ሊጉ ለብሔራዊ ቡድን ዝግጅት እና ጨዋታዎች ከመቋረጡ በፊት የሚደረጉት የጨዋታ ሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ፍልሚያዎች እንዲህ ተዳሰዋል።
አዲስ አበባ ከተማ ከ ጅማ አባ ጅፋር
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ የሚገኙት አዲስ አበባ እና ጅማ ነገ እርስ በእርስ የሚያደርጉት ጨዋታ ትርጉሙ ብዙ ነው። ያለፉትን ስድስት ጨዋታዎች ተመሳሳይ የአቻ ውጤት ያስመዘገበው አዲስ አበባ ከተማ ከናፈቀው ድል ጋር ታርቆ ከአስጊው ቀጠና ለመውጣት የሚያደርገውን ሩጫ ያፋጥናል ተብሎ ሲገመት ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ ከሁለት ተከታታይ ድሎች በኋላ ካጋጠሙት ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በማገገም ነጥቡን ሀያዎቹ ውስጥ ለመክተት እንደሚጥር ይታሰባል።
ውጤት የማስጠበቅ ስር የሰደደ ችግር ያለበት አዲስ አበባ ከተማ ባሳለፍነውም ሳምንት ሙሉ ለሙሉ በራሱ ጥፋት ማለት እስከሚያስችል ድረስ በእጁ የገባውን ሦስት ነጥብ ባለቀ ሰዓት ጥሏል። ቡድኑ በጨዋታው በተሻለ የግብ ልዩነት ማሸነፍ የሚችልበት ሁነት ቢፈጠርም ይህ ሳይሆን ቀርቶ ባለቀ ሰዓት እጅ ሰጥቷል። ባሳለፍነው ሳምንት ብቻ ሳይሆን ቡድኑ ካደረጋቸው 24 ጨዋታዎች በዘጠኙ ቀድሞ መምራት እየቻለ ማግኘት ከሚገባው 27 ነጥብ ሀያውን መጣሉ ችግሩ ምን ያህል ስር የሰደደ እንደሆነ ይጠቁማል። ጨዋታን ከመቆጣጠር ጋር ተያይዞ የሚመጣው ይህ ክፍተት በተደጋጋሚ መከሰቱ አግራሞትን የሚጭር ቢሆንም የቡድኑ እንቅስቃሴ መጥፎ አለመሆኑ ግን አሁንም በቀጣዩ ጨዋታ ተስፋ እንዲኖር ያደርጋል። ከድሬዳዋ ጋር በተደረገው ጨዋታ በብዙ መስፈርቶች ጥሩ የነበረው ቡድኑ ነገም የሀይል ሚዛኑን ወደ ራሱ በማምጣት እንደሚንቀሳቀስ ይገመታል። ይህ ቢሆንም ጅማም ኳስን ለመቆጣጠር የሚሻ ስለሆነ መሐል ሜዳው ላይ የሚኖረው ፍልሚያ ምናልባት ጨዋታውን ሊወስን ይችላል። ከዚህ ውጪ ከሰበታ በመቀጠል ብዙ ግቦችን ያስተናገደው የጅማ የተከላካይ ክፍል የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ሪችሞንድ አዶንጎ እና ፈጣኖቹ የመስመር አጥቂዎች ሊፈትኑን እንደሚችል ይጠበቃል።
ምክትል አሠልጣኙን ጊዜያዊ አድርጎ ከሾመ በኋላ ሁለት ተከታታይ ድሎችን ያስመዘገበው ጅማ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ግን በሊጉ አናት እና ግርጌ በሚገኙት ሰበታ እና ጊዮርጊስ ተረቷል። በሁለቱም ጨዋታዎች ለትችት የሚዳርገው እንቅስቃሴ ባያደርግም ውጤት አላገኘም። ሊጉ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደመገኘቱ መጠን እና ቡድኑ ካለበት ደረጃ መነሻነት ጥሩ በሆኑበት አይደለም ጥሩ ባልተንቀሳቀሱበት ጨዋታም ድሎች እጅግ ወሳኝ ስለሆኑ ቡድኑ እንቅስቃሴውን በውጤት ማሳጀብ ይገባዋል። ይህ ቢሆንም በቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ የግብ ዘባቸው በቀይ ካርድ ወጥቶ አንድ ለምንም እየተመሩ ከጨዋታው አንዳች ነገር ይዞ ለመውጣት ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ ነበር። የሆነው ሆኖ ከኳስ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ሲሞክር የሚታየው ቡድኑ ነገም በዚሁ ፍላጎቱ እንደሚጫወት የሚገመት ሲሆን ከላይ እንደገለፅነው የአማካይ መስመሩን መቆጣጠር የጨዋታው ወሳኙ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ፈጣኖቹን አጥቂዎች ያማከለ ሽግግር የሚያደርገው ጅማ በተቃራኒው ሚዛንን የመጠበቅ ክፍተት ላለበት የአዲስ አበባ ቡድን የሜዳ ላይ ስራን ሊያበዛ ይችላል። ከምንም በላይ በጣምራ የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆኑት እዮብ እና መሐመድኑር አዲስ አበባዎች ትኩረት ሊያረጉባቸው የሚገቡ ተጫዋቾች ናቸው።
