ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፩) – ክለብ ትኩረት

በጨዋታ ሳምንቱ የተመለከትናቸው ትኩረት የሳቡ ክለቦች በመጀመሪያው የዓበይት ጉዳይ ፅሁፋችን ተዳሰዋል።

👉 ወደመጣበት እየመለሰው የሚገኘው የአዲስ አበባ አልፈታ ያለ ችግር

በዘንድሮው የውድድር ዘመን ዳግም ወደ ሊጉ የተመለሱት አዲስ አበባ ከተማዎች ራሳቸውን ለመስዋት ያዘጋጁ ይመስላል በመጡበት የውድድር ዘመን ወደ ከፍተኛ ሊግ ለመውረድ በሰንጠረዡ ግርጌ የሚገኙትን ቡድኖች እየተማፀኑ ያለ ይመስላል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን የገጠመው ቡድኑ በሁለቱም አጋማሾች በብዙ መመዘኛዎች የበላይ ሆኖ ቢዘልቅሞ ጨዋታውን በጊዜ መግደል ሳይችል እንደተለመደው በመጨረሻ ዋጋ ለመክፈል ተገዷል።

ከተጋጣሚያቸው በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው አዲስ አበባ ከተማዎች የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ጭምር ልቀው ቢታዩም ማስቆጠር የቻሉት ግን አንዱን ነበር። አምስት ሙከራዎችን ያደረጉት አዲስ አበቤዎቹ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት የፈጠሯቸው ሁለት አደገኛ ዕድሎች ለማመን በሚቸግር መልኩ በቢኒያም ጌታቸው መክነዋል።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ጨዋታውን በጊዜ መቋጨት የተቸገሩት አዲስ አበባ ከተማዎች በ95ኛው ደቂቃ ባስተናገዱት ግብ ብዙ ከታተሩበት ጨዋታ ከሦስት ነጥብ ይልቅ ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ተገደዋል። በመጨረሻ ስድስት ጨዋታዎች በሙሉ ነጥብ የተጋራው ቡድኑ ያለ ግብ ከተጠናቀቀው የአዳማው ጨዋታ ውጪ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋሩበትን ጨምሮ በአምስቱም ጨዋታዎች አስቀድመው ባስቆጠሩት ግብ መምራት ቢችሉም በስተመጨረሻም ከጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ይዘው ወጥተዋል። ከእነዚህ የአቻ ውጤቶች የተወሰኑት ወደ ድል ተቀይረው ቢሆን ኖሮ ቡድኑ አሁን ላይ በሰንጠረዡ ይገኝበት የነበረውን ቦታ ላሰበ አዲስ አበባዎች በእጃቸው የነበረውን ወርቃማ ዕድል እያመከኑ እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም።

በ24 ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የመዲናዋ ክለብ በቀጣይ በሚያደርጋቸው ቀሪ የስድስት ሳምንት ጨዋታዎች ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም ለኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ደረጃ ቅርብ ከሆኑት ሲዳማ ቡና ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ወላይታ ድቻ በተጨማሪ በሊጉ ግርጌ ደግሞ የቅርብ ተፎካካሪዎቹ ጅማ አባ ጅፋር እና ሰበታን ይገጥማል። ቡድኑ አሁን እየሄደበት በሚገኘው አካሄድ ከእነዚህ በሁለቱ የሰንጠረዥ ፅንፍ ተዋናያን ከሆኑ ቡድኖች ጋር ከሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ ይወስዳል ብሎ ማሰብ እጅግ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው።

