ከነገው ወሳኝ ጨዋታ በፊት መግለጫ ተሰጥቷል

አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ የነገውን ጨዋታ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በሕንድ አስተናጋጅነት ለሚደረገው ከ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታውን ነገ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከናይጄርያ አቻው ጋር የመጀመርያ ጨዋታውን ከማድረጉ አስቀድሞ አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ እና የቴክኒክ ዳሬክተሩ አቶ ቴዎድሮስ በተገኙበት ወሎ ሠፈር በሚገኘው የፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ጥቂት የየሚዲያ አካላት በታደሙበት በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ብሔራዊ ቡድኑ ከዩጋንዳ እና ደቡብ አፍሪካ ጨዋታ በኋላ ሚያዚያ 25 ጀምሮ በአዲስ አበባ በነበረውን የዝግጅት በአንዳንድ ክፍተቶች ላይ ለማስተካከል ጠንክረው እየሰሩ እንደነበር እና ሁሉም ተጫዋቾች ለነገው ጨዋታ ጤነኛ መሆናቸውን እንዲሁም በጥሩ መነቃቃት ላይ እንደሚገኙ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማስከተል ከጋዜጠኞች ጥቂት ጥያቄዎች ለሁለቱም አካላት የቀረበላቸው ሲሆን የተነሱ ጥያቄዎች እና ምላሾቻቸው እንዲህ ቀርበዋል።

ስለተጋጣሚያቸው ናይጄሪያ ጥንካሬ እንዲሁም ወቅታዊ መረጃ ምን ያህል አላቹሁ ?

“ናይጄሪያ ሁሉንም ጨዋታ በማሸነፍ ነው ከእኛ ጋር የደረሰው። እኛ ስንሰራ የቆየነው መጀመርያ ለዩጋንዳ ቀጥሎ ለደቡብ አፍሪካ አሁን ደግሞ ለመጨረሻው ምዕራፍ ለናይጄሪያ ጨዋታ ነው። ለነገው ጨዋታ በፊት ከነበረብን ነገር በመነሳት ራሳችንን እያዘጋጀን ቆይተናል። እውነት ነው ናይጄሪያ በሁሉም የዕድሜ እርከን በቀላሉ ለዓለም ዋንጫ የሚያልፍ እና የሚበላ ቡድን ነው። እኛም እንዴት ነው ጠንካራ መሆን ያለብን ፣ የምንገጥመው ቡድን ጠንካራ ቢሆንም እኛ ጠንካራ መሆኑን ችለን የምናሸንፈው ብለን ስንዘጋጅ ቆይተናል። የናይጄሪያ ቡድን ጨዋታ ልናይ አልቻልንም። ለማግኘትም ብዙ ሞክረናል ግን ልናገኝ አልቻልንም። ባየነው ጥቂት ነገር በመነሳት በራሳችን ቡድን ላይ ሰርተናል።

በደቡብ አፍሪካው የመልስ ጨዋታ ላይ በእንቅስቃሴም በሌሎች መለኪያ ብልጫ ተወስዶብን ነበር ምክንያቱ ምን ነበር ?
“ደቡብ አፍሪካ ላይ በነበረው ጨዋታ ጠንካራ ነበርን። በሜዳችን የምንጫወት ነበር የምንመስለው። እዚህ ከመጣን በኋላ በዩጋንዳውም በደቡብ አፍሪካ ጨዋታ ልክ አልነበርንም። እኛም ችግሩ ምድነው በማለት ብዙ ስንነጋገር ነበር። ልምምድ ላይ የምንሰጣቸው እና ሜዳ ላይ የሚተገብሩት ልክ ያልሆነ ነበር። ለምን ብለን ስናስብ ከጉጉት የተነሳ እዛ ያመጡት ውጤት ጥሩ ስለነበር አስጠብቀው ለመውጣት ሲያስቡ ያልሆነ ረጃጅም ኳስ እየተጫወቱ ነበር። ይህ ድክመት አለብን ፤ በዚህ ላይ ጠንክረን እየሰራን ነው።

መሐል ሜዳ ላይ ኳስ የሚያደራጁ ተጫዋቾች ክፍተት ነበር። በነገው ጨዋታ ተስተካክሏል ?

“መሐል ላይ ክፍተቶች ነበሩ። በዚህ ቦታ ላይ ያለ ተፈጥሯዊ ቦታቸው ያልሆኑ ተጫዋቾች ተጠቅመናል። ተፈጥሯዊ ክህሎት ያላቸው ተጫዋቾች ባለማግኘታችን ምክንያት ነበር። አሁን ግን በተቻለ አቅም ንጋት እና ቤቴልሔም የሚባሉ ልጆች ጨምረናል ። ጥሩ ከቡድኑ ጋር እየተዋሀዱ ነው ፤ ነገም ላይ ጥሩ ሥራ ይሰሩልናል ብለን እናስባለን። ነገ በሜዳችን ናይጄሪያን በማሸነፍ እንጀምራለን ።”

አስተዳደራዊን እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ አቶ ቴዎድሮስ ፍራንኮ ተከታዮን ምላሽ አጋርተዋል።

“ናይጄሪያ ትልቅ ቡድን ነው፣ ሲባል እኛንም ማየት ያስፈልጋል። እንደ ሀገር ምስራቅ አፍሪካ ላይ ከ20 እና ከ17 ዓመት በታች ቡድን የበላይነት እየወሰድን ነው። ይሄም ቢሆን ክፍተቶች አሉ ለምሳሌ በሜዳ የሚደረግ ጨዋታን መጠቀም፣ የኳስ ፓተርናችን፣ የኳስ ንክኪያችን እዚህ ላይ ማስተካከል አለብን። እናሸንፋለን ስንል ሳንሰራ አይደለም። ያልሰራናቸው ነገሮች አሉ፣ ግን ናይጄሪያ ትልቅ ቡድን ነው እያልን ልጆቹን ተፅዕኖ ውስጥ እንዳንከት፣ ፈርተው እንዲገቡ ባናደርግ ጥሩ ነው።

“የስታዲየሙ አንድ አራተኛ እስከ ስድስት ሺህ ተመልካች መግቢያ በነፃ እንዲገባ ይደረጋል። ሀገሩን የሚወድ ማንኛውም ሰው መጥቶ እንዲደግፍ እንደ ፌዴሬሽን ጥሪ እናቀርባለን።

“ማበረታቻ ሽልማት በእያንዳንዱ ጨዋታ አላቸው። ግን ዕድሜን መሠረት ያደረገ መሆን አለበት። ጫፍ ላይ ሲደርሱ አንሸልማለን በማለት ልጆቹን የማይሆን ነገር እንዳንከታቸው ያስፈልጋል። ከጨዋታው ይልቅ ትኩረታቸው ስለ ሽልማቱ ማሰብ እንዳይሆን። ይሄን ከልጆቹ ጋር ተነጋግረናል፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴሪም ፌዴሬሽኑም ሽልማት የሚያደርግ ቢሆንም ለጊዜው እንዳይገለፅ ነው የተፈለገው። በአጠቃላይ ልጆቹን ጫና ውስጥ የማይከት ትኩረታቸው ጨዋታ ላይ ያደረጉ ስራዎችን ስንሰራ ቆይተናል።”