አዲስ አበባ ከተማ ወሳኝ ተከላካዮቹ ዘሪሁን አንሼቦ፣ ሳሙኤል አስፈሪ እና ቴዎድሮስ ሀሙን በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ ሲያጣ የአጥቂው ፍፁም ጥላሁን መሰለፍም አጠራጣሪ ነው ተብሏል። ጅማ አባ ጅፋር በበኩሉ በቅጣት ተስፋዬ መላኩ፣ አላዛር ማርቆስ እና ሽመልስ ተገኝን በጉዳንት ደግሞ አድናን ረሻድ እና ቦና ዓሊን ግልጋሎት የማያገኝ ሲሆን ቀላል ጉዳት ያስተናገደው አስጨናቂ ፀጋዬም መግባቱ አጠራጣሪ እንደሆነ ተነግሮናል።
4 ሰዓት በሚጀምረው ጨዋታ ምስጋናው መላኩ በመሐል ማንደፍሮ አበበ እና አያሌው አሰፋ የመስመር ተስፋዬ ጉርሙ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሲሆኑ ሰለሞን ተስፋዬ እና ተከተል በቀለ የጎል አጠገብ ረዳቶች ሆነው ተመድበዋል።
እርስ በርስ ግንኙነት
– አዲስ አበባ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር በሊጉ ለሁለተኛ ጊዜ ነገ ይገናኛሉ። በመጀመርያው ዙር ጅማ 1-0 ማሸነፉም ይታወሳል።
ግምታዊ አሰላለፍ
አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)
ዳንኤል ተሾመ
አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ልመነህ ታደሠ – አዩብ በቀታ – ሮቤል ግርማ
ሙሉቀን አዲሱ – ቻርለስ ሩባኑ – ኤሊያስ አህመድ
እንዳለ ከበደ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ፍፁም ጥላሁን
ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)
ለይኩን ነጋሽ
በላይ አባይነህ – ኢያሱ ለገሠ – የአብስራ ተስፋዬ – ወንድማገኝ ማርቆስ
ሱራፌል ዐወል – መስዑድ መሐመድ – ዳዊት እስቲፋኖስ
ዱላ ሙላቱ – መሐመድኑር ናስር – እዮብ አለማየሁ
ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና
በሁለት ነጥብ እና አንድ ደረጃ ተበላልጠው አምስተኛ እና ስድስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና በተለያየ የጨዋታ መንገድ ጥሩ ፉክክር የሚታይበት ፍልሚያ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዋንጫ ፉክክሩ ቀስ በቀስ ራሱን እያራቀ የመጣው ሀዋሳ ከተማ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ሦስት ነጥብ አግኝቶ በጊዜያዊነትም ቢሆን ወደ ሦስተኛ ደረጃ ከፍ ለማለት የነገውን ጨዋታ ሲፈልገው ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ከሁለት ጣፋጭ ድሎች በኋላ በሀዲያ ሆሳዕና ከደረሰበት ሽንፈት ለማገገም እና ደረጃውን ለማሳደግ ጠንክሮ እንደሚቀርብ ይታመናል።
በሁለተኛው ዙር የሊጉ ውድድር እጅግ የተዳከመው ሀዋሳ ከተማ ብዙ ጠንካራ ጎኖቹ ከድተውት ይገኛል። በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ እምብዛም እንከን የሌለበት ቡድኑ ባለፉት ጥቂት ፍልሚያዎች ጨዋታዎችን የሚቀርብበት እና የሚከውንበት መንገድ ብዙ ስህተቶች ያሉበት ነው። እርግጥ በጉዳት እና ቅጣት ምክንያት በአራቱም የመጫወቻ ክፍሎች ወሳኝ ተጫዋቾችን ማጣቱ ለመዳከሙ ትልቁን ድርሻ ቢወስድም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች በአንፃራዊነት ቀለል ያሉ ተጋጣሚዎችን አግኝቶ ውጤት አለማግኘቱ ግን የሚያስተቸው ነው። በአርባምንጭ ሁለት ለአንድ ሲረቱ ደግሞ በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች የነበራቸው ድክመት ዋጋ አስከፍሏቸዋል። ከኋላ ተሻጋሪ ኳሶችን ለመመከት የሚያስችል የቦታ፣ ሰው እና ጊዜ አጠባበቅ ስህተቶች ሲስተዋሉ ከፊት ደግሞ አጋጣሚዎችን የመጠቀም ድክመት ነበር። በነገው ጨዋታ ቡድኑ ከነበረበት በዛ ያለ ጉዳት ከወገብ በታች የሚሰለፉትን ወሳኝ ተጫዋቾች ማግኘቱ በታችኛው ሜዳ የተሸነቆረውን ነገር እንደሚያስተካክል ይታመናል። ይህ የመከላከል መዋቅር ከተስተካከለ ደግሞ ከፊት ያለውም አጨዋወት እንደሚመጣ እና ከኳስ ውጪ ባለ አደረጃጀት የሚታማውን ቡናን እንደሚያስጨንቅ ይገመታል።
