ሊጠናቀቅ አንድ ሳምንት የቀረው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ በአሰላ እና በባቱ ከተማ መካሄዳቸውን ቀጥለው የተለያዩ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በአሰላ ከተማ መካሄድ የነበረበት የኢትዮጵያ መድን እና የወላይታ ቱሳ ጨዋታ ወላይታ ቱሳ በፋይናስ ችግር ምክንያት ውድድሩን በማቋረጡ ኢትዮጵያ መድን ሦስት ነጥብ እና ሦስት ንፁሁ ጎል ማግኘት ችሏል።
በመቀጠል የተደረገው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ በኢትዮጵያ ቡና እና በአዲስ አበባ ከተማ መካከል ተካሂዶ በቡናማዎቹ 2–0 አሸነፊነት ተጠናቋል።
በሁለቱ ቡድኖች የነጥብ መቀራረብ እና በሚመዘገበው ውጤት የደረጃ ለውጥ የሚያመጣ በመሆኑ ጠንካራ ፉክክር እንደሚኖር ተጠብቆ የነበረው ጨዋታ እንደተጠበቀውም ዕረፍት አልባ ጥሩ እንቅስቃሴ አስመልክቶናል። ወደ ፊት በመድረስ ለጎል የቀረበ ሙከራ በማድረግ ኢትዮጵያ ቡናዎች ቀዳሚ ነበሩ። ከዚህ ውስጥ ከግራ ጠርዝ አስራ ስድስት ከሀምሳ መስመር ላይ የተሰጠውን ቅጣት ምት ሀቢብ ዛኪር የመታውና ለጥቂት የግቡን አግዳሚ ታኮ የወጣው የሚጠቀስ ነው።
ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ኳስን ከራሳቸው ሜዳ መስርተው በመውጣት በክፍት ሜዳ ጎል ለማግኘት የሚያደርጉት ፉክክር ተመልካቹን እያዝናና ቀጥሎ የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ዳግም ባህሩ ከኳስ ውጪ የአዲስ አበባውን አጥቂ በዋይ ኮዋችን በክርን መማታቱ የጨዋታውን ወደ ኃይል አጨዋወት ቀይሮታል። በቅርብ ርቀት የነበሩት የዕለቱ ዳኛ ውሳኔ አለማሳለፋቸውም ብዙዎችን አስገርሟል።
36ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ቡናዎች በልማደኛው አጥቂ አማካኝነት መሪ መሆን የቻሉበትን ጎል አግኝተዋል። ከመሀል ሜዳ በጥሩ ቅብብል አማኑኤል አድማሱ የሰጠውን ሰንጣቂ ኳስ ከተከላካዮች መሀል አፈትልኮ በመውጣት በጥሩ አጨራረስ ተስፈኛው አጥቂ ከድር ዓሊ ለቡድኑ የመጀመርያ ለራሱ የውድድር ዓመቱን 11ኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል።
በቀጣይ ደቂቃዎች የጨዋታው እንቅስቃሴ እየተቆራረጠ ወደ መቀዛቀዝ ቢያመራም አዲስ አበባዎች በአጥቂያቸው በዋይ ኮዋች አማካኝነት ግልፅ የጎል አጋጣሚ አግኝተው አልተጠቀሙበትም። በመልሶ ማጥቃት በፈጣን አንቅስቃሴ የማጥቃት ሽግግር የሚያደርጉት ኢትዮጵያ ቡናዎች ሁለተኛ ጎላቸውን በ45+4ኛ ደቂቃ አግኝተዋል። በቀኝ መስመር ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን በፍጥነት ወደ ሳጥን በመግባት ከድር ዓሊ አመቻችቶ ያቀበለውን የአብስራ ተስፋዬ በቀላሉ ወደ ጎልነት ቀይሮት የቡድኑን የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጎታል።
የመጀመርያው አጋማሽ የነበረው ጥሩ ፉክክር በሁለተኛው አጋማሽ ቀዝቀዝ ብሎ የጎል ሙከራ ሳንመለከት ኢትዮጵያ ቡና ከዕረፍት በፊት በተቆጠሩ ሁለት ጎሎች አሸንፎ ሊወጣ ችሏል። በውጤቱም አዲስ አበባ ከተማ መሸነፉን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ አንድ ጨዋታ እየቀረው የምድብ ለ አሸናፊ መሆኑን ከወዲሁ እንዲያረጋግጥ ሲያስችለው ኢትዮጵያ ቡና ቀጣይ ተጋጣሚው ወላይታ ቱሳ ባለመኖሩ ምክንያት በፎርፌ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቅ ለአዳማው የደረጃ ጨዋታ ማለፉን አረጋግጧል።
ባቱ ላይ ከሰዓት የተካሄዱ ተጠባቂ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። አስቀድመው የተገናኙት ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አዳማ ከተማ ሦስት አቻ በሆነ ውጤት ጨዋታቸውን አጠናቀዋል። ለአዳማዎች ዮሴፍ ታረቀኝ ፣ ዮሐንስ ፋንታ እና ፉአድ ኢብራሂም ሲያስቆጥሩ ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ ሙከረም ረሽድ ፣ በረከት ብርሀኑ ሁለት ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።
ሌላኛው የአስር ሰዓት ተጠባቂ ጨዋታ የነበረው የወላይታ ድቻ ከሲዳማ ቡና ጨዋታ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት ሲጠናቀቅ ኬነዲ ከበደ እና ተመስገን ብርሀኑ ለወላይታ ድቻ ለሲዳማ ቡና ደግሞ ፍቅር ግዛቸው እና ዳመና ደምሴ አስቆጥረዋል።
ወላይታ ድቻ ምድቡን አንደኛ ሆኖ ማጠናቀቁ ሲረጋገጥ ሁለተኛ ሆኖ ለማጠናቀቅ ንግድ ባንክ እና በሀዲያ ሆሳዕና መካከል የሚካሄደው የመጨረሻ ጨዋታ የሚጠበቅ ይሆናል።