የአሰልጣኞች አስተያየት | አዲስ አበባ ከተማ 1-1 ድሬዳዋ ከተማ

የረፋዱ ጨዋታ በአንድ አቻ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት አጋርተዋል።

አሰልጣኝ ሳምሶም አየለ – ድሬዳዋ ከተማ

ስለጥብቅ መከላከል

“ጥሩ ነው፣ የመጀመርያ አርባ አምስት ላይ ተከላካዩ የሚገባውን ሥራ ሰርቶ በሩን አስጠብቆ ያለ ጎል ወጥቷል። እንደ አጠቃላይ እኔ ከጠበኩት በታች ነው። የእኛ ቡድን በዚህ ረገድ የተሰጠውን ነገር ታክቲካሊ ሳይተገብር የወጣበት አጋጣሚ ካለፉት ጨዋታዎች የወረደ ነው። በአጠቃላይ ልጆቹ ላለመሸነፍ እስከመጨረሻው ደቂቃ ያደረጉት መስዋዕትነት ትልቅ አክብሮት አለኝ፣ በቀጣይ አስተካክለን ለመምጣት እንሞክራለን።

የጎል ሙከራ ውስንነት

“ ምክንያቱ መሐል ሜዳ ነው። ከመስመር የሚወጡ ድጋፍ የሚሰጡ ልጆች በተገቢው ኳስ አያገኙም፣ ከመሐል የሚነሱ ኳሶች የተቆራረጡ ነበር። ከተከላካይም በስርዓት ኳሶች አይመጡም። እነዚህ የማጥቃት እንቅስቃሴውን እንዳናደርግ መሰናክል ሆኖውብናል።

ስለመጨረሻው ጎል

“ትልቅ ዋጋ አለው። አንደኛ በእነርሱ ውጤት
ቢያልቅ ኖሮ የአንድ ነጥብ ልዩነት ይሆናል። ይህ ጎል ለቀጣይ ጨዋታ ያነሳሳናል። ሁለተኛ ከእነርሱ ጋር ያለንን የነጥብ ልዩነት ባለበት እንዲቀጥል ያደርጋል።

ስለሄኖክ አየለ

“ሄኖክ ካገኘ ያገባል ፤ የቦታ አጠቃቀሙ ምርጥ ነው። በጣም የተረጋጋ ብዙ የሚረበሽ ሰው አይደለም ዕድሉን ካገኘ። በቀጣይ ብዙ ጎሎች ያገባል የሚል ዕምነት አለኝ።”

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው – አዲስ አበባ ከተማ

ስለጨዋታው

“ያው ያገኘህውን ብዙ የጎል አጋጣሚ ሳትጠቀም ስትቀር ይህ ነገር ሊፈጠር እንደሚችል ይጠበቃል። ያመከናቸው ኳሶች ብዙ የሚያስቆጭ ነው። የእግርኳስ ውበቱ ስለሆነ በፀጋ መቀበል ነው።

ሰለመከላከል ድክመት

“የመጨረሻውን ጎል ከመመልከታችን በፊት እኛ ያገኘናቸውን ኳሶች ያያቹሁት ነው። እኔ በመጨረሻው ደቂቃ ስለተቆጠረው ጎል ማንንም መውቀስም ኃላፊነት እንዲወስድም አልፈልግም።

ስለአንድ ነጥቡ

“ ይህ ሦስተኛ ጨዋታዬ ነው። እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ፣ አሁንም አዲስ አበባ ይወርዳል የሚል ዕምነት የለኝም። እስከ መጨረሻው እታገላለሁ።

ስለሌሎች ክለቦች ውጤት

“እንግዲህ ማየት ነው። የራስን ነጥብ እየጣልክ የሰውን መቀነስ እና መደመሩ ሌላ ስሌት ስለሚሆን በራስ ለማሸነፍ ትግል ማድረግ ነው።”