ሪፖርት | አዲስ አበባ አሁንም መሪነቱን ማስጠበቅ ሳይችል ቀርቷል

በ25ኛ የጨዋታ ሳምንት የመክፈቻ በነበረው መርሐግብር አዲስ አበባ ከተማ ለአምስተኛ ተከታታይ ጨዋታ አስቀድሞ መምራት ቢችልም በመጨረሻ ባስተናገደው ግብ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ነጥብ ተጋርቷል።

አዲስ አበባ ከተማዎች በመጨረሻ ጨዋታቸው ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋራው ስብስብ ሦስት ለውጥ ሲያደርጉ በዚህም ሳሙኤል አስፈሪ ፣ ሙሉቀን አዲሱ እና ፍፁም ጥላሁንን አሳርፈው በምትካቸው ቢኒያም ጌታቸው ፣ ዋለልኝ ገብሬ እና አሰጋኸኝ ጴጥሮስን ተክተው ያስገቡ ሲሆን በአንፃሩ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተሸንፈው የመጡት ጅማ አባ ጅፋሮች ደግሞ ባደረጓቸው አራት ለውጦች አላዘር ማርቆስ ፣ ተስፋዬ መላኩ ፣ አስጨናቂ ፀጋዬ እና ቦና ዓሊ ወጥተው ለይኩን ነጋሽ ፣ ኢዳላሚን ናስር ፣ ሙሴ ከበላ እና እዮብ ዓለማየሁ ወደ መጀመሪያ ተመራጭነት በማምጣት የዛሬውን ጨዋታ አድርገዋል።

በሁለቱም ቡድኖች በኩል ፈጠን ባለ ማጥቃት የጀመረው ይመስል በነበረው አጋማሽ አዲስ አበባ ከተማዎች ፍፁም የበላይ የነበሩ ሲሆን በአመዛኙ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተደጋጋሚ አጥቅተው በመጫወት ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም እንደተለመደው መጠቀም ሳይችሉ የቀሩበት ነበር። ገና ከጅምሩ በፈጣን ቅብብሎች የጅማን ተከላካይ መፈተን የጀመሩት አዲስ አበባ ከተማዎች በ10ኛው ደቂቃ ላይ ከጥሩ የቅብብል ሂደት በኋላ የተገኘውን አጋጣሚ ቢኒያም ጌታቸው ከሳጥን ጠርዝ ወደ ግብ የላካት እና ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ በወጣችበት ኳስ የመጀመሪያውን አስቆጭ አጋጣሚ ፈጥረዋል።

በ17ኛው ደቂቃ በጨዋታው መሀል ሜዳ ላይ ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው አማካዩ ቻርልስ ሪባኑ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት በግቡ ቋሚ ወደ ውጭ ስትወጣበት በ22ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ከሳጥን ውጭ ያደረገው ግሩም ሙከራ በለይኩን ነጋሽ ግሩም ቅልጥፍና አድኖበታል። ምናልባት በአጋማሹ ከተፈጠሩ ዕድሎች ፍፁም አስቆጭ በነበረችው አጋጣሚ በ24ኛው ደቂቃ አዲስ አበባዎች በላይኛው የሜዳ ክፍል ከነጠቁት ኳስ ኤልያስ አህመድ ቢኒያም ጌታቸውን ከይኩን ነጋሽ ጋር 1-1 ቢያገነኛውም በማይታመን ሁኔታ አጋጣሚዋን አምክኗታል።

በአጋማሹ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ዱላ ሙላቱን ከተከላካይ ጀርባ ለማሮጥ ጥረት ከማድረግ ውጪ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ለማድረግ የተቸገሩት ጅማዎች ከውሃ ዕረፍት መልስ በተወሰነ መልኩ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት አድርገዋል በዚህም በተሻለ መልኩ በተጋጣሚ አጋማሽ በቁጥር በዝተው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ 52ኛው ደቂቃ ላይ ሪችሞንድ አዶንጎ ላይ የዓብስራ ሙሉጌታ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ኤልያስ አህመድ ተረጋግቶ በማስቆጠር አዲስ አበባ ከተማዎች ቀዳሚ በማድረግ ነበር አጋማሹ የጀመረው።

ከግቧ በኋላ ምንም እንኳን ተደጋጋሚ እድሎችን ባንመለከትም ጅማ አባ ጅፋሮች ይበልጥ ጫና ማሳደር የጀመሩበት ነበር ፤ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ሜዳ በገባው በላይ አባይነህ በተሰለፈበት የቀኝ መስመር በኩል ተደጋጋሚ ዕድሎችን ከተሻጋሪ ኳሶች ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል።

በ60ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር በላይ አባይነህ ያሻማውን ኳስ መሐመድኑር ናስር በግንባሩ ገጭቶ ያደረጋትን ግሩም ሙከራ ዳንኤል ተሾመ እንደምንም ያዳነበት ኳስ እንዲሁም በ69ኛው ደቂቃ ላይ ዱላ ሙላቱ ከሳጥን ጠርዝ በቀጥታ አክርሮ የመታው ኳስ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣችበት ኳስ አደገኛ ሙከራዎች ነበሩ።

በአንፃሩ ምንም እንኳን አውንታዊ ቅያሬዎችን በማድረግ ለመጫወት የሞከሩት አዲስ አበባዎች ምንም እንኳን በተወሰነ አጋጣሚዎች በመልሶ ማጥቃት አስፈሪ ቢመስሉም በአመዛኙ በጅማ አባ ጅፋሮች ጫና ወደ ራሳቸው አጋማሽ ለመሰብሰብ የተገደዱበት ነበር።

በ79ኛው ደቂቃ ሙሴ ካበላ ከሳጥን ውጪ የመታው ኳስ በልመንህ ታደሰ ሲመለስ ሳጥን ውስጥ በጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ዳዊት ፍቃዱ ያገኘውን ኳስ አስቆጠረ ሲባል የሰውነት ሚዛኑን መጠበቅ ባለመቻሉ ካመከነቸው አጋጣሚው በአምስት ደቂቃ ልዩነት ዳዊት ፍቃዱ ለግብ መቆጠር መንስኤ ሆኗል። በ84ኛው ደቂቃ መስዑድ መሀመድ ከተከላካይ ጀርባ ያደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ዳዊት ፍቃዱ ከግራ የሳጥን ጠርዝ ያሻማውን ኳስ መሀመድኑር ናስር በግንባሩ በመግጨት የጅማን የአቻነት ግብ አስቆጥሯል።

ከአቻነት ግቧ በኋላ ዳግም ወደ መሪነት ለመምጣት የሞከሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ዳግም መሪ መሆን የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎችን ፈጥረዋል በተለይም በ89ኛው ደቂቃ በሪችሞንድ አዶንጎ አማካኝነት ያገኙትን ዕድል አጥቂው አጋጣሚውን በሚገባ መጠቀም ሳይችል የቀረበት እና ሙከራውን ለይኩን ነጋሽ በቀላሉ የያዘበት አጋጣሚ እጅግ የሚያስቆጭ ነበር።

ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ አዲስ አበባ ከተማዎች በነበሩበት 14ኛ ደረጃ ላይ በ25 ነጥብ ሲረጉ በአንፃሩ ጅማ አባ ጅፋሮች ነጥባቸውን 20 አድረሰው ለጊዜውም ቢሆን ወደ 15ኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል።