“ዕድል ከእኛ ጋር ስላልሆነ ልንሸነፍ ችለናል” አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በናይጄሪያ 1-0 ከተሸነፈበት ጨዋታ በኋላ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አስተያየት ሰጥተዋል።

ወደ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ የመጨረሻ የማጣሪያ መርሐ-ግብር የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ከናይጄሪያ ጋር በአበበ ቢቂላ ስታዲየም አድርጎ 1-0 ከተሸነፈ በኋላ የቡድኑ አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ ይህንን ብለዋል።

ስለሽንፈቱ

“የእኛ ቡድን ደካማ አልነበረም፡፡ ናይጄሪያም ጠንካራ ቡድን ነው፡፡ በሰራነው ስህተት ነው ፣ ጎል ሊገባብን የቻለው፡፡ እኛም የቻልነውን አድርገን ተጫውተናል፣ ከባለፉት ጨዋታዎች በሜዳችን የተሻለ ነበርን።፡ ዕድል ከእኛ ጋር ስላልሆነ ፣ ልንሸነፍ ችለናል፡፡

ስለረጃጅም ኳስ አጨዋወት

“አንዳንዴ ስህተቶች ለማሸነፍ ስትጥር ይፈጠራሉ፡፡ ከእዛ የተፈጠረ ነው እንጂ ፣ ስህተቱ ልምምድ ላይ ተረጋግተው እየተጫወቱ የነበረው፡፡ ዛሬም ጨዋታው የሚያስከፋ አይደለም። ጥሩ ነበር ግን አልተሳካልንም፡፡

ስለናይጄሪያ ቀጣይ ጨዋታ

“በሜዳቸው ነው የምንጫወተው ጠንካራ እንደሆኑ አይተናል፡፡ ግን እኛ ከሜዳ ውጪ የተሻለ ውጤት አለን፣ እዛ ውጤቱን ቀይረን ፣ ለመምጣት ጥረት እናደርጋለን፡፡ በእርግጠኝነት እግዚአብሔር ይረዳናል ይሄንን ለማድረግ ብዙ እንሰራለን፡፡

ስለሚቆራረጡ ኳሶች

“አሁን ያሉትን ችግሮች በሙሉ ለማስተካከል እንሞክራለን፡፡ ክፍተቶችም አሉ ፣ ሙሉ በሙሉ የእኛ ቡድን የተሻለ ነው ብዬ አይደለም። ለዛም ነው ያላሸነፍነው። ግን ኳስ በትክክል እንዲደርስ መሐል ላይ በበለጠ ሰርተን ተቀናጅተው እንዲገኙ የቻልነውን ነገር እናደርጋለን፡፡