አዲስ አበባ በሰንጠረዡ ከሚገኝበት ቦታ አንፃር አለመሸነፍን ብቻውን በራሱ በመልካምነት ለመውሰድ የሚያስችል አለመሆኑን ተከትሎ የቡድኑ አሁናዊ አካሄድ እጅግ አሳዛኝ ሆኗል። በእያንዳንዱ ጨዋታ የተሻለ እየተንቀሳቀሰ በዚህ ደረጃ ነጥቦችን አሳልፎ የመስጠቱ ነገር በተናጠል የተወሰነ አካል ላይ ጣት የሚያስቀስር ሳይሆን እንደ ቡድን ሁሉም አባላት በጋራ የሚጋሩት መጥፎ ጉዞ ነው። ውጤት ያለማስጠበቅ ችግሩ በቅርብ ጨዋታዎች ብቻ ሳይሆን በውድድር ዓመቱ ሲታይበት የኖረ መሆኑ ደግሞ ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል። በዚህ ስር የሰደደ ችግር አዲስ አበባ ከእስካሁኖቹ 24 ጨዋታዎች በዘጠኙ ቀድሞ መምራት ቢችልም ውጤት ማስጠበቅ ባለመቻሉ 20 ነጥቦችን እንደዘበት ጥሏል።

በመሆኑም ይህ ሂደት በፍጥነት መገታት የሚችል ካልሆነ አዲስ አበባ ከተማ እንደ 2009ኙ ታሪኩ ሁሉ ባደገበት ዓመት ወደ መጣበት ሊግ ተንከብክቦ መመለሱ አይቀሬ ይሆናል።

👉 ባህር ዳር እና ድል ታርቀዋል

የፎርፌውን ውጤት ሳይጨምር በ12ኛ የጨዋታ ሳምንት ሀዋሳ ከተማን ከረቱ ወዲህ በጨዋታ ሦስት ነጥብ ለማስመዝገብ ተቸግረው የከረሙት ባህር ዳር ከተማዎች አዳማ ከተማን በመርታት ከ11 ጨዋታዎች በኋላ ሙሉ ሦስት ነጥብን በ90 ደቂቃ እንቅስቃሴ አሳክተዋል።

ከወትሮው በተሻለ ጨዋታውን ፈጣን በሆነ መንገድ ለመጀመር ጥረት ያደረጉት ባህር ዳር ከነማዎች ተመስገን ደረሰ ገና በ5ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ግብ ነበር ቀዳሚ መሆን የቻሉት። ከግቧ በኋላም በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ አዎንታዊነት መጫወት የቻለው ቡድኑ በተለይ በፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች አዳማ ከተማን ፈትኗል። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ከነበረባቸውም ጫና መነሻነት የተገኘውን ውጤት ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ በጥንቃቄ በመጫወት የናፈቃቸውን ድል አሳክተው ወጥተዋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተጫዋቾቹ እና በአሰልጣኞች ቡድን አባላት ላይ ይታይ የነበረው የደስታ ስሜት ቡድኑ የነበረበትን የአዕምሮ ውጥረት ደረጃ የሚያሳይ ነበር። በመጀመሪያዎቹ ሁለት በሜዳቸው ባደረጓቸው ጨዋታዎች ማሸነፍ አለመቻላቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ተቃውሞን ያስተናገዱት ባህር ዳሮች ይህ ድል ከደጋፊዎቻቸው ለመታረቅ ይረዳቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

አስከፊ የውጤት እጦት ጉዞ ላይ የነበረው የጣናው ሞገድ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት አዳማ ከተማ ላይ ያስመዘገበው ድል አጠቃላይ የውድድር ዘመን ጉዞውን የመቀየር አቅም አለው። በቀጣይ ሁለት የጨዋታ ሳምንታት ከሲዳማ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ከባድ ጨዋታዎች የሚጠብቁት ቡድኑ እነዚህን ፈተናዎች እንዴት ይወጣቸዋል የሚለውም ጉዳይ ከወዲሁ አጓጊ ሆኗል።

👉 ሀዋሳ ከተማ እየተፍረከረከ ይገኛል

የመጀመሪያው ዙር ሲጠናቀቅ በ27 ነጥቦች ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ4 ነጥብ ርቆ ይከተል የነበረው ሀዋሳ ከተማ አሁን ላይ ከዘጠኝ የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ነጥቡን በዘጠኝ ብቻ አሳድጎ ከመሪው በ18 ነጥብ ርቆ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በእነዚህ ዘጠኝ የጨዋታ ሳምንታት ቡድኑ ማግኘት ከሚገባው 27 ነጥብ ውስጥ ማሳካት የቻለው ነጥብ በመቶኛ ሲሰላ 33.34% ብቻ መሆኑ ሀዋሳ በሁለተኛው ዙር እንዴት አስቸጋሪ ጊዜን እያሳለፈ እንደሚገኝ ጠቋሚ ነው።

