የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ ተራዘመ

በዩጋንዳ አስተናጋጅነት የሚዘጋጀው የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ የቀን ማሻሻያ ተደርጎበታል፡፡

ሉሲዎቹን ተሳታፊ የሚያደርገው የዘንድሮው የሴካፋ የሴቶች ዋንጫ በዩጋንዳ አስተናጋጅነት እንደሚደረግ ይጠበቃል፡፡

አስቀድሞ የውድድሩ የበላይ አካል ሴካፋ ከግንቦት 14 እስከ 28 ድረስ በሁለት ምድብ ተከፍሎ በስምንት ሀገራት መካከል እንደሚደረግ ገልፆ የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያን ጨምሮ ተጨማሪ ሁለት ሀገራት ውድድሩ እንዲራዘም ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት በማግኘቱ የቀን ማሻሻያ ሊደረግበት ችሏል፡፡

በዚህም መሠረት ውድድሩ ከግንቦት 24 እስከ ሰኔ 4 ድረስ እንዲከወን የመጨረሻ ቀን ተቆርጦለታል፡፡ በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያ በምድብ ሁለት ከታንዛኒያ ፣ ዛንዚባር እና ደቡብ ሱዳን መደልደሏ ይታወሳል፡፡ የምድብ ጨዋታዎቿን የምታከናውንባቸው ቀናትም የሚከታሉት ናቸው :-

ሐሙስ ግንቦት 25 ከ ዛንዚባር

ቅዳሜ ግንቦት 27 ከ ታንዛኒያ

ሰኞ ግንቦት 29 ከ ደቡብ ሱዳን