ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

በሦስተኛው የሳምንቱ የዓበይት ጉዳይ ፅሁፋችን አሰልጣኞች ላይ ያተኮሩ ሀሳቦች ተዳሰውበታል።

👉 ፋሲል ተካልኝ እና አዳማ ተለያይተዋል

በክረምቱ አዳማ ከተማን የተረከበው ፋሲል ተካልኝ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ በቀድሞ ክለቡ ባህር ዳር ከተማ መሸነፉን ተከትሎ በተደረገ አስቸኳይ ስብስባ ከክለቡ ጋር በስምምነት ተለያይቷል።

በዝውውር መስኮቱ በጥሩ ምልመላ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ በመቀላቀል አምና ፍፁም ደካማ የውድድር ዘመን ያሳለፈውን ቡድን በተሻለ መንፈስ ተፎካካሪ የማድረግ ውጥን ይዞ የጀመረው አዳማ ከተማ መልካም የሚባሉ ጊዜያትን ቢያሳልፍም በሂደት ግን ሳይጠበቅ ከወራጅ ቀጠናው በቅርብ ርቀት ተገኝቷል።

ለወጣቱ አሰልጣኝ ፋሲል ትካልኝ በዋና አሰልጣኝነት ሁለተኛው በነበረው የአዳማ ከተማ ሥራ ምንም እንኳን ቡድኑ ሜዳ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴን የሚያደርግ ቢሆንም ግቦችን እያስቆጠረ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ግን ተቸግሮ ተስተውሏል። በዚህም ካደረጋቸው 24 ጨዋታዎች በ15 ጨዋታዎች አቻ ሲለያይ ይህም አሰልጣኙን በተደጋጋሚ ጫና ውስጥ እንዲገባ ምክንያት ሲሆን ተመልክተናል።

በመሆኑም ከቀጣዩ የጨዋታ ሳምንት አንስቶ በሚኖሩ ጨዋታዎች የፋሲል ተካልኝ ረዳት በመሆን ሲያገለግል የነበረው እና የቀድሞው የአዳማ ከተማ ድንቅ አማካይ ይታገሱ እንዳለ በቀጣይ አዳማን የሚመራ ይሆናል። በደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ቅቡልነት ያለው ይታገሱ እንዳለ ከዚህ ቀደም በአዳማ የዕድሜ እርከን ቡድኖች በማሰልጠን አሳልፏል። አሰልጣኙ ሳይጠበቅ ወደ ሰንጠረዡ ግርጌ ያሽቆለቆለውን ቡድን ከፍ የማድረግ ኃላፊነት የሚጠብቀው ይሆናል።

👉 የሙሉጌታ ምህረት ተምሳሌታዊ ንግግር

ሀዲያ ሆሳዕና ኢትዮጵያ ቡናን ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ከሱፐር ስፖርት ጋር ቆይታ ያደረገው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን ደጋግሞ ስለማሸነፉ የቀረበለትን ጥያቄ ሲመልስ እንዲህ ብሏል።

“በእርግጥ አራት ጊዜ ስታሸንፍ ያለ ምንም ቀመር አይሆንም። ሜዳ ለይ እንደ አሰልጣኝ የእርሱን ቡድን ብቻ ሳይሆን የሌሎቹንም እያየው ነው ልዘጋጅ የምችለው። ግን አራት ጊዜ ባሸንፈውም ካሳዬን እበልጣለው ማለት አይደለም። ሜዳው እና ጨዋታው የሚፈቅደውን ስለሆነ ማሸነፍ ስላለብን ተዘጋጅተን እንመጣለን እንጂ ሌላ የተለየ ነገር የለውም። በነገራችን ላይ የካሳዬ አጨዋወት ለኔ ብቻ ሳይሆን ለሁላችንም ምሳሌ ሊሆን የሚችል በመሆኑ በጣም ደሰ ይለኛል።” የሚል ሀሳብ ሰጥቷል።

በሙሉጌታ ንግግር ውስጥ ሁለቱ ዓበይት ሀሳቦች “ማክበር እና ማድነቅ” ናቸው። ይህ ደግሞ የእግርኳሳችን መዝገበ ቃላት ላይ የሌሉ መሰረታዊ ሀሳቦች ናቸው። በእግርኳሳችን በትንሽ ስኬቶች የመታበይ እና ከእኛ ውጪ ወደ ውጪ የሚሉ ለሌሎች ዝቅተኛ ግምት የመስጠት አባዜ ፀሀይ የሞቀው ሀቅ ነው። በዚህ ሂደት አንዱ አንዱን በማንኳሰስ ከመመልከት ባለፈ በይፋ አክብሮት ሲሰጥ እምብዛም አንመለከትም።

ሙሉጌታ ምህረት ግን ለሙያ አጋሩ ካሳዬ ክብር በመስጠት እና ራሱን ዝቅ በማድረግ መልካም ስብዕናውን ዳግም አስመስክሯል። ይህንን መመልከታችን በቀጣይ ዓመታት እግርኳሱን ሊቆጣጠሩ በሚችሉ ወጣት አሰልጣኞች መሀል ጥሩ የመከባበር ስሜት እያደገ እንደሚሄድ ተስፋ የሰጠ ነበር።

👉 ሥልጠናችን እስከምን ድረስ ?

