ሪፖርት | ሰበታ ተከታታይ ድሉን አሳክቷል

በዛሬው ቀዳሚ ጨዋታ ሰበታ ከተማ ከኋላ በመነሳት ወልቂጤ ከተማን 2-1 አሸንፎ አንድ ደረጃ አሽሏል።

ወልቂጤ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡናው ሽንፈት ሦስት ለውጦች ሲያደርግ ሰዒድ ሀብታሙን በሮበት ኦዶንካራ ፣ ዮናታን ፍሰሀን በተስፋዬ ነጋሽ እንዲሁም አክሊሉ ዋለልኝን በዮናስ በርታ ምትክ ተጠቅሟል። ሰበታ ከተማዎች ግን ጅማን የረቱበትን ቀዳሚ አሰላለፍ ሳይቀይሩ ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ጨዋታው በተነቃቃ የማጥቃት ጥረት የተጀመረ ነበር። ወልቂጤዎች በፍጥነት የማዕዘን ምት ያስገኘላቸውን ጥቃት ሲሰነዝሩ ሰበታዎችም ገና በ2ኛው ደቂቃ ያለቀለት የግብ ዕድል ፈጥረዋል። አብዱልሀፊስ ቶፊቅ በቶሎ በተጀመረ ቅጣት ምት 3 ለ 1 በሆነ የቁጥር ብልጫ ሳጥን ጋር ደርሶ ለጌቱ ኃይለማሪያም ያሳለፈውን ኳስ የመስመር ተከላካዩ በቀኝ ገብቶ ከሰዒድ ሀብታሙ ፊት ጥሩ ዕድል ቢያገኝም ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። ቀጣዮቹ ደቂቃዎችም በጥሩ የማጥቃት ምልልስ የቀጠሉ ነበሩ። በተለይም የወልቂጤው አጥቂ ጌታነህ ከበደ በመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ብቻ ወደ አራት የሚጠጉ ሙከራዎችን አድርጓል። ከእነዚህም ውስጥ 9ኛው ደቂቃ ላይ በግራ ከበኃይሉ ተሻገር የደረሰውን የተሰነጠቀ ኳስ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ወደ ግብ ሞክሮ በለዓለም ብርሀኑ ጥረት የዳነበት ኢላማውን የጠበቀ ነበር።

ጨዋታው በሂደት የማጥቃት ግለቱ እየተቀዛቀዘ በመሀል ሜዳ ፍልሚያ ተተክቷል። ቡድኖቹ የጨዋታውን የኳስ ፍሰት ለመቆጣጠር በተመጣጠነ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ እና የማቀበል ስኬት ቢፎካከሩም ወልቂጤዎች ወደ ቀኝ አድልተው አልፎ አልፎ ወደ አደጋ ከመቅረባቸው ውጪ የመጀመሪያዎቹ ሙከራዎች በድጋሚ ሳይታዩ ቆይተዋል።

ከውሃ ዕረፍቱ በኋላ ግን የወልቂጣዎች የቀኝ ጥቃት በጥሩ የማጥቃት ሽግግር ሙከራዎችን ማሳየት ጀምሯል። በተለይ 30ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ከመሀል ተቀብሎ በቀኝ ለሚገኘው ጫላ ተሺታ ካሳለፈለት በኋላ በቀጥታ ሩጫ ግብ አፋፍ ላይ ደረሶ ጫላ የመለሰውን ኳስ ተንሸራቶ ለማስቆጠር ያደረገው ሙከራ ለግብ የቀረበ ነበር። 38ኛው ደቂቃ ላይም አብዱልከሪም ወርቁ ከተከላካይ ጀርባ የጣለለትን ኳስ ረመዳን የሱፍ ከሳጥን ውስጥ በቀጥታ ሞክሮ ከፍ ብሎ ወጥቶበታል።

