የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 1-3 ኢትዮጵያ ቡና

ቡና ሀዋሳን ከረታበት ጨዋታ ፍፃሜ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለሦስት ነጥቡ

“ጥሩ ነው በጣም፡፡ ከሥነ ልቦና አንፃር ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ ነጥብ እየጣልክ በሄድክ ቁጥር የምትፈልገውን ነገር በምትፈልገው ደረጃ እንዳትተገብር የሚያመጣው የሥነ ልቦና ተፅእኖ አለ እና ማሸነፉ ከእዛ አንፃር በጣም ጠቀሜታ አለው፡፡

ዛሬ በቡድኑ የተለየው ነገር

“እኛ በተቻለ መጠን ፓሶች እንዳይበላሹ ነው፡፡ ፓሶች እንዳይበላሹ ምን ማድረግ አለብን እንደ ቡድን ክንፋችንን መጠበቅ አለብን ፣ እንደ ግለሰብ ደግሞ ቶሎ የራሳቸውን አቋም ፓዚሽናቸውን ማስተካከል አለባቸው፡፡ ያንን በማያደርጉበት ሁኔታ ውስጥ ነው ትክክለኛ ፓስ መስጠት የሚቸግራቸው እና የሚቆራረጠውን ፓስ ነው የሚጠብቁት እነርሱ የሚፈጠሩ ክፍተቶች እንዳሉ ያውቃሉ፡፡ ክፍተቱን ከራሳችን ጥቅም አንፃር ነው የምናደርገው እነዚህን ለማረም ነው ከዕረፍት በኋላ የተነጋገርነው፡፡ የታረሙ ነገሮች አሉ የሚታዩ ስህተቶች አሉ፡፡

መሀል ላይ አብነት እና ሮቤል ስለተሰለፉበት ምክንያት

“አብነት እና አማኑእል ትንሽ ጨዋታውን የመያዝ ባህሪ አላቸው ሲጫወቱ፡፡ እንቅስቃሴ ማስቀጠል የሚችል ሰው የመፈለግ ጨዋታው ሊቀጥል የሚችልበትን ፣ ሮቤል ደግሞ ቶሎ ወደ ፊት የመሄድ ጎሉን የመፈለግ ባህሪ አለው፡፡ ታፈሰም ለዛ ነው የሚሆነው ግን በእነዚህ እንጀምር ብለን ነው ፤ ጥሩ ነበር፡፡

በባህርዳር ስለተደረጉ አራቱ ጨዋታዎች

“አዎ ጥሩ ነው፡፡ አራት ጨዋታዎችን አድርገናል ፤ ሦስቱን አሸንፈናል ፤ በአንዱ ነጥብ ጥለናል፡፡ ከዛ አንፃር ሲታይ ጥሩ ነው በእንቅስቃሴም አንፃር ሲታይ ለእኛ ጥሩ ጊዜ ነበር፡፡

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ስለ ሁለቱ አርባ አምስት ደቂቃ

“ከዕረፍት በኋላ ጥሩ አልነበርንም በአጠቃላይ፡፡ ተቀይረው የገቡ ልጆችም ባለው ነው የሚሰራው እና መፈተሽ እንዳለበት ነው የሚሰማኝ ቡድኑ ፣ ምክንያቱም የወረደ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ስለዚህ ደስተኛ አይደለሁም፡፡

የመጀመሪያው 25 ደቂቃ በራስ ሜዳ ላይ ስለ ቆዩበት

“መጀመሪያ ጠብቀን ለመጫወት ነበር፡፡ በዚህ መንገድ ተጫውተን አንድ ለባዶ መምራት ችለን ነበር፡፡ በራሳችን ስህተት ነው፡፡ ጥፋት ሰራን ቅጣት ምቱ ገባ ሁለት ለአንድ ሆነን ግን የማግባት አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ በተለይ ዳኛው መጨረሻ ላይ ያስቆመው ኳስ የሚገባ ኳስ ነው እነዚህም ነገሮች እያወረዱን ነው የመጡት፡፡ ሦስተኛው በስህተት ነው ፔናሊቲ ነው፡፡ ስለዚህ ስንነሳ ፣ ለመነሳት ስናስብ ጎሎች እየተቆጠሩ የገቡ ልጆችም ቡድኑን አላረጋጉም፡፡ በእንቅስቃሴ ደረጃም ጥሩ አይደሉም፡፡ በአጠቃላይ ቡድናችን ከዕረፍት በኋላ ጥሩ አልነበረም፡፡

ስለ ተደረጉ ቅያሪዎች

“በሁለት መንገድ ነው ልጆቹን ያስገባሁት አንደኛ ተጫውተው አያውቁም ፤ እየተመራን ነው፡፡ የነበሩ ልጆች ጨርሰዋል ፣ ስለዚህ እነርሱንም ማየት አስፈላጊ ስለሆነ ለማድረግ ሞክሪያለሁ፡፡ መቶ ