ሪፖርት | ፋሲል ከመሪው ጋር ያለውን ልዩነት አስጠብቋል

ጥሩ ፉክክር ባስመለከተን የምሳ ሰዓቱ ጨዋታ ፋሲል ከነማ መከላከያን 2-1 በማሸነፍ ከቀጣዩ ወሳኝ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በፊት ቁልፍ ድል አስመዝግቧል።

ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ሲዳማ ቡናን አሸንፈው የመጡት መከላከያዎች በጨዋታው የተጠቀሙት ስብስብ ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ የቀረቡ ሲሆን በአንፃሩ ፋሲል ከነማዎች ባህር ዳር ከተማን ከረታው ስብስብ ባደረጉት ሁለት ለውጥ ቀይ ካርድ በተመለከተው ያሬድ ባየህ ምትክ ሙጂብ ቃሲምን እንዲሁም በይሁን እንደሻው ምትክ ደግሞ ሀብታሙ ተከስተን ብቻ ቀይረው ቀርበዋል።

መከላከያዎች ገና በመጀመሪያው ደቂቃ ነበር አደገኛ ሙከራ ማድረግ የቻሉት። በሜዳው የላይኛው ክፍል ከነጠቁት ኳስ መነሻ ባደረገ የጨዋታ ሂደት የተገኘችን አጋጣሚ እስራኤል እሸቱ ከሳጥን ጠርዝ በቀጥታ ሞክሮ ሚካኤል ሳማኪ በግሩም ቅልጥፍና አድኖበታል። ፈጠን ባለ አጀማመር የቀጠሉት መከላከያዎች በ5ኛው ደቂቃ ቢኒያም በላይ ላይ ከድር ኩሊባሊ በሰራው ጥፋት የተገኘችውን የፍፁም ቅጣት አሚኑ ነስሩ አስቆጥሮ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ያደረጉት ፋሲል ከነማዎች በ10ኛው ደቂቃ አቻ መሆን ችለዋል። በግሩም የማቀበል ሂደት በረከት ደስታ ከግራ የሳጥን ጠርዝ ወደ ውስጥ ያሳለፈለትን ኳስ ተጠቅሞ ሽመክት ጉግሳ በተረጋጋ አጨራረስ የአቻነት ግቧን አስቆጥሯል።

መሀል ሜዳ ላይ በተለይ ከበድ ያለ ፉክክርን ባስመለከተን አጋማሽ ፋሲሎች የተሻለ ኳሶችን በመቀባበል ተደራጅተው መሀል ሜዳ ላይ ኳሶችን በማቋረጥ አደጋ ለመፍጠር ያሰቡት መከላከያዎች ላይ የበላይነት ለመውሰድ ጥረዋል። ከአጀማመሩ አንፃር ቀዝቀዝ ብሎ በቀጠለው ጨዋታ መከላከያዎች ከርቀት በሚደረጉ ሙከራዎች አደጋ ለመፍጠር ሞክረዋል። በ24ኛው ደቂቃ ላይ በግሩም ቅብብል በኋላ ምንተስኖት አዳነ ያገኘውን ኳስ ከሳጥን ውጪ የመታው ጠንካራ ምትን እና በ35ኛው ደቂቃ ላይ በተመሳሳይ ግሩም ሀጎስ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ ወደ ግብ በላካት ኳስ አደገኛ ሙከራ ቢያደርጉም በሁለቱም አጋጣሚዎች ሚካኤል ሳማኪ የሚቀመስ አልሆነም።

በተመሳሳይ ቢኒያም በላይ በተሰለፈበት የግራ ወገን የቡድን ማጥቃት የተሻለ የነበረበት አጋማሽ ነበር። በዚህም ቢኒያም በግሉ ተጫዋቾችን እየቀነሰ ስጋት ለመደቀን ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። በተለይ በ38ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ከተሻገረ ኳስ የፈጠሩትን ዕድል ምንተስኖት አዳነ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በአንፃሩ ፋሲል ከነማዎች ደግሞ ከኳስ ውጪ ቦታዎችን በመዝጋት ረገድ ጠጣር የነበረው የመከላከያ ውቅርን ለማስከፈት ተቸግረዋል።

በሁለተኛው አጋማሽም እንደ መጀመሪያው ሁሉ ፋሲሎች ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩበት ሲሆን በአንፃሩ መከላከያዎች ደግሞ በተነፃፃሪነት የተሻለ የማጥቃት አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም በማጥቃት ሲሶ ላይ የነበራቸው አፈፃፀም እጅግ ደካማ ነበር። ደቂቃዎች እየገፉ ሲሄዱ ከተጠባባቂ ወንበር እየተነሱ ፋሲልን በመታገድ ረገድ ባለ አስደናቂ አበርክቶዎቹን ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ እና ፍቃዱ ዓለሙን ቀይረው ያስገቡት ፋሲሎች ቅያሬያቸው ዳግም ፍሬ አስገኝቶላቸዋል።

በ74ኛው ደቂቃ ላይ በፋሲሎች በኩል ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ ፋሲልን መሪ አድርጓል። ዓለምብርሃን ይግዛው ከቀኝ መስመር አስደናቂ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ወደ መከላከያ ሳጥን ከደረሰ በኋሌ ወደ ውስጥ ያሳለፈው ኳስ በአሚን ነስሩ ሲመለስ ሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሆኖ ያገኛትን ኳስ ነበር ናትናኤል በግሩ እግሩ በመምታት የቡድኑን የዋንጫ ተስፋ ያለመለመች ግብ ያስቆጠረው።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ሁለቱም ቡድኖች የተሻለ የማጥቃት ጥረት የተመለከትን ቢሆንም ለግብነት የቀረቡ ሙከራዎችን ግን አምብዛም አልታዩም። በ87ኛው ደቂቃ ቢኒያም በላይ ያሻማል ተብሎ ሲጠበቅ ወደ ግብ የላካትን ኳስ ሳማኪ የያዘበት ኳስ የተሻለች አጋጣሚ ነበረች።

መደበኛ ደቂቃው መጠናቀቂያ ላይ የጭንቅላት ጉዳትን ያስተናገደው የፋሲል ከነማው የግብ ዘብ ሚካኤል ሳማኬ ቀሪዎቹን ደቂቃዎች የህክምና እርዳታ ተደርጎለት ለማጠናቀቅ ተገዷል። በተጨማሪ ደቂቃ መከላከያዎች በተከታታይ የማዕዘን ምቶች ተደጋጋሚ ጫና መፍጠር ቢችሉም ፋሲሎች ይህን ጫና ተቋቋመው ወሳኙን ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል። በተለይም ግሩም ሀጎስ ከማዕዘን ምት ከተናሳ ኳስ ያደረገውን ሙከራ ሀብታሙ ተከስተ ከመስመር ላይ ያዳነበት አጋጣሚ እጅግ አደገኛ ነበር።

ድሉን ተከትሎ ፋሲል ከነማዎች ነጥባቸውን ወደ 46 በማሳደግ በቀጣይ ሳምንት የሚገጥሙት ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ጫና ማሳደራቸውን ሲቀጥሉ መከላከያዎች ደግሞ በ30 ነጥብ ወደ 8ኛ ደረጃ ተንሸራተዋል።

ያጋሩ