ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ወደ ድል ተመልሷል

በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ በግብ ቀዳሚ መሆን ቢችልም ኢትዮጵያ ቡና ከመመራት ተነስቶ 3-1 አሸንፏል።

በሀዋሳ ከተማዎች የግራ መስመር ጫና የጀመረው ጨዋታ እምብዛም ሳይቆይ በኢትዮጵያ ቡና ከፍ ያለ የኳስ ቁጥጥር ተተክቷል። ሀዋሳዎች በአመዛኙ ከኳስ ጀርባ ሆነው ለተጋጣሚያቸው ክፍተት ላለመስጠት በተንቀሳቀሱባቸው ደቂቃዎች ጨዋታው ተቀዛቅዞ ታይቷል። ቀዳሚው ሙከራም 17ኛው ደቂቃ ላይ የታየ ሲሆን ገዛኸኝ ደሳለኝ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ኳስ ዳግም ተፈራ በቅልጥፍና አድኖበታል።

የቡናዎች የኳስ ንክኪ በተሻለ መልኩ ሳጥን ውስጥ የደረሰው 25ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን እንዳለ ደባልቄ በጥሩ ሁኔታ ተከላካዮችን አልፎ ያመቻቸውን ሮቤል ተክለሚካኤል ቢመታም ተከላካዮች ተደርበው አውጥተውበታል። በፈለገው መጠን ሀዋሳዎችን ሰብሮ መግባት ያልቻለው ቡድኑ ከውሃ ዕረፍት መልስም ቀጣዩን ሙከራ ከሳጥን ውጪ ሲያደርግ የአብነት ደምሴ 27ኛው ደቂቃ ጠንካራ የርቀት ሙከራ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል።

በተመሳሳይ አኳኋን በቀጠለው ጨዋታ ሀዋሳዎች ሲጠብቁት የነበረውን ቅፅበት አግኝተዋል። በዚህም 34ኛው ደቂቃ ላይ ተባረክ ሄፋሞ በቡና ሜዳ ላይ የቀማዉን ኳስ ሄኖክ ድልቢ ጥሩ አድርጎ ሲያሳለፍለት ብሩክ በየነ ከገዛኸኝ ደሳለኝ ጋር ታግሎ ሳጥን ውስጥ በመግባት በግራ እግሩ አስቆጥሯል። ሆኖም ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ቀኝ መስመር ያደላ ቅጣት ምት ሲያገኙ አላዛር ሽመልስ በቀጥታ በመምታት ግሩም ጎል አስቆጥሮ ጨዋታውን ወደ አቻ ውጤት መልሶታል።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ጨዋታው በተሻለ ፍጥነት ጀምሯል። የኢትዮጵያ ቡና የኳስ ፍሰት ከመጀመሪያው በተሻለ ወደ ተጋጣሚው የግብ ክልል እየቀረበ ሲታይ ሀዋሳዎችም ፈጠን ያሉ ጥቃቶችን መሰንዘር ጀምረዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ ቡናዎች ሰምሮላቸው 56ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን ችለዋል። አቤል እንዳለ ወደ ሳጥን ያሾለከውን ኳስ እንዳለ ደባልቄ ለመጭረፍ ያደረገው ጥረት ባይሳካም ኳሱን ለማዳን እንዳለ ጋር የደረሰው የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ዳግም ተፈራ ነክቶት ግብ ተቆጥሯል።

ከግቡ በኋላ ሀዋሳ ከተማዎች ወደ አቻነት ለመመለስ የተሻለ ጫና ፈጥረው ለመጫወት ሞክረዋል። ይህን ለማድረግ ከግብ ክልላቸው ርቀው መንቀሳቀስ በመጀመራቸው ጨዋታው የተሻለ ክፍት ሆኖ ታይቷል። በዚህ ሂደት ቡናዎችም ፈጠን ባለ ጥቃት ወደ ሳጥን የሚደርሱባቸው አጋጣሚዎች መታየት ሲጀምሩ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው አላዛር ሽመልስ በቀኝ ጠርዝ ወደ ሳጥን ሲገባ ቸርነት አውሽ በሰራበት ጥፋት ቡናዎች የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። አጋጣሚውንም የቡድኑ አምበል 82ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ግብነት ቀይሮት ልዩነቱን ወደ ሁለት አስፍቷል።

ሀዋሳዎች በቀሩት ደቂቃዎች ግብ ለማግኘት ካደረጉት ጥረት ውስጥ 90ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ምንተስኖት እንድሪስ በቀኝ ሳጥን ውስጥ ሲደርስ ብሩክ በየነ ከግራ አቅጣጫ ጥሩ ኳስ አድርሶት አደገኛ ሙከራ ቢያደርግም በረከት አማረ አድኖታል። ቡናዎችም ወደ ፊት በመድረስ እንዳለ ደበላቄን ያማከሉ ጥቃቶችን እየሰነዘሩ ጨዋታው ወደ ፍፃሜው ዘልቆ በቡና 3-1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ቡና 37 ነጥቦች ላይ ደርሶ ወደ 4ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሀዋሳ በደ 6ኛነት ተንሸራቷል።