ነጥቦቹን እንኳን ወደ ጎን ትተን ቡድኑን በእንቅስቃሴ ረገድ ከመዘነው በተለይ በ18ኛ ሳምንት በከተማ ባላንጣቸው ሲዳማ ቡና 3-1 ከተረቱ ወዲህ የቀደመውን ሀዋሳ ከተማ ለመሆን ፍፁም ተቸግሯል።

በመጀመሪያ ዙር በተለየ ፍላጎት እና ትጋት ሲጫወት የምናውቀው ሀዋሳ ከኳስ ውጪ ከፍ ባለ ጉልበት ተጋጣሚውን ፋታ የሚነሳ እና ስል መልሶ ማጥቃት የሚሰነዝር ጭምር ነበር።
በመጨረሻዎቹ ጥቂት ጨዋታዎች ግን ፍፁም ተዳክሞ እና በጨዋታዎች ውስጥ ራሱን ለመግለፅ ተቸግሮ እየተመለከትን እንገኛለን። በአንድ ወቅት ስለአፍሪካ ተሳትፎ ያልም የነበረው ሀዋሳ አሁን ላይ በሁለተኝነት በሚደረገው ፉክክር ስለመዝለቁ መናገር አስቸጋሪ ነው። ወጣቱ ግብ ጠባቂ ዳግም ተፈራ በቋሚዎቹ መካከል ከሚያደርገው ጥረት ባለፈ የተቀሩት ክፍሎች በማጥቃትም ሆነ በመከላከል ፍፁም ደካማ ጊዜያትን እያሳለፉ ይገኛል። በተለይ ደግሞ የቡድኑ መከላከል በፍፁም እንደቀደመው ጊዜ ለመሆን ያለመቻሉ ጉዳይ አሳሳቢ ሆኗል። በተደጋጋሚ ዋጋ እያስከፈለው የሚገኘው ይህ የቡድኑ መከላከል በተጫዋቾች ሆነ በአደራደር መለዋወጥ ውስጥ እንኳን መሻሻሎችን አለማሳየቱ ጉዳይ ደግሞ ችግሩ ከግለሰባዊ ይልቅ መዋቅራዊም ስለመሆኑ ይጠቁመናል።

እርግጥ አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ እንዳሉትም በተለያዩ ምክንያቶች ከሰሞኑ የቡድኑ ተቀዳሚ ተመራጮች ግልጋሎት አለመስጠታቸውን እንደ ምክንያትነት ማቅረብ ቢቻልም ከጥቂት ሳምንታት በፊት ብዙዎችን ተስፋ እንዲሰንቁ ያስገደደ ነገርን ያሳየው ቡድን አሁን ላይ በዚህ ደረጃ መንገራገጩ እጅግ የሚያስገርም ነው።

👉 ስልታዊው ሀዲያ ሆሳዕና ወደ ማሸነፍ ተመልሷል

በመጨረሻ ሦስት የጨዋታ ሳምንት ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች አንድ ብቻ ማሳካት ችለው የነበሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን በመርታት ወደ ድል ተመልሰዋል።

በሊጉ በተለይ በመከላከሉ ረገድ የተረጋጋ የነበረው ቡድኑ ሰሞኑን በቀላሉ ግቦችን ሲያስተናግድ የተመለከትን ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን በተለይ የተስፋዬ አለባቸው እና ግርማ በቀለን መመለስ ተከትሎ በመከላከሉ ረገድ ጠንካራ የነበረው ሀዲያን ተመልክተናል።

