አርባምንጭ ሀዋሳን 2-1 ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ
የፈለጉትን ስለማግኘታቸው
“ከሌሎች ጊዜ የተሻለ ነገር ነው። በመጀመሪያ አርባ አምስት እንደዚሁም በሁለተኛው ከገባብን በኋላ ነገሮችን ለመለወጥ ጥረት አድርገናል፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን በምታልፍበት መንገድ አንዳንዴ የአባቶችም ኃጥያት ሳይሆን የእኛም ድካም ሳይሆን አንዳንዴ በእግዚአብሔር ክብር የምታልፍበት ነገር ይኖራል፡፡ ስለዚህ ዛሬ እግዚአብሔርን በጣም ነው የማመሰግነው ፤ መልካም ነበር፡፡
ስለ ነበረው ጉጉት
“ይታወቃል ፤ ተቃራርበን ተሰብስበን ነው ያለነው፡፡ አሁን ካለንበት መውጣት አለብን። በተለይ ከእዚህ ከሀያ አካባቢ እና ከአስር በታችም ካለው አካባቢ መውጣት መቻል አለብን፡፡ ሦስት ተሸንፈን አንድ አቻ ሆነን ነው የመጣነው ስለዚህ አስቸጋሪ ነው። አስራ ሁለት ነጥብ ማግኘት ከነበርብንም አንፃር መቀራረቦች ጋር ተያይዞ እንዲህ ዓይነት ስሜት ይኖራል፡፡ ግን እግዚአብሔር ረድቶን ተጨንቀህ የምታመጣው አንዳንዴ ደስ ይላል፡፡
አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ
ስለ ጨዋታው
“እንቅስቃሴው መጥፎ አይደለም፡፡ በተሻለ ኳስ ይዘን ተጫውተናል፡፡ ትንሽ መጨረሻ አካባቢ ላይ የመጨረስ ችግር ዛሬ በቡድናችን ታይቷል፡፡ በተደጋጋሚ በተለይ ከዕረፍት በኋላ አግኝተናል የመጠቀም ችግር ነው፡፡ ከዛ ውጪ መሀል ተከላካዮቻችን የሚታየው ስህተት መጨረሻ ላይ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ በእንቅስቃሴ የተሻልን ሆነን ጎል ጋር ቶሎ ደርሰናል፡፡ እነርሱ በሚጥሉት ረጃጅም ኳሶች እኛ በምንሰራው ስህተት ነው ለመጠቀም ያሰቡት። የመጀመሪያውን የቆመ ኳስ ነው ያገቡት፡፡ ሁለተኛውም የተከላካዮቻችን የአቋምም ችግር ነው፡፡ በእንቅስቃሴ ደረጃ ጥሩ ብንሆንም በውጤት ባንታጀብም ተሸንፈናል፡፡
በቀኝ መስመር የነበረው ክፍተት
“መስመር ላይ ያሉት የእነርሱ በእንቅስቃሴ ሳይሆን፡፡ እዛ ጋር ወጣ ይሉና ያገኙት እና ክሮስ ያደርጉታል፡፡ ይሄን ያህል የከፋ አደጋ የተፈጠረ ነገር የለም። እንደዛም ሆኖ በኳስ ቁጥጥሩ ፣ ጎል ጋር በመድረስ ፣ የጎል አጋጣሚዎችን በመፍጠር ፣ በጣም የተሻልን ነበርን፡፡ ይሄን በግልፅ መናገር ይቻላል፡፡ ቡድናችን አልፎ አልፎ የሚቆሙ ኳሶች ችግር አሁንም እየተቆጠረብን ነው፡፡ ያንን ማስተካከል ነው፡፡
ከወልቂጤ በኋላ አለማሸነፋቸው
“ሦስት ነጥብ ዝሞ ብሎ የሚገኝ አይደለም፡፡ በተደጋጋሚ የሰራኸው ቡድን ሲፈርስ አዲስ ቡድን ነው የምትሰራው እና በእዚህ መሀል ውጤት ለማምጣት ትቸገራለህ፡፡ ይሄ ነው እኔ ቡድን ላይ የሚታየው ስድስት ሰባት ሰው ከቋሚ ሲወጣ ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ የቡድናችን የስኳድ ጥበት አንዱ ችግር ነው፡፡ እነዚህን መሸፈን አለመቻላችን ሌላው ሁለተኛ ችግር ነውና በዚህ አጋጣሚ በእንቅስቃሴ ለመምጣት ብንሞክርም አሁንም ተፅእኖ ፈጣሪ ልጆቻችን ቡድኑ ውስጥ ባለመኖራቸው እየከፈልን ያለነው መስዋዕትነት ነው ብዬ የማስበው፡፡”