ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ የሚቀጥልባቸውን ሦስት ጨዋታዎች የተመለከተው ዳሰሳችንን እነሆ።
አዲስ አበባ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ
የነገው የጨዋታ ዕለት በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ከፍ ያለ ትርጉም ባለው ጨዋታ ይጀምራል። አሁን ላይ በወራጅ ዞኑ ውስጥ የሚገኘው አዲስ አበባ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ራሱን ከሽንፈት ቢያርቅም ከ8 በላይ ነጥቦችን አላሳካም። በመሆኑም በአራት ነጥቦች ብቻ የሚበልጠው የነገ ተጋጣሚውን ማሸነፍ በቀጣይ ሳምንታት ለመትረፍ በሚያደርገው ትንቅንቅ ውስጥ ትልቅ ፈይዳ ይኖረዋል። በኢትዮጵያ ቡና መሀል ላይ ሽንፈት ቢገጥማቸውም ሀዲያ ሆሳዕናን በሰፊ ግብ በማሸነፍ ወደ መልካም ወቅታዊ አቋማቸው የተመለሱት ድሬዎች የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻሉ ወደ ዘጠነኛ ደረጃ ከፍ ማለት የሚችሉ በመሆኑ ውጤቱን እጅግ አጥብቀው ይፈልጉታል።
አዲስ አበባ አሁንም ከህመሙ የተፈወሰ አይመስልም። ለስምንተኛ ጊዜ ቀድሞ መምራት በቻለበት የሀዋሳ ከተማ ጨዋታ ፍፁም ቅጣት ምት በማባከን ጭምር ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል። አሰልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው ከዚያ ጨዋታ መጀመር አስቀድሞ እና ከተጠናቀቀ በኋላ በአዲሱ ቡድናቸው ውስጥ በዋነኝነት ተጫዋቾችን የማነሳሳት ኃላፊነት እንደሚኖርባቸው ጠቅመዋል። ይህ የማነሳሳት ስራቸው ደግሞ በነገው ጨዋታ ይበልጥ አስፈላጊ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህም ባለፈ ግን ቡድኑ በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ባለው አፈፃፀም በኩል እርጋታን እንዲጨምር ማድረግ እና በቁጥር በርካታ የሆኑ ዕድሎችን የማባከን አባዜውን ማስተካከል ከአሰልጣኞቹ ተጠባቂ ነው። አዲስ አበባ አሁንም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች ይኑረው እንጂ በማቀበል እና ወደ ግብ በመሞከር ውሳኔ ላይ የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ የሚታይባቸው ደካማ ውሳኔ አሰጣጥ ለነገም ፈተናው ይሆናል።
ድሬዳዋ በሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ ያሳየው ብቃት የኢትዮጵያ ቡናው ሽንፈት የቡድኑን መሻሻል ወደ ኋላ ያልጎተተው መሆኑን ያሳየ ነበር። ሆኖም በየጨዋታዎቹ ላይ ተመሳሳዩን ብቃት ማሳየት ከብርቱካናማዎቹ ይጠበቃል። በእንደነገ ዓይነቱ ወሳኝ ጨዋታ ደግሞ ቡድኑ ይበልጥ የአፈፃፀም ብቃቱ ከፍ ብሎ መግባት ይኖርበታል። ከድሉ ባሻገር ድሬዎች ግባቸውን ሳያስደፍሩ መውጣታቸው በርካታ የግብ ዕድል ከሚፈጥረው የነገ ተጋጣሚያቸው ጋር ለሚያደርጉት ጨዋታ ማሳደር የሚገባቸው ጥንካሬ ነው። እንደቡድን ከመከላከሉ ባለፈ የአማካይ ክፍል ቁጥጥርን ለተጋጣሚው አሳልፎ አለመስጠት ቡድኑ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ወሳኝ ሲሆን በማጥቃቱ ረገድ ያለው ግለሰባዊ እምርታዎችም ነገ ሊያግዙት ይችላሉ። ከአዲስ አበባ አጥቂዎች እጅግ በላቀ መረጋጋት ዕድሎችን ሲጨርስ የታየው ሄኖክ አየለ እንዲሁም የጨዋታ አቀጣጣይነት ሚና ኖሮት ያየነው አብዱርሀማን ሙባረክ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ የሚሆኑ እና ነገ ለምስራቁን ክለብ ወሳኝ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው።
አዲስ አበባ ከተማ ቴዎድሮስ ሀሙ እና ዘሪሁን አንሼቦ በጉዳት ምክንያት ለነገው ጨዋታ አይደርሱለትም። አቤል ከበደን በቅጣት የሚያጣው ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ዳንኤል ኃይሉ ከጉዳት ሲመለስለት ሁለት ቀን በጉዳት ምክንያት ልምምድ ያልሰራው ጋዲሳ መብራቴ መሰለፍ እርግጥ አልሆነም።
የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ዮናስ ካሳሁን ፣ ረዳቶች ፍፁም ካሳሁን እና ኤፍሬም ኃይለማርያም ፣ አራተኛ ዳኛ ምስጋናው መላኩ ፣ ተጨማሪ ረዳቶች አያሌው አሰፋ እና ተከተል በቀለ።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ሦስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ድሬዳዋ ሁለቴ አሸንፎ አንዴ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ድሬዳዋ ሦስት አዲስ አበባ ደግሞ አንድ ጎል አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)
ዳንኤል ተሾመ
አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ሳሙኤል አስፈሪ – አዩብ በቀታ – ሮቤል ግርማ
ሙሉቀን አዲሱ – ቻርለስ ሩባኑ – ኤሊያስ አህመድ
እንዳለ ከበደ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ፍፁም ጥላሁን
ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)
ፍሬው ጌታሁን
እንየው ካሣሁን – አውዱ ናፊዩ – መሳይ ጳውሎስ – አብዱለጢፍ መሐመድ
አቤል አሰበ – ብሩክ ቃልቦሬ
አብዱርሀማን ሙባረክ – ሱራፌል ጌታቸው – ጋዲሳ መብራቴ
ሄኖክ አየለ
ባህር ዳር ከተማ ከ አዳማ ከተማ
የአሁኑን እና የቀድሞውን የውድድሩ አስተናጋጅ ከተማ ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ ቀትር ላይ ይከናወናል። በሜዳው የውድድሩን የመጨረሻ ምዕራፍ በማድረግ ላይ የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ ከፋሲል ከነማው ሽንፈት መልስ አዳማን ይገጥማል። ከወልቂጤው ፎርፌ በኋላ በአምስት ጨዋታዎች ሁለት ነጥቦችን ብቻ ያሳኩት የጣና ሞገዶቹ ቀስ በቀስ ራሳቸውን ለወራጅ ቀጠናው ቀርበው ያገኙት በመሆኑ ይህንን ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ይኖርባቸዋል። ከድል ከራቀ ዘጠኝ ጨዋታዎችን ያስቆጠረው አዳማ ከተማም የአደጋ ክልሉ ስጋት የለበትም ማለት አይቻልም። በመሆኑም የናፈቀውን ድል ማግኘት እና ነጥቡን 30 ማድረስ አዳማ ከዚህ ጨዋታ የሚፈልገው የመጨረሻ ውጤት ነው።
የጣና ሞገዶቹ አሁንም ንፁህ የግብ ዕድሎችን ደጋግሞ የመፍጠር እና በግብ ፊት ትክክለኛ ውሳኔ ወስኖ የማስቆጠር ችግራቸው ለሦስት ዘጠና ደቂቃዎች እንደቀጠለ ነው። በፈጠራው ረገድ የቡድኑ ዐይን የሆነው እና በሰባት ግቦች የቡድኑ ከፍተኛ አስቆጣሪንነትን የሚመራው ፍፁም ዓለሙን በነገው ጨዋታ ማጣት ደግሞ ለአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ ተጨማሪ የራስ ምታት ይመስላል። ጨዋታው ጠንካራ የመከላከል መዋቅር ካለው ቡድን ጋር እንደመደረጉ ቡድኑ ወደ ሳጥን የሚደርስባቸውን ሌሎች መንገዶች መዘየድ የግድ ይለዋል። ባለፉት ጨዋታዎች እጁ ላይ ያሉትን የፊት መስመር ተሰላፊዎች በሙሉ አፈራርቆ የተጠቀመው ባህር ዳር የሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር ሚናን ለአብዱልከሪም ኒኪማ ጭምር ሰጥቶ ግብ የማስቆጠር ችግሩን ለመፍታት ጥረት አድርጓል። እስካሁን ይህንን ችግሩን መፍታት ባለመቻሉ ነገም የደጋፊውን ጉጉት ተከትሎ የሚመጣን ጫና ተቋቁሞ በእርጋታ ዕድሎችን የሚጨርስ ጥምሩት አስፈላጊው ይሆናል።
