸው ይገባሉ ባሏቸው አንኳር ጉዳዮች ላይ ሀሳብ ሰጥተዋል።

ጉባኤው ከንግግራቸው በኋላ ሲቀጥልም ሁለት ድምፅ የሚቆጥሩ እንዲሁም ሦስት ቃለ ጉባኤ የሚይዙ አባላትን በመሰየም ቀጥሎ በዋና ፀሀፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን የቀረቡት የጉባኤው አጀንዳዎች በአባላት እንዲፀድቁ ተደርጓል።

በመቀጠልም የመጀመሪያ አጀንዳ የነበረው የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ አመራር ረቂቅ ደንብ በህግ ባለሙያው አቶ ኃይሉ ሞላ በአጭሩ ከቀረበ ወዲህ በጉባኤው አባላት ሀሳቦች ተሰንዝረውበታል። በተለይም አንቀፅ ሦስት ላይ የሰብሳቢው ሥልጣን በሚነደነግገው አዋጅ ላይ ክርክሮችን የሚያውክን አባል ንግግር ማስቆም እና መገሰፅ ባለፈ ከጠቅላላ ጉባኤው ማሰናበት ይችላል የሚለው ጉዳይ ብዙ ያነጋገረ ነበር። በተጨማሪም አንቀፅ ስምንት ላይ ለጠቅላላ ጉባኤ የሚቀርቡ ሀሳቦች በፅሁፍ መቅረብ ብቻ ይኖርባቸዋል የሚለው ጉዳይ ላይ በጉባኤተኞች በቃልም መቅረብ ይኖርባቸዋል በሚል የተሰጠው አስተያየት ተካቶበት በመጨረሻም በሙሉ ድምፅ እንዲፀድቅ ተደርጓል።

በመቀጠል ለጉባኤተኛው የቀረበው ሌላኛው ሰነድ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ረቂቅ መተዳደርያ ደንብ ነበር። በተመሳሳይ በአቶ ኃይሉ ሞላ ያቀረቡት ረቂቅ ሰነድ ላይ በቅድሚያ ፊፋ በ2015 ያጋጠመውን ውጥንቅጥ ለመፍታት ያዘጋጀውን የሪፎርም ሰነድ እና በ2020 አስጠንቶ ተግባራዊ ባደረገው አዲሱ አስተዳደራዊ መዋቅር ላይ ሰፊ ገለፃን ሰጥተዋል።

ቀጥለውም የፊፋን አዲሱን መተዳደርያ መነሻ በማድረግ አዲሱን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ረቂቅ መተዳደርሪያ ላይ በአንቀፅ 29 የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ድምፅ እና ውክልና ለመወሰን ሁለት አማራጭ ሀሳቦችን አቅርበዋል ፤ በዚህም የድምፅ አወሳሰናቸው የተለያዩ የሆኑ ሁለት 74 እና 79 አባላት ያላቸው አማራጮች የቀረቡ ሲሆን ከዚህ ባለፈም ለፕሬዝዳንትነት እጩ ሆኖ ለመቅረብ ከዚህ ቀደም ከነበረው መመሪያ ላይ በተለየ በህግ ኢትዮጵያዊ የሆነ ወይንም የኢትዮጵያ ተወላጅነት መታወቂያ ካርድ ያለው እና ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር የሚል እና ዕድሜ ላይ ከ21 ዓመት እስከ 74 ዓመት በሚል የተሻሻሉ ዝርዝር ሀሳቦችም እንዲሁ በሰነዱ ላይ ቀርበዋል።

በተጨማሪነትም ከዚህ ቀደም ከነበረው አሰራር በተለየ ተቋማዊ ገለልተኝነት ላይ ትኩረት ያደረጉ አዳዲስ ኮሚቴዎችም እንዲሁ እንደሚዋቀሩ ተጠቅሷል። በዚህም አዲስ የፍትህ አካል የሆነው ስነ ምግባር ኮሚቴ እንዲዋቀር የሚጠይቅ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም የአስተዳደር እና የምርመራ ኮሚቴ እና የግልግል ዳኝነት ላይ የሚሰራ አካልም እንዲቋቋም ረቂቅ ደንቡ ያትታል።

ሌላው በረቂቅ ደንቡ የቀረበው ትኩረት የሳበው ሃሳብ የሂሳብ ሪፖርቶችን ጨምሮ ሌሎች የፕሬዝዳንቱ ፣ የስራ አስፈፃሚ አባላት ፣ ዋና ፀሀፊ እና ገለልተኛ ኮሚቴዎችን ጨምሮ የሚፈፀሙላቸው ክፍያዎች በፌደሬሽኑ ድረ ገፅ በኩል ይፋ መደረግ አለበት የሚለም ጉዳይ ይገኝበታል።

