አነጋጋሪ የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔዎች በታዩበት ጨዋታ ሲዳማ ቡና ወላይታ ድቻን 1-0 አሸንፏል።
በጨዋታው ወላይታ ድቻ በቅጣት እና በጉዳት ያጣቸው ደጉ ደበበ እና ምንይሉ ወንድሙን በመልካሙ ቦጋለ እና አበባየሁ አጪሶ ተክቷል። ሲዳማ ቡናዎች በአንፃሩ ከመከላከያው ጨዋታ አንፃር የመከላከል ዲፓርትመንታቸውን በሙሉ ቀይረዋል። በዚህም ዛሬ መክብብ ደገፉ ፣ ጊት ጋትኩት ፣ ያኩቡ መሀመድ ፣ አማኑኤል እንዳለ እና መሀሪ መና ጨዋታውን ሲጀምሩ አማካይ ክፍል ላይም ፍሬው ሰለሞን በክሪዚስቶም ንታምቢ ምትክ ወደ ሜዳ ገብቷል።
በጣም የተቀዛቀዘ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታው እንቅስቃሴ በወላይታ ድቻ ሜዳ ላይ ጀምሮ የተጠናቀቀ ነበር። ሲዳማዎች ከጅምሩ አንስቶ ኳስ ይዘው የወላይታ ድቻን የመከላከል መዋቅር ለማለፍ ጥረት ጀምረዋል። ሆኖም አደጋ የሌላቸውን ሙከራዎች ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን 17ኛው ደቂቃ ላይ ይገዙ ቦጋለ ከሀብታሙ ገዛኸኝ የተቀበለውን ኳስ ከቀኝ አቅጣጫ ሞክሮ ቢኒያም ገነቱ የመለሰውን ሳላዲን ሰዒድ ከቅርብ ርቀት በድጋሚ ሞክሮ የሳተው ቀዳሚው ጠንካራ ሙከራ ነበር።
14ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም ፍቅሬ ከመሀል ሜዳ ወደ ግብ የላከውን ኳስ መክብብ ደገፉ በቀላቡ ሲይዝበት ከታየው ሙከራ ውጪ ወላይታ ድቻዎች የማጥቃት ሂደቶችን በማቋረጥ ላይ ተጥምደው አሳልፈዋል። ቡድኑ ከስንታየሁ እና ምንይሉ ጉዳት ሌላ በሙሉ ጤና ላይ ይገኝ የነበረው አጥቂው ቃልኪዳን ዘላለምንም በጉዳት አጥቶ ለመቀየር በመገደዱ በመልሶ ማጥቃት ለመውጣት የሚያደርገውን ጥረት ይበልጥ አዳክሞበታል። ያም ቢሆን በመከላከሉ በኩል ድቻዎች 41ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት በተነሳ ኳስ ጊት ጋትኩት ካደረገው እና ቢኒያም ገነቱ ካዳነው ሙከራ ውጪ ሌላ የከፋ ጥቃት እንዳይሰነዘርባቸው ማድረግ ችለው ነበር።
ሆኖም አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሲቃረብ የዕለቱ ደካማ የዳኝነት ውሳኔዎች መታየት ጀምረዋል። በዚህም በረከት ወልደዮሐንስ ሳጥን ውስጥ ኳስ ለማስጣል ከይገዙ ቦጋለ
ጋር በተገናኘበት ቅፅበት አርቢትሩ ጥፋት ሰርቷል በማለት የሰጡትን አወዛጋቢ ፍፁም ቅጣት ምት ይገዙ ቦጋለ አስቆጥሮ ሲዳማ ቡናን መሪ አድርጓል።
ከዕረፍት መልስ ወላይታ ድቻዎች በተሻለ የማጥቃት ጉልበት ተመልሰዋል። ቡድኑ በፈጠረው ጫና የቆመ ኳስ ዕድሎችን ለማግኘት ቢጥርም ያለቀለት የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻለም። የተሻለው የ54ኛ ደቂቃ እንድሪስ ሰዒድ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራም ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። በቀጣዩ ደቂቃ ግን በጨዋታው ሌላ አነጋጋሪ የዳኝነት ውሳኔ ተመልክተናል። አበባየሁ አጪሶ ወደ ሳጥን ሲገባ በያኩቡ መሀመድ ጥፋት ተሰርቶብኛል በሚል ሲወድቅ ወላይታ ድቻዎች ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። ሆኖም እንድሪስ ሰዒድ የመታውን ኳስ ከዳኞች እይታ ውጪ መሆን የቻለው መክብብ ደገፉ መስመሩን ለቆ በመውጣት አድኖታል።
አጋጣሚውን መጠቀም ያልቻሉት ወላይታ ድቻዎች ያሏቸውን የቅያሪ አማራጮች በመጠቀም ለውጦችን በማድረግ በተሻለ ሁኔታ ጫና ፈጥረው ለማጥቃት ሞክረዋል። ሆኖም በአመዛኙ ከመስመሮች በሚነሱ ኳሶች ላይ የተመሰረተው የቡድኑ ጥቃት ተፈላጊዎቹን የግብ አጋጣሚዎች መፍጠር አልቻለም። ከመጀመሪያው አጋማሽ የኳስ ቁጥጥራቸው የራቁት ሲዳማዎች በአንፃሩ አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት ለመውጣት ቢሞክሩም አልሆነላቸውም። ሲዳማዎች የማጥቃት ሽግግሩ 77ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ይገዙ ቦጋለ ከፍሬው ሰለሞን በደረሰው ኳስ ሳጥን ውስጥ ቢገኝም በግብ ጠባቂው ቢኒያም ገነቱ ጥፋት ተሰርቶበት ወድቋል። በጨዋታው ሌላኛው አነጋጋሪ ውሳኔ ይህ እንቅስቃሴ በአርቢትሮቹ ሳይታይ ቀርቷል።
ጨዋታው ወደ ፍፃሜው ሲቃረብ ተቀይሮ የገባው ብሩክ ሙሉጌታ 87ኛው ደቂቃ ላይ ከፍሬው የተቀበለውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ይዞ በመግባት አስቆጠረ ሲባል ወደ ላይ የላከው ኳስ አስገራሚ ነበር። በተደጋጋሚ የቆሙ ኳሶች ከፍ ያለ ጫና መፍጠር የቻሉት ወላይታ ድቻዎችም 89ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ተነስቶ አንተነህ ጉግሳ ባመቻቸው ኳስ ጥሩ ዕድል ቢፈጥሩም ንጋቱ ገብረስላሴ አክርሮ የመታው ኳስ በመክብብ ደገፉ ተመልሷል።
ጨዋታው በዚህ መልኩ በሲዳማ 1-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ቡድኑ በ 37 ነጥቦች ወደ 3ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ሲችል ወላይታ ድቻ በአንድ ነጥብ ተበልጦ አራተኛ ላይ ተቀምጧል።
በጨዋታው በታየው የዳኝነት ውሳኔ በደል ደርሶኛል ያለው ወላይታ ድቻ የቴክኒክ ክስ ማስያዙም ተሰምቷል።