በሦስት ዳኞች ላይ ውሳኔ ተላልፏል

በወላይታ ድቻ እና በኢትዮጵያ ቡና ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ ዳኞች ከፕሪምየር ሊጉ ውድድር ተሸኝተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በሀድያ ሆሳዕና 1-0 መረታቱ ይታወሳል፡፡ ይህን ጨዋታ በዋና ዳኝነት የመሩት ፌዴራል ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ በተጫዋቾች ላይ አላስፈላጊ ቃላትን ስለመጠቀማቸው ሪፖርት የቀረበባቸው ሲሆን ኢትዮጵያ ቡናም የቴክኒክ ክስ አስይዞ ነበር፡፡ ጉዳዩን የተመለከተው የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ዳኛው ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ከፕሪምየር ሊጉ ጨዋታዎች እንዲሸኙ ማድረጉን የሊጉ አክሲዮን ማህበር ይፋ አድርጓል፡፡

አነጋጋሪ በነበረው በሳምንቱ የማሳረጊያ ጨዋታ ወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና የተገናኙበት ጨዋታ በሲዳማ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ተበድያለሁ ያለው ወላይታ ድቻ ለአክስዩን ማህበሩ አቤቱታውን አቅርቧል። ክለቡ ባቀረባቸው ሁለት ክሶች ያልተገባ የፍፁም ቅጣት ምት እንደተሰጠበት እንዲሁም ያገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ደግሞ የሲዳማ ቡናው ግብ ጠባቂ መስመሩን ለቆ እንዳዳነበት በመግለፅ የዕለቱን ዳኞች ተጠያቂ አድርጎ ነበር። የሊጉ አክሲዮን ማህበር ይፋ እንዳደረገው ክሱን የተመለከተው የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ጨዋታውን መርተው የነበሩት ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ለሚ ንጉሴ እና ረዳት ሳኛ አብዱ ይጥና የዚህን ዓመት ቀጣይ ጨዋታዎች እንዳይመሩ በሚል ከውድድሩ አሰናብቷል፡፡

ያጋሩ