አዳማ ከተማም በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ተመሳሳይ ችግር አለበት። ከአቻ ውጤቶች መላቀቅ ቀላል ያልሆነለት አዳማ ከተማ በግለሰብ ደረጃ እንደዳዋ ሆቴሳ ዓይነት ጥሩ አጥቂዎችን ቢይዝም ሜዳ ላይ አስፈላጊ በሆኑ ቅፅበቶች ወቅት ግቦችን እያስቆጠረ አይገኝም። ለአዳማ ከተማ ጥሩ ዜና የሚሆነው የነገው ጨዋታ አርባምንጭ ከተማን ከገጠመበት የመጨረሻ ጨዋታ አንፃር ጥብቅ መከላከል ሊገጥመው አለመቻሉ ነው። ይህ መሆኑ ለተቀዛቀዙት የቡድኑ አጥቂዎች በፈጣን ጥቃት የተሻለ ጊዜ እና ቦታን የሚያገኙባቸው ቅፅበቶችን ሊፈጥርላቸው ይችላል። ከዚህ ባለፈም ግን የቡድኑ የአማካይ ክፍል ከፍ ባለ መታተር ብልጫ እንዳይወሰድበት ከማድረግ ባለፈ መሀል ለመሀል ዕድሎችን መፍጠር ሲጠበቅበት የተዳከመው የመስመር ተከላካዮቹ የማጥቃት ተሳትፎም ጥራት ያላቸውን ኳሶች ወደ ሳጥን በማድረስ በኩል ሊሻሻል
ይገባዋል።
በጨዋታው በሁለቱም በኩል የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን ባህር ዳር ከተማ ፍፁም ዓለሙ እና ኦሴይ ማዉሊን በቅጣት ምክንያት ሲያጣ አዳማ ከተማ ደግሞ አዲስ ተስፋዬ ከቅጣት ይመለስለታል።
የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ፣ ረዳቶች አሸብር ታፈሰ እና ሰለሞን ተስፋዬ
፣ አራተኛ ዳኛ አለማየሁ ለገሰ፣ ተጨማሪ ረዳቶች ክንዴ ሙሴ እና ሸዋንግዛው ይልማ።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን ከተገናኙባቸው አምስት ጨዋታዎች ሦስቱ በባህር ዳር ከተማ አሸናፊነት ሲጠናቀቁ አንዴ ነጥብ ተጋርተው አዳማ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ድል ቀንቶታል። በግንኙነታቸው ባህር ዳር ከተማ ስድስት አዳማ ከተማ ደግሞ አንድ ግቦች አሏቸው።
ግምታዊ አሰላለፍ
ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)
አቡበከር ኑራ
ሣለአምላክ ተገኘ – ፈቱዲን ጀማል – ሰለሞን ወዴሳ – አህመድ ረሺድ
ፉዓድ ፈረጃ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – አብዱልከሪም ኒኪማ
ተመስገን ደረሰ – ዓሊ ሱሌይማን – ግርማ ዲሳሳ
አዳማ ከተማ (4-3-3)
ሴኩምባ ካማራ
ጀሚል ያዕቆብ – ቶማስ ስምረቱ – ሚሊዮን ሰለሞን – ደስታ ዮሐንስ
አማኑኤል ጎበና – ዮሴፍ ዮሐንስ – ዮናስ ገረመው
አቡበከር ወንድሙ – ዳዋ ሆቴሳ – አሜ መሐመድ
አርባምንጭ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ
የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ በወራጅ ቀጠናው እና በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ ፉክክር ላይ ጉዳይ ያላቸው ተጋጣሚዎችን ያገናኛል። ከአቻ ውጤት ቢመለስም ከዚያ በፊት ሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች ያገኙት አርባምንጭ ከሰንጠረዡ ወገብ ተንሸራቶ ራሱን ወደ ወራጅ ቀጠናው ተጠግቶ አኝቶታል። ከታችኛው ዞን ያለውን የአራት ነጥብ ርቀት በዚህ ጨዋታ ማስፋት ካልቻለም በቀሪ ሳምንታት ይበልጥ ጫና ውስጥ ሊገባ ይችላል። ከድል ከራቀ አራት ጨዋታዎች የሆኑት ሀዋሳ ከተማም ደካማ አቋሙ ከሁለተኝነት ደረጃ እያራቀው ይገኛል። ቡድኑ ነገ ሙሉ ውጤት ካላሳካም ወደ አፍሪካ ውድድር መድረክ የመመለስ ህልሙ እየሳሳ ሊሄድ ይችላል።
