አዳማ ከተማ ከአሠልጣኙ ጋር ተለያይቷል

ያለፉትን አስር ጨዋታዎች በሊጉ ማሸነፍ ያልቻለው አዳማ ከተማ ከአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጋር በስምምነት መለያየቱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

የዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከመጀመሩ በፊት አዳማ ከተማን ለማሠልጠን ፊርማውን ያኖረው አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በዝውውር መስኮቱ ራሱን በማጠናከር ውድድር ቢጀምርም እስካሁን ከአራት ጨዋታዎች በላይ ቡድኑን ለድል ማብቃት አልቻለም። በእንቅስቃሴ ደረጃ ብዙ የሚያስተቹ ችግሮች ቡድን ላይ ባይኖሩም ጨዋታን ከማሸነፍ ጋር ተያይዞ ባለ ክፍተት የክለቡ አመራር ከደቂቃዎች በፊት አሠልጣኙ ላይ ውሳኔ ማሳለፉን አውቀናል።

ከትናንቱ የባህር ዳር ከተማ ሽንፈት ማግስት ከአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጋር ለመነጋገር የተቀመጠው የክለቡ አመራርም በስምምነት እንዲለያዩ ማድረጉን አውቀናል። በቀሪ የሊጉ ጨዋታዎች ቡድኑን በጊዜያዊነት እያሰለጠነ እንዲቀጥል ደግሞ የፋሲል ምክትል የነበረው ይታገሱ እንዳለ ተመርጧል። ሁለተኛው ምክትል አሠልጣኝ አብዲ ቡሊ ደግሞ ይታገሱን እንዲረዳ መደረጉን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

አዳማ ቀጣይ የሊጉ መርሐ-ግብሩን በሳምንቱ መጨረሻ በደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ ከሚገኘው ሰበታ ከተማ የሚያደርግ ይሆናል።

ያጋሩ