ሰበታ ከተማዎች በመጨረሻዎቹ አምስት ደቂቃዎች ወደ ወልቂጤ ከተማ ሳጥን መቅረብ ችለዋል። በዚህም በሳሙኤል ሳሊሶ ፣ ኃይለሚካኤል አሰፍርስ እና አብዱልሀፊስ ቶፊቅ ከሳጥን ውጪ ሙከራዎች ማድረግ ችለው ነበር። ከሁሉም በላይ ግን 45ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ ጌቱ የተሻማውን ኳስ ዴሪን ንስባምቢ አመቻችቶለት ጋብርኤል አህመድ ባያገኘውም አብዱልሀፊስ በነፃነት ከቅርብ ርቀት ወደ ግብ የላከው ኳስ በሰዒድ ሀብታሙ እና በግቡ ቋሚ የተመለሰበት ለሰበታ የሚያስቆጭ ሙከራ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ወልቂጤዎች ከፍ ባለ ጫና ጨዋታውን ጀምረዋል። በክፍት እንቅስቃሴ እና በቆሙ ኳሶች ደጋግመው ወደ ግብ ሲደርሱም ታይቷል። በተለይ 54ኛው ደቂቃ በኃይሉ ከመሀል ሜዳ እየገፋ የመጣውን ኳስ ይሰጣል ተብሎ ሲጠበቅ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ በቀጥታ የመታው ኳስ ወደ ላይ የወጣበት አደገኛ ነበር። 

ቡድኑ ማጥቃቱን ቀጥሎ 61ኛው ደቂቃ ላይ በለስ ሲቀናው በግራ ከከፈተው ጥቃት ረመዳን የሱፍ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ የላከው ኳስ በተከላካዮች ተጨረርፎ ሲደርስ ግብ ሲያነፍነፍ የቆየው ጌታነህ ከበደ ሁለተኛው ቋሚ ላይ በግንባሩ ጎል አድርጎታል። ሆኖም ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ሰበታዎች አደጋ ሲጥሉበት ከነበረው የቀኝ መስማር ጌቱ ኃይለማሪያም ያሻማውን ኳስ ሳሙኤል ሳሊሶ ሁለተኛው ቋሚ ላይ ደርሶ በግንባሩ ግብ አድርጎታል።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎች መሀል ሜዳ ላይ የነበረው ፍልሚያ ተመልሶ ሲታይ ቡድኖቹ በእንቅስቃሴ ከሁለቱ ሳጥኖች መራቅ ጀምረው ነበር። ሆኖም 80ኛው ደቂቃ ላይ ሰበታ ከተማዎች በድንቅ የማጥቃት ሽግግር ጎል አስቆጥረዋል። በዚህም አብዱልሀፊስ ቶፊቅ በተከላካዮች መሀል ለመሀል በመሬት የሰነጠቀውን ኳስ ዱሬሳ ሹቢሳ በፍጥነት በመግባት ከሰዒድ ጋር ተገናኝቶ ጎል አድርጎታል።

በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ወልቂጤዎች ሙሉ ኃይላቸውን በማጥቃት ላይ በማድረግ ተንቀሳቅሰዋል። ሆኖም ሰበታ ከተማዎች አደገኛ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ሲያገኙ ታይቷል። ከእነዚህ ውስጥ በጭማሪ ደቂቃ ንስምባቢ በረጅሙ ከተጣለለት ኳስ ከተከላካይ ጀርባ ገብቶ ያደረገው ሙከራ ሰዒድ ተጨርፎት በዳግም ከግብ አፋፍ ላይ ሲወጣ ተቀይሮ የገባው ዓለምአንተ ካሳ ነፃ ሆኖ የሳተው ሰበታን ዋጋ የሚያስከፍል ይመስል ነበር። ወልቂጤ ከተማዎችም በጌታነህ ከበደ ያደረጉት ሙከራ ሳጥን ውስጥ በበረከት ሳሙኤል የተደረበ ሲሆን ሰከንዶች ሲቀሩ ያገኙትን የቅጣት ምትም ጌታነህ ለማስቆጠር ሞክሮ ሳይሳካለት ጨዋታው በሰበታ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተቋጭታል።

በውጤቱ ተከታታይ ድል ያሳካው ሰበታ ከተማ ነጥቡን 20 አድርሶ ከሊጉ ግርጌ ወደ 15ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ወልቂጤ ከተማ 29 ነጥቦች ላይ ቀርቷል።