ከተከታታይ ሽንፈቶች መልስ ወደ አቻ ውጤት የመጣው አርባምንጭ ከተማ በደረጃ ሰንጠረዡ ያለበት ቦታ በአቻ ውጤት እንዲረካ የሚያደርግ አይደለም። በመሆኑም በነገው ጨዋታ ቡድኑ በዋናነት ግቦችን ስለሚያስቆጥርበት መንገድ አጥብቆ ማሰብ የሚገባው ይመስላል። በአራት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ ኳስ እና መረብን ያገናኙት አርባምንጮች አዳማን በገጠሙበት ጨዋታ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን የፈጠሩባቸው አጋጣሚዎች በጣም ጥቂት ነበሩ። ከዚህ አንፃር ቡድኑ ነገ የተሻለ ድፍረት ጨምሮ በዋናነት ከኋላ ስህተቶችን የደጋገመው የነገ ተጋጣሚውን እንቅስቃሴ ከጅምሩ በማፈን ወደ ግብ ለመድረስ እንደሚጥር ይጠበቃል። ለቡድኑ ቀጥተኛ አጨዋወት የተመቸው አህመድ ሁሴን ባሳለፍነው ጨዋታ በተጠባባቂነት መታየቱ ነገ የመሰለፍ ዕድልን የሚያሰጠው ከሆነ ለአዞዎቹ የፊት መስመር መጠናከር ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ይገመታል።
ሀዋሳ ከተማ ለሳምንታት የመጣበት የአሰላለፍ እና የተጫዋቾች ምርጫ በቅርብ ሳምንታት በአስገዳጅ ሁኔታ ለውጦችን እያስተናገደ ሲመጣ በሁሉም ዲፓርይመንቶች ላይ መዳከሞች እየተስተዋለበት ይገኛል። ከሁሉም በላይ ግን ግለሰባዊ እና የግሩፕ ስህተቶች የበረከተበት የኋላ ክፍሉ ከውጤት እያራቀው ይገኛል። በኳስ ምስረታ ሂደቱ መጀመሪያ ላይ ከነገ ከተጋጣሚው የፊት መስመር ከፍ ያለ ጫና ሊሰነዘርበት መቻሉ ደግሞ በዚህ ድክመቱ ላይ ይበልጥ ሰርቶ እንዲመጣ መልዕክት የሚያስተላልፍለት ነው። በማጥቃቱ ረገድ ኃይቆቹ አጥቂያቸው ብሩክ በየነ ወደ ግብ አስቆጣሪነት መመለሱ መልካም ዜና ይሆንላቸዋል። ሆኖም ግን ሀዋሳ የቀደመ ጥንካሬውን ለመመለስ ከመስመር መነሻ የሚያደርጉ አደገኛ ኳሶቹን እንዲሁም ለተጋጣሚ ሳጥን ቀርበው ልዩነት የሚፈጥሩ አማካዮቹን ብቃት መልሶ ማግኘት ያሻዋል።
አርባምንጭ ከተማ አንድነት አዳነ ፣ ፍቃዱ መኮንን እና ተካልኝ ደጀኔን በጉዳት ምክንያት አያገኝም። በሀዋሳ ከተማ በኩል ላውረንስ ላርቴ ፣ ፀጋአብ ዮሐንስ ፣ መስፍን ታፈሰ እና መሐመድ ሙንታሪ ጉዳት ላይ የሚገኙ ሲሆን መድኃኔ ብርሀኔ ግን ከቅጣት መልስ ለቡድኑ እንደሚሰለፍ ይጠበቃል።
የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ባህሩ ተካ ፣ ረዳቶች ማንደፍሮ አበበ እና ድሪባ ቀነኒ ፣ አራተኛ ዳኛ እያሱ ፈንቴ ፣ ተጨማሪ ረዳቶች ፍሬዝጊ ተስፋዬ እና አብዱ ይጥና።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ቡድኖቹ እስካሁን 15 ጊዜ የመገናኘት ታሪክ አላቸው። ከዚህ ውስጥ ስድስቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ሀዋሳ ከተማ ስድስት ጊዜ አርባምንጭ ደግሞ ሦስት ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በጨዋታዎቹ ከተቆጠሩ ግቦች 17ቱ የሀዋሳ 12ቱ ደግሞ የአርባምንጭ ሆነው ተመዝግበዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)
ሳምሶን አሰፋ
ወርቅይታደስ አበበ – ማርቲን ኦኮሮ – በርናንድ ኦቼንግ – መላኩ ኤልያስ
ሙና በቀለ – አቡበከር ሸሚል – እንዳልካቸው መስፍን – ሀቢብ ከማል
ፀጋዬ አበራ – በላይ ገዛኸኝ
ሀዋሳ ከተማ (4-3-3)
ዳግም ተፈራ
ዳንኤል ደርቤ – ፀጋሰው ድማሙ – አዲስዓለም ተስፋዬ – መድኃኔ ብርሀኔ
ወንድምአገኝ ኃይሉ – አንዱልባስጥ ከማል በቃሉ ገነነ
ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ – ተባረክ ሄፋሞ