ቅድመ ዳሰሳ | የ24ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

የ24ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ነገ ሲጀምሩ በዕለቱ የሚደረጉ ሁለት ፍልሚያዎችን እንደሚከተለው ዳሰናቸዋል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ኢትዮጵያ ቡና

የደረጃ ሰንጠረዡን አካፋይ ቦታ ይዞ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ አልቻለም። በተለይ ባሳለፍነው ሳምንት በወራጅ ቀጠናው አፋፋ ላይ በነበረው ድሬዳዋ ከተማ ያስተናገደው የአራት ለምንም ሽንፈት አስደንጋጭ ነበር። ከዚህ መጥፎ ወቅታዊ ውጤት ለመውጣት ደግሞ ነገ ጠንክሮ ወደ ሜዳ በመግባት ነጥቡን ሠላሳዎቹ ውስጥ ለማስገባት እንደሚጥር ይታመናል። በተቃራኒው ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ ከሁለት ጨዋታዎች ያለማሸነፍ ጉዞ በኋላ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን ረቷል። የሳምንቱን የመክፈቻ ጨዋታ በማሸነፍ ደግሞ ከረጅም ጊዜ በኋላ በሊጉ በጊዜያዊነትም ቢሆን ሦስተኛ ደረጃን ለመያዝ እንደሚታትር ይጠበቃል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ባሳለፍነው ሳምንት ሲጫወት በዘንድሮ የውድድር ዓመት መጥፎ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እና ውጤት ያስመዘገበበት ፍልሚያ ሆኖ አልፏል። ኳስን ተቆጣጥሮ ከመጫወት ውጪ በብዙ መስፈርቶች በድሬዳዋ ተበልጦ የነበረው ቡድኑ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ ከነበረበት መዳከም ነገ ተሻሽሎ መቅረብ ይገባዋል። በዋናነት በፍላጎት በመጫወት ረገድ ክፍተት የነበረበት ቡድኑ ለወትሮ ግብ ሲቆጠርበት ወዲያው ምላሽ ለመስጠት የሚሄድበት መንገድ ጠፍቶት ተስተውሏል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች የታየው የቡድኑ የወረደ የመከላከል አጨዋወት ደግሞ ይበልጥ ላልቶ መምጣቱ ዋጋ እንዲከፍል አድርጎታል። በዚህ ሂደት ከወገብ በታች ወሳኝ ተጫዋች የሆኑት ተስፋዬ አለባቸው እና ግርማ በቀለ አለመኖራቸው ደግሞ ትልቁ እጦት እንደነበረ በጉልህ ታይቷል። በነገው ጨዋታ ሁለቱ ተጫዋቾች ከቅጣት መልስ ቡድናቸውን ስለሚያገለግሉ የተሸነቆረ የሚመስለው የኋላ መስመር በመጠኑ የሚጠገን ይመስላል። የኋላው መስመር ከተስተካከለ ደግሞ ለማጥቃት የማይቦዝኑት የወገብ በላይ ተጫዋቾች ነፃነት ስለሚያገኙ ከድሬው በበለጠ ጫና ለማሳደር እንደሚጥሩ ይጠበቃል።

ባህር ዳር ላይ ሁለቱንም ጨዋታቸውን ካሸነፉ ሦስት ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ኢትዮጵያ ቡና በጥሩ መነቃቃት ላይ ያለ ይመስላል። በተለይ ሁለቱን ጨዋታዎች ያሸነፈበት መንገድ ቡድኑ ዕድገት ላይ እንደሆነ የሚያመላክት ነው። በዚህም በድሬዳዋውም ሆነ በወልቂጤው ጨዋታ የተመዘገቡት ድሎች ከመመራት ተነስተው የተገኙ ናቸው። ይህ ትልቅ አዕምሮዋዊ እድገት መኖሩን የሚያሳይ እና ተስፋ ሳይቆርጡ በጨዋታ መቆየት መቻል የሚደነቅ ነገር ቢሆንም ሁሌ ሊሳካ የማይችል ነገር ስለሆነ ግን ቀድሞ ግብ የሚቆጠርበትን ሂደት ማስተካከል ይኖርበታል። ከዚህ ውጪ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ብቻ ዘጠኝ ግቦችን ማስተናገዱም ሲታወስ እንደ ተጋጣሚው ሀዲያ የኋላ መስመሩ መሻሻል እንዳለበት ያመላክታል። በተለይ የአቋቋም እና የቦታ አጠባበቅ ስህተቶች ለረጅም ጊዜያት ሲስተዋሉ የነበሩ ክፍተቶች ናቸው። ቡና እንደ ሁል ጊዜው ኳሱን ተቆጣጥሮ ለመጫወት እንደሚጥር ሲጠበቅ ሀዲያ ሆሳዕና በጨዋታው በቁጥር አብዝቶ አማካይ መስመር ላይ ሊያሰልፍ የሚችላቸውን ተጫዋቾች በልጦ መገኘት ግን ወሳኝ ነው። የባህር ዳር ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳ ወደ ጎን ሰፋ ያለ ስለሆነ ደግሞ በቁጥር በዛ ያሉትን ተጫዋቾች ጨዋታውን ወደ ሁለቱ መስመሮች በመለጠጥ ለመዘርዘር እንደሚሞክር ይታሰባል። በዚህ የመስመር አጨዋወት ደግሞ በወልቂጤው ጨዋታ ጠንካራ ጎን የነበረው የግራ መስመር ነገም የቡድኑ የግብ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ቀድሞ መናገር ይቻላል።

በሀዲያ ሆሳዕና ቤት ግብ ጠባቂው ሶሆሆ ሜንሳ ከረጅም ጊዜ ጉዳት፣ግርማ በቀለ እና ተስፋዬ አለባቸው ደግሞ የአምስት ቢጫ ቅጣታቸውን ጨርሰው ለነገው ጨዋታ የሚመለሱ ሲሆን ዑመድ ኡኩሪ በአምስት ቢጫ አይሰለፍም። ከዚህ ውጪ ኤልያስ አታሮ እና አንበሉ ሄኖክ አርፊጮ ህመም ላይ የሚገኙ ቢሆኑም ለነገ ጨዋታ እንደሚደርሱ ሰምተናል። ኢትዮጵያ ቡና በቅጣት የሚያጣው ተጫዋች ባይኖርም በጉዳት ምክንያት የወንድሜነህ ደረጀ፣ ሚኪያስ መኮንን እና ቴዎድሮስ በቀለ አገልግሎት አያገኝም።

ጨዋታው በሚካኤል ጣዕመ የመሐል ማንደፍሮ አበበ እና ሸዋንግዛው ይልማ ረዳት፣ እያሱ ፈንቴ አራተኛ ዳኝነት እንዲሁም ሰለሞን ተስፋዬ እና ኤፍሬም ኃይለማርያም የጎል አጠገብ ረዳትነት የሚከወን ይሆናል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– በሁለቱ ቡድኖች የቀደመ አምስት ግንኙነት ኢትዮጵያ ቡና 3 ሀዲያ ሆሳዕና 1 ሲያሸንፉ አንዱን አቻ ተለያይተዋል። ከተቆጠሩት አስር ጎሎች ደግሞ ሀዲያ 4 ቡና 6ቱን በስማቸው አስመዝግበዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ


ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2)

ሶሆሆ ሜንሳ

ግርማ በቀለ – ፍሬዘር ካሣ – ሔኖክ አርፌጮ

ብርሃኑ በቀለ – አበባየሁ ዮሐንስ – ተስፋዬ አለባቸው – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን – ኢያሱ ታምሩ

ባዬ ገዛኸኝ – ሀብታሙ ታደሠ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

አቤል ማሞ

ኃይሌ ገብረትንሳይ – አበበ ጥላሁን – ገዛኸኝ ደሳለኝ – ያብቃል ፈረጃ

አማኑኤል ዮሐንስ – አብነት ደምሴ – ታፈሠ ሰለሞን

ዊሊያም ሰለሞን – አቡበከር ናስር – አስራት ቱንጆ

ጅማ አባ ጅፋር ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በ32 ነጥቦች ተራርቀው በደረጃ ሰንጠረዡ አናት እና ግርጌ የሚገኙት ጅማ አባ ጅፋር እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ በተቃራኒ አቅጣጫ እየተጓዙ ቢሆንም በየመንገዳቸው የነገው ሦስት ነጥብ ያስፈልጋቸዋል። በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ እየዳከረ የሚገኘው ጅማ በምክትል አሠልጣኙ የሱፍ ዓሊ እየተመራ ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን ቢያሸንፍም ባሳለፍነው ሳምንት በሌላኛው ላለመውረድ በሚጥረው ሰበታ ከተማ ሽንፈት አስተናግዷል። በሊጉ ለመክረም ከፍተኛ ብርታት የሚጠበቅበት ቡድኑ ነገ ደግሞ በቶሎ ከሽንፈቱ እንዲያገግም የሚያደርገው ቀላል ቡድን አለመግጠሙ ፈተናውን ያጠናበታል። እስካሁን አንድም ሽንፈት ያላስተናገደው የሊጉ መሪ ጊዮርጊስ ወደ ዋንጫ የሚያደርገውን ጉዞ ቢቀጥልም ባሳለፍነው ሳምንት በወላይታ ድቻ ነጥብ ጥሏል። በጨዋታ ሳምንቱ ተከታዩ ፋሲል ቢያሸንፍም ግን የነጥብ ልዩነቱ ስምንት በመሆኑ እምብዛም ጫና ውስጥ እንዲገባ እንደማያደርገው ይታመናል። ነገም በታችኛው ደረጃ የሚገኘውን ክለብ አሸንፎ ዳግም የነጥብ ልዩነቱን ለማስፋት ይጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ብዙም የሚታማ ነገር የሌለው ጅማ አባ ጅፋር ውጤት የመያዝ ችግሩ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲገኝ አድርጎታል። በተለይ በሁለቱ ወሳኝ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ስል እና ጠንካራ አለመሆኑ ትልቁ ችግሩ ይመስላል። በዋናነት ደግሞ ግብ ፊት ያለው አይናፋርነት ዋጋ ሲያስከፍለው ቆይቷል። በባህር ዳሩ እና አርባ ምንጩ ጨዋታ ብቻ በድምሩ 38 ሙከራዎችን ያደረገው ቡድኑ በንፅፅር ቀለል ያለውን ሰበታ ከተማ ሲገጥም ከ12 ያልበለጡ ሙከራዎችን ብቻ ነበር ያደረገው። ይህም ሆኖ ቀድሞ ግብ ቢያስቆጥርም ያንን ጎል ማስጠበቅ ተስኖት ወሳኙን ጨዋታ አጥቷል። በተለይ ከመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ውጪ በተነሳሽነቱ ረገድ ደካማ የነበረው ቡድኑ ነገም በተመሳሳይ አቀራረብ ወደ ሜዳ ከገባ እጅ መስጠቱ አይቀሬ ነው። ምናልባት በቅዱስ ጊዮርጊስ ካለው የተጫዋች እና የቡድን ጥራት መነሻነት የጨዋታው ግለት መቆጣጠር ሊከብዳቸው እንደሚችል ቢጠበቅም ፈጣኖቹን አጥቂዎቻቸውን ያማከለ የመልሶ ማጥቃት እየተከተሉ ከጨዋታው አንዳች ነገር ይዞ ለመውጣት እንደሚጥሩ ይታሰባል። ለዚህ ደግሞ ከፍ ብሎ የሚከላከለው የጊዮርጊስ የኋላ መስመር ጀርባ መስዑድ እና ዳዊት ኳሶችን እየላኩ አደጋ እንዲፈጠር ሊያደርጉ ይችላሉ።

ዘንድሮ በብዙ መመዘኛዎች የተሟላ ቡድን የሆነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሳይሸነፍ ሊጉን ለማገባደድ እየተጋ ይገኛል። ከሳምንት ሳምንት ለዋንጫው እየቀረበ የመጣው ቡድኑ እንዳልነው እስካሁን ባይሸነፍም ባሳለፍነው ሳምንት በወላይታ ድቻ ነጥብ ጥሏል። እርግጥ በጨዋታው በእንቅስቃሴ ረገድ መጥፎ ባይሆንም ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ግን ሲቸገር ነበር። ጠጣሩን የድቻ የኋላ መስመር በተደጋጋሚ ቢጎበኝም መረቡን ሳያገኝ ወጥቷል። ይህ የአቻ ውጤት ቡድኑን በቀጣይ ጨዋታዎች ጫና ውስጥ እንዲገባ ባያደርጉትም ቀጣይ ጨዋታዎችን ኮስተር ብሎ እንዲቀርብ ምልክት የሚሰጠው ይመስላል። በተወሰነ መልኩም በአንዳንድ ቦታዎች የተደረጉት የመጀመሪያ አሰላለፍ የተጫዋች ለውጦች ፍሬያማ አለመሆናቸው በድቻው እንዲሁም በአዳማው ጨዋታ ፍንጭ ስለታየ ቀጣዮቹ ፍልሚያዎች ትምህርት ተወስዶባቸው የሚገባባቸው ናቸው። ጊዮርጊስ በድቻው ጨዋታ በመልሶ ማጥቃቶች ሲጋለጥ ሲስተዋል ነበር። የነገው ተጋጣሚ ጅማም ለመልሶ ማጥቃቶች ራሱን አዘጋጅቶ ሊገባ ስለሚችል የመከላከል አደረጃጀቱን ማሳደግ ይገባዋል። ከዚህ ውጪ ተለምዷዊው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ጫና ነገም እንደሚተገበር ይታመናል። ጅማ የመከላከል አደረጃጀት ስህተት የሚያበዛ ቡድን ስለሆነም ስራቸው እምብዛም ላይጠና ይችላል። ፈጣኖቹ አማኒኤል፣ አቤል እና ቸርነት የሚዋልል አጨዋወት ደግሞ ለተከላካዮቹ ከባድ ፈተናን የሚሰጥ ይሆናል።

በጅማ በኩል አድናን ረሻድ በጉዳት ሽመልስ ተገኝ ደግሞ በግል ጉዳይ የማይገኙ ሲሆን ከጉዳቱ የተመለሰው እዮብ አለማየሁም መግባቱ አጠራጣሪ እንደሆነ ተጠቁሟል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ነገም የእስማኤል ኦሮ-አጎሮን ግልጋሎት የሚያጣ ሲሆን በተቃራኒው አቤል ያለው ግን ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑ መነገሩ ለቡድኑ መልካም ዜና ነው። ባሳለፍነው ሳምንት ጉዳት አስተናግዶ የወጣው ከነዓን ማርክነህ በበኩሉ ልምምድ እየሰራ ቢገኝም መሰለፉ እርግጥ አልሆነም።

ጨዋታውን ተከተል ተሾመ በመሐል አልቢትርነት ፍሬዝጊ ተስፋዬ እና አያሌው አሰፋ የመስመር ረዳት እንዲሁም ዮናስ ማርቆስ አራተኛ ዳኛ ሆነው ሲመሩ ካሣሁን ፍፁም እና አብዱ ይጥና ደግሞ የጎል አጠገብ ረዳቶች እንደሆኑ ታውቋል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ጅማ አባ ጅፋር ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ 7 ጊዜ ተገናኝተው ጊዮርጊስ በ4 ድል ቀዳሚ ሲሆን ጅማ 1 አሸንፏል። በሁለቱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። ጊዮርጊስ 11 ሲያስቆጥር ጅማ 5 አስቆጥሯል

ግምታዊ አሰላለፍ


ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)

አላዛር ማርቆስ

ወንድማገኝ ማርቆስ – ኢያሱ ለገሠ – የአብስራ ተስፋዬ – ተስፋዬ መላኩ

መስዑድ መሐመድ – አስጨናቂ ፀጋዬ – ዳዊት እስቲፋኖስ

ዱላ ሙላቱ – መሐመድኑር ናስር – ሱራፌል ዐወል

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ቻርለስ ሉኩዋጎ

ሱሌይማን ሀሚድ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሄኖክ አዱኛ

ሀይደር ሸረፋ – ጋቶች ፓኖም

አቤል ያለው – የአብስራ ተስፋዬ – ቸርነት ጉግሳ

አማኑኤል ገብረሚካኤል