ከሁለተኛው የደረጃ ሰንጠረዥ ግልባጭ ወደ ቀዳሚው ቀስ በቀስ የመጣው ኢትዮጵያ ቡና ባሳለፍነው ሳምንት በሀዲያ ሆሳዕና የአንድ ለምንም ሽንፈት አስተናግዷል። ከእርሱ ጨዋታ በፊት እየተመራ ተከታታይ ድል አግኝቶ የነበረው ቡድኑ በሀዲያው ጨዋታ በመጠኑ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግሮ ነበር። በተለይ ሀዲያ ሆሳዕና ከኳስ ውጪ በቁጥር በርከት ብሎ ወደ ኋላ በመውረድ ክፍተቶችን ለመዝጋት ያደረገውን ጥረት ፉርሽ ማድረግ ተስኖት ነበር። የነገው ተጋጣሚ ሀዋሳ ከተማም ከኳስ ውጪ ዘለግ ያለውን ጊዜ ለማሳለፍ የሚሞክር ቡድን ስለሆነ የባለፈው ፈተና መልሶ መደገሙ አይቀርም። በዚህ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ክፍተት ላይ ደግሞ ቡድኑ ላይ ያለው የቅጣት ዜና ነገሩን በእንቅርት ላይ ያደርገዋል። ዋነኛ የቡድኑ የማጥቃት መሐከል የሆነው አቡበከር ናስር እና ዊሊያም ሰለሞን ነገ አይኖሩም። ይህ ትልቅ ማጣት እና ከፊት መሳሳት የሚያስከትል ቢሆንም ቡድኑ ባለው አማራጭ የሀሳብ ለውጥ ሳያደርግ ኳሱን በመያዝ በትዕግስት ለማጥቃት እንደሚውተረተር ይጠበቃል። ከዚህ ውጪ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦችን ያስተናገደው የኋላ መስመርም ተጠናክሮ መቅረብ ይገባዋል። በዋናነት ግን የተጋጣሚን ሜዳ ለጥጦ መጫወት እና ክፍተቶችን ማግኘት የሚያዘወትረው ቡድኑ ነገም በዚሁ አካሄድ የሀዋሳን ጠጣር የኋላ መስመር ለማስከፈት እንደሚጥር ይጠበቃል።
ሀዋሳ ከተማ ከነበሩበት ስድስት ጉዳቶች አራቱን ነገ ያገኛል። በዚህም ላውረንስ ላርቴ፣ ፀጋአብ ዮሐንስ፣ ዳዊት ታደሠ እና በቃሉ ገነነ ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸው ሲጠቆም ፀጋሰው ድማሙ እና መስፍን ታፈሠ ግን አሁንም እንዳላገገሙ ሰምተናል። ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ በቅጣት አቡበከር ናስር እና ዊሊያም ሰለሞንን በጉዳት ደግሞ ወንድሜነህ ደረጀ፣ ኃይሌ ገብረትንሣኤ እና ቴዎድሮስ በቀለን አያገኝም።
ይህንን ጨዋታ እያሱ ፈንቴ ከረዳቶቻቸው ድሪባ ቀነኒሳ እና ሸዋንግዛው ይልማ አራተኛ ዳኛው አለማየሁ ለገሰ እንዲሁም የጎል አጠገብ ረዳቶች ከሆኑት ካሣሁን ፍፁም እና ኤፍሬም ኃይለማርያም ጋር ይመሩታል።
እርስ በርስ ግንኙነት
– ከሊጉ ጅማሮ አንስቶ እስካሁን ያሉት ሁለቱ ክለቦች የሊጉ ከፍተኛው የግንኙነት ቁጥር ያላቸው ሲሆን 45 ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ 15 ሲያሸንፍ ቡና 14 አሸንፏል። በ16 አጋጣሚዎች አቻ ተለያይተዋል።
– በጨዋታዎቹ ኢትዮጵያ ቡና 52 ጊዜ ኳስ እና መረብን በማገናኘት የበላይ ሲሆን ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ሦስት የፎርፌ ግቦችን ጨምሮ 47 ግቦችን ማስመዝገብ ችሏል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሀዋሳ ከተማ (3-4-3)
ዳግም ተፈራ
ላውረንስ ላርቴ – ፀጋሰው ድማሙ – አዲስዓለም ተስፋዬ
ዳንኤል ደርቤ – ወንድምአገኝ ኃይሉ – በቃሉ ገነነ – መድኃኔ ብርሀኔ
ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ – ተባረክ ሄፋሞ
ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)
በረከት አማረ
አስራት ቱንጆ – አበበ ጥላሁን – ገዛኸኝ ደሳለኝ – ያብቃል ፈረጃ
አማኑኤል ዮሐንስ – አብነት ደምሴ – ታፈሠ ሰለሞን
አቤል እንዳለ – እንዳለ ደባልቄ – ተመስገን ገብረኪዳን