ሁሌም ቢሆን ከጨዋታዎች መጠናቀቅ በኋላ በሚኖሩ ድህረ ጨዋታ አስተያየቶች ላይ አሰልጣኞች በጨዋታው የተመለከቷቸውን አጠቃላይ የቡድን ግምገማቸውን ሲያቀርቡ እንሰማለን። ታድያ በዚህ ሂደት ከሚነሱ ጉዳዮች አንዱ ቡድናቸው ላይ የተመለከቷቸው ድክመቶች ይጠቀሳሉ።

ምናልባት እነዚህን አስያየቶች ለተከታተለ በተደጋጋሚ የሚነሱ ሀሳቦች ውስጥ በአሰልጣኞች እንደ ድክመት የሚቀርቡ ሀሳቦች ከጨዋታ ጨዋታ የመመሳሰላቸው ጉዳይ ትኩረትን ይስባል። በአሰልጣኞቹ ሀሳብ ውስጥ በቀጣይ ጨዋታዎች ድክመቱን በተመለከተ ለማሻሻል ስራዎች እንደሚሰሩ ጠቆም አድርገው የማለፍ ነገር የተለመደ ቢሆንም በእውን ግን እነዚህ ችግሮች ሲቀረፉ እምብዛም አንመለከትም። ጥያቄው የሚመጣውም እዚህ ጋር ነው። ችግሮቹ ታውቀው ለማሻሻል ጥረት እንደሚደረግ ከተነገረ በኋላ ችግሮቹ ላይ ለውጥ መመልከት ያለመቻላችን ጉዳይ ከምን የሚመነጭ ይሆናል ? በመሰረታዊነት ለዚህ ጉዳይ በምክንያትነት ማቅረብ የሚቻለው ሁለት ዓበይት ጉዳዮችን ነው። እርግጥ ድርሻው ቢለያይም እነዚህ ጉዳዮች የራሳቸው አስተዋጽኦ እንዳላቸው እሙን ነው።

አንደኛው እና ቀዳሚው ጉዳይ ከአሰልጣኞች እና ሥልጠና ጋር የሚያያዝ ነው። ይህም አሰልጣኞቻችን የቡድናቸውን ነባራዊ ሁኔታ በግልፅ በመረዳት ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ የሚረዱ ሥልጠናዎችን በመንደፍ እና እነዚሁን ወደ ሜዳ ለማውረድ የሚደረጉት ጥረቶች አነስተኛ የመሆን ጉዳይ ነው። ሌላው ጉዳይ ከተጫዋቾች ሥልጠናዎችን የመገንዘብ እና ተግባራዊ የማድረግ አቅም ጋር የሚያያዝ ነው።

ለቡድኖች ድክመት አለመሻሻል ተጫዋቾች ተጠያቂነት የለባቸውም ማለት ሳይሆን ድክመቶቹ ሳይቀረፉ በቆዩ እና ውጤት በጠፋ ሰዓት የመጀመሪያው በትር የሚያርፈው አሰልጣኞች ላይ ከመሆኑ አኳያ ክፍተቶችን የማስተካከል ኃላፊነቱ ወደእነሱ ማመዘኑ የማይቀር ነው። በቡድኑ ውስጥ ያለውን ክፍተት ራሳቸው በይፋ ሲናገሩ መደመጣቸውም ደግሞ ነገም ስላለመሻሻሉ ቀዳሚ ተወቃሽ ለመሆን የሚያበቃቸውም ነው። በመሆኑም አሰልጣኞቻችን በእነሱ በኩል ያለውን ክፍተት ለመሙላት ራሳቸውን ተራማጅ እና ብቁ አሰልጣኝ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በየጨዋታ ሳምንቱ የሚያነሷቸውን ችግሮች ቀርፈው ቡድናቸውን ወደ ውጤት በመምራት ማሳየት በስራቸው ላይ ለመዝለቅ ጭምር ወሳኝ እንደሆነ ይታመናል።

👉 ወንድማገኝ ተሾመ የመጀመሪያ ጨዋታውን መርቷል

በ23ኛ የጨዋታ ሳምንት በመከላከያ ያልተጠበቀ ሽንፈት ያስተናዱት ሲዳማ ቡናዎች ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ጋር መለያየታቸው ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ የገብረመድህን ረዳት በመሆን ሲያገለግል የነበረው የቀድሞው የቡድኑ የዕድሜ እርከን አሰልጣኝ የነበረው ወንድማገኝ ኃይሉ ኃላፊነቱን የተረከበ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታውን በኃላፊነት በመራበት ጨዋታ ቡድኑ ወደ ድል ተመልሷል።

አሰልጣኙ በጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ በነበረው መርሐግብር ወላይታ ድቻን በአወዛጋቢ መንገድ በተገኘች የፍፁም ቅጣት ምት ግብ በማሸነፍ በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታውን በድል ጀምሯል።

ያጋሩ