አሰልጣኙ ከጨዋታ በኋላ እንደተናገሩትም ለተጋጣሚ ኳሱን ለቆ ለመጫወት የፈለገው ቡድን በተለይ መሀል ሜዳው ላይ የተጫዋቾቹን ቁጥር በማብዛት ለተጋጣሚ ተጫዋቾች ጨዋታውን አስቸጋሪ ለማድረግ ጥረት አድርጓል ፤ በዚህም ከመሀል ሜዳ ከሚነጠቁ ኳሶች ጥቃቶችን ለመሰንዘር ሞክርሯል። በጨዋታው የኢትዮጵያ ቡናን እንቅስቃሴ በማክሸፍ ውጤታማ ያደርገናል በሚል ተግባራዊ ያደረጉት ይህ ስልት በስተመጨረሻም ባለ ድል አድርጓቸዋል።

ሌላኛው ትኩረት የሚስበው ጉዳይ ሀዲያ ሆሳዕና በተለይ በሰንጠረዡ አናት ከሚገኙ ቡድኖች ጋር በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች በጣም ኮስተር ብሎ ተጋጣሚዎቹ በሚፈልጉት መንገድ ጨዋታዎችን መወሰን እንዳይችሉ ሁኔታዎችን አስቸጋሪ ለማድረግ ሲሞክር በአመዛኙ ይህ አካሄዱ ውጤታማ ሲያደርገው እየተመለከትን የመሆኑ ጉዳይ ነው። የቡድኑ የውጤት ዝርዝርም ይህን በሚገባ ያሳያል።

ኢትዮጵያ ቡናን በደርሶ መልስ ሲረታ ከሀዋሳ እና ወላይታ ድቻ ላይ ሦስት ነጥብ የወሰደው ቡድኑ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ አንድ ነጥብን እስካሁን ባደረጋቸው ጨዋታዎች አሳክቷል። በሊጉ ከወገብ በታች ካሉ ቡድኖች ጋር ግን የማሸነፍ ቅድመ ግምትን አግኝቶ በሚገባባቸው ጨዋታዎች ውጤቱ ከአማካይ በታች ሆኖ በተደጋጋሚ ነጥቦችን ሲጥል ታይቷል።

በዚህ የውጤት ተቃርኖ ውስጥ የሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና ቀሪ የውድድር ጊዜውን በወጥ ብቃት ያጠናቅቅ ይሆን ?

👉 መሪውን የፈተነው ጅማ አባ ጅፋር

በሊጉ ግርጌ ላለመውረድ እየተውተረተረ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ምንም እንኳን ቢሸነፍም የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስን በከባዱ መፈተን ችሏል።

በጨዋታው ገና ከጅምሩ ጥንቃቄን በመምረጥ ከኳስ ውጪ በተደራጀ መልኩ ለመከላከል ጥረት ያደረጉት ጅማ አባ ጅፋሮች ለቅዱስ ጊዮርጊሶች ኳሱን እንዲቆጣጠሩ ቢፈቅዱላቸውም ጊዮርጊሶች በትዕግሥት ይህን አወቃቀር ለማስከፈት መቸገራቸውን ተከትሎ በቀጥተኛ እና ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች ብቻ ጥቃቶችን እንዲፈፅሙ ማስገደድ ችለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ 52ኛው ደቂቃ አንስቶ ግብ ጠባቂያቸው አላዛር ማርቆስን በቀይ ካርድ አጥተው እንዲሁም አንድ ግብ አስተናገድው የነበረ ቢሆንም በአጋማሹ በጎዶሎ እየተጫወቱ እንኳን ሜዳ ላይ ያሳዩት የነበረው ትጋት እና ውጤቱን ለመለወጥ የነበራቸው ፍላጎት እጅግ የሚደንቅ ነበር። በጨዋታ በጥቅሉ ዒላማውን በጠበቀ ሙከራ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ጅማዎች በሁለቱም አጋማሾች ለግብ የቀረቡባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ።

ወሳኝ ምዕራፍ ላይ በሚገኘው የሊጉ ውድድር ምንም እንኳን አስፈላጊው ነገር ነጥቦችን ማሳካት ቢሆንም ጅማ አባ ጅፋሮች በርቀት ሊጉን እየመራ ከሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያሳዩት ተጋድሎ ግን አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲወጡ የሚያደርግ ነበር።

ያጋሩ