ከሰነዱ በኋላ ለሻይ ዕረፍት የተበተነው ጉባኤው ከሻይ እረፍት ሲመለስ ከጉባኤው በፊት ለተሳታፊዎች በተበነው ሰነድ ላይ ከ3 ክለቦች እና ከ3 ማህበራት በቀረበ ግብረ መልስ ላይ ሀሳቦችን የህግ ባለሙያው አቶ ኃይሉ ሞላ አንስተዋል። በተለይም ከፕሪምየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር ከትርጓሚ አንፃር ያነሳቸው ሀሳቦች ላይ ማሻሻያ ስለመደረጉ ገልፀዋል።

በመቀጠል በሰነዶች ላይ ከተሳታፊዎች ሀሳብ የተሰነዘረ ሲሆን በቅድሚያም የባህል እና ስፖርት ሚንስትሩ በረቂቁ ላይ በቀረበው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በፕሬዝዳንትነት መወዳደር ይችላሉ የሚለው ጉዳይ ከብሔራዊ ጥቅም አንፃር ሌሎች መመሪያዎችን በማጣቀስ ይህን ጉዳይ ከሀገሪቱ ህግ አንፃር የሚጣረስ በመሆኑ ቢታይ የሚል ሀሳብ አንስተዋል።

በማስከትል ረጅም ደቂቃዎችን በፈጀ ሂደት በርከት ያሉ ሀሳቦች ተነስተዋል ፤ ከተነሱት ሀሳቦች መካከል አንኳሮቹ ፤

– ፊፋ ምክረ ሀሳብ የማቅረብ እንጂ እንደዚህ አድርጉ ብሎ የማስገደድ መብት የለውም ይህን ማድረግ የሚችለው ጠቅላላ ጉባኤ ነው።

– ጠቅላላ ጉባኤ አባላት ድምፅ እና ውክልና ላይ የቀረቡት ሁለት አማራጮች ላይ ቁጥርን ለመቀነስ ብቻ ሲባል የአንደኛ ሊግ ክለቦች እና የሴቶች ውድድሮች ላይ የሚካፈሉ ቡድኖችን ድምፅ እንዳይኖራቸው መደረጉ ተገቢ አይደለም

– ከፊፋ የማሻሻያ ሰነድ ባለፈ በአፍሪካ በእግርኳስ የተሻሉ የሚባሉት ሀገራት ተሞክሮ መቀመር ነበረበት

– ለእግር ኳስ አስተዳደር የዕድሜ ገደብ መቀመጡ ተገቢ አይደለም። ከተጠቀሰው እድሜ ያለፉ ሰዎችም ማገልገል እስከቻሉ ክፍት ሊደረግላቸው ይገባል

– ሁሉም ክልሎች ዕኩል ድምፅ ሊኖራቸው ይገባል ፤ ማህበራት እና ክልሎች ላይ የሚሰጡት ድምፅ ኮታ መሻሻል ይገባዋል

– በነበረው ደንብ ተመርተን መጪውን ምርጫ ካደረገን በኋላ በቀጣይ የሚመረጠው ስራ አስፈፃሚ ይህን ሰነድ እንደመነሻ በመውሰድ ጊዜ ተወስዶ ይበልጥ ሊዳብር ይገባል።

ከጉባኤው ለተነሱ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ የሰጡት የፊደሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ በንግግራቸው የፊፋ አባል ሀገራት መብት እና ግዴታን በጣሰ መልኩ ፊፋ እግርኳሳችን ላይ አይመለከተውም የሚለው ሀሳብ ፍፁም የተሳሳተ ስለመሆኑ አንስተዋል።

ሌላኛው ምላሽ የሰጡበት ጉዳይ ብዙ ሲያነጋግር በነበረው እና ከአሳታፊነት አንፃር የቀረቡት ሁለት የጠቅላላ ጉባኤውን አባላት ብዛት በሚወስኑት እና በአንቀፅ 29 ስለተቀመጡት አማራጮች ነበር። በንግግራቸውም እነዚህ አማራጮች ከምን አግባብ እንደረቀቡ አስረድተው መነሻ እንደመሆናቸው ሊሻሻሉ የሚችሉ ስለመሆናቸው አስረድተዋል።

እነዚህ አማራጮች ከመቅረባቸው በፊት ሀሳብ እንዲቀርብ በተላከው ሰነድ ላይ አማራጭ በጉባኤተኛው ባልቀረበበት ሁኔታ ተጠንቶ የቀረበውን ረቂቅ ማጣጣሉ ተገቢ አለመሆኑን አንስተዋል።

የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ክለቦች የጠቅላላ ጉባኤ ተሳትፎን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ አብዛኞቹ የወንድ ክለቦች በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ስላላቸው በሚል የቀረበ ሀሳብ ነው መሻሻል አለበት ከተባለ ይህ ረቂቅ ስለሆነ መሻሻል የሚችልም ነው ብለዋል።

በመቀጠል መድረኩን የተቀበሉት የህግ ባለሙያው አቶ ኃይሉ ሞላ ከህግ አንፃር ምላሽ በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማስከተል በፕሬዚዳንቱ መሪነት ወደ ድምፅ መስጠት ሂደት የተገባ ሲሆን በዚህም ብዙ ሲያከራክር የዋለው የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ድምፅ እና ውክልና ለመወሰን የቀረበው ረቂቅ (አንቀፅ 29) በ92 አባላት ተቃውሞ ከረቂቁ ለጊዜው እንዲወጣ የተደረገ ሲሆን ከዚህ አንቀፅ ውጪ የቀረቡት የረቂቁ ክፍሎች በጉባኤው ከቀረቡት ማሻሻያ ሀሳቦች ጋር የ103 አባላት ድጋፍን በማግኘት ፀድቋል።

በመቀጠል በህግ ባለሙያ አቶ ኃይሉ የቀረበው የተሻሻለው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን የፕሬዝዳንትና የሦራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ማስፈፀሚያ ደንብ አጭሩ የቀረበ ሲሆን ይህም ደንብ መጠነኛ ሀሳቦች ከተሰጡበት ወዲህ በ113 ድምፅ ፀድቋል።

አስከትሎም የምርጫ አስፈፃሚ እና የይግባኝ ሰሚ አባላት መነሻ የሚሆኑ ዕጩዎች ከመድረክ የቀረቡ ሲሆን በተሳታፊዎች ተጨማሪ ጥቆማዎች ቀርበው ድምፅ እንዲሰጥባቸው የተደረገ ሲሆን በዚህም መሰረት

በምርጫ አስፈፃሚነት

1- ረሂማ አወል
2- ኃይሉ ሞላ
3- መንግሥቱ መሐሩ
4- ኢሳያስ ደንድር
5- በለጠ ዘውዴ የተመረጡ ሲሆን አቶ አበባው ሰለሞን እና ኢብራሂም አደም በተጠባባቂነት እንዲያዙ ተደርጓል።

 

በይግባኝ ሰሚ ኮሚቴነት ደግሞ

1- አንበሳው እንየው
2- ተስፋዬ ዘወዴ
3- ብርሃኑ ከበደ ሲመረጡ በተጠባባቂነት ደግሞ መኮንን ጤናው እና አፈወርቅ አየለ ተመርጠዋል።

የጉባኤው ማሳረጊያ በነበረው ንግግራቸው ፕሬዚደንት ኢሳይያስ ጂራ በሀሳብ ልዕልና የተመራ ባሉት ጉባኤ በእግርኳሳችን ውስጥ ያለው እኛ እና እነሱ የሚለውን ሀሳብ በመቀየር ረገድ የሚቀሩ ነገሮች ቢኖሩም በምሳሌነት የሚቀርብ ጉባኤ በመሆኑ ለጉባኤተኞች ምስጋና አቀርባለው ብለዋል።

አያይዘውም ስለ ሰሞነኛው የስታዲየሞቻችን ውድቅ የመደረግ ጉዳይ ሃሳባቸውን የሰጡት አቶ ኢሳያስ ሰሞነኛውን ጉዳይን ሁላችንም እንደ ቁጭት በመውሰድ እዚህ ጉባኤ ላይ የተሳተፋችሁ የክልል የስፖርት አመራሮች በመንግስት ደረጃ በሚኖራችሁ ስብሰባ ይህን ሀሳብ በአፅንኦት አንስታችሁ የተጀመሩትን ስታዲየሞች እንዲጠናቀቁ ግፊት እንዲያሳድሩ አደራ ሰጥተዋል።

በመጨረሻም በሀገሪቱ በተለያዩ ክፍሎች ሰው ሰራሽ በሆኑ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ክለቦች እና አጠቃላይ የስፖርት ቤተሰቡ በመረባረብ ወደ ቀደመ ህይተወታቸው ልንመልሳቸው ይገባል በሚል ባስተላለፉት ጉባኤው ፍፃሜውን አግኝቷል።

ያጋሩ