የአሰልጣኞች አስተያየት | አዲስ አበባ ከተማ 1-1 ጅማ አባ ጅፋር

የረፋዱ የ25ኛ ሳምንት የመጀመርያ ጨዋታ በአንድ አቻ ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው – አዲስ አበባ

ስለጨዋታው

“የምንስታቸው ኳሶች እንደተጠበቀ ሆኖ ፤ አይሳት አይባልም። ጎል እየደረስን ነው የምንመለሰው። በሳል ተከላካይ ባለመኖሩ ባለው መጠቀም ነው። አጭር ጊዜ ስለሆነ አመጣጤ ፤ ተጫዋችም ለመተካት ጊዜው ስላልሆነ ባሉት ልጆች እንጫወታለን። ውጤት አስጠብቆ የሚወጣ ባለመኖሩ ባህር ዳር ያደረኳቸው ጨዋታዎች በሙሉ ዋጋ የሚያስከፍሉ እና የሚያስቆጩ ናቸው።

ስለማጥቃት ክፍተት

“እንግዲህ ኦዶንጎ ላይ ቢንያምን ደርበን ነው የምንጫወተው። በዚህ ሁለት ጨዋታዎች ምን ያህል እንደሳተ ቁጥሩን ማየት ነው። አሁን ባለው ልጅ መጠቀም ነው። እስከመጨረሻው አዲስ አበባን ለማትረፍ ትግል ማድረግ ነው። በአጠቃላይ ከጅማ ጨዋታ ብቻ ሳይሆን በቀጣይ የምናረጋቸው ጨዋታዎች ጎል ጋር እንደርሳለን አላስቆጠርንም ፤ የሚመጣውን ውጤት መጠበቅ ነው።

ስለቀጣይ ጨዋታ ዕቅድ

“ማጥቃቱ ራሱ መከላከል ስለሆነ ወደ መከላከሉ የማደላበት ምንም ምክንያት የለም። አጥቅቼ ነው የምጫወተው ፤ ተቃራኒ ሜዳ ኳስ እስካለ ድረስ ወደ እኛ ስለማይመጣ የተጎዱ ልጆች ከመጡ እንደምንም ጠጋግኜ ቡድኑን ለማትረፍ እስከመጨረሻው ዕታገላለው።”

አሰልጣኝ የሱፍ ዓሊ – ጅማ አባ ጅፋር

ስለጨዋታው

“መጀመርያው አጋማሽ በምንፈልገው መንገድ አላገኘነውም። በሁለተኛው ላይ ማስተካከል የሚገባንን አስተካክለን ወደ ሜዳ ገብተን በተሻለ ነገር በድግግሞሽ ወደ ጎል ብንደርስም ያገኘነውን ዕድል ባለመጠቀም ይሄን ውጤት ይዘን ወጥተናል።

ስለጨዋታቸው መንገድ

“በአራት ሦስት ሦስት ማጥቃት ላይ ነው። ሦስቱ አጥቂዎች ለመከላከል አይመጡም ነበር። መሐል ላይ ያሉ ልጆች በምንፈልገው መንገድ አልመጡም።

ስለግብጠባቂው ለይኩን

“ለይኩን የምንጠብቀው ነበር ፤ ሁለቱም ጥሩ ናቸው። እንዳውም የተሻለ ነገር ያመጣል በለን እንጠብቀዋለን። ትንሽ የፈራነው ጉዳት እንዳይመጣ እንጂ በሜዳ ላይ ጥሩ እንደሚሆን እርግጠኛ ነበርን።

ስለ ቀይ ምልክት

“አዎ ቁጥሮችን መቁጠር እንጀምራለን። እኛ ብናሸንፍ፣ እከሌ ቢሸነፍ በማለት። በፊት ማሸነፍ ብቻ ላይ ነበር ትኩረት የምናደርገው ፤ አሁን ደግሞ እኛ ስናሸንፍ ከእኛ ጋር የሚፎካከረው ቡድን እናስባለን። ከፈጣሪ ጋር ጥሩ ውጤት አምጥተን መጨረሻውን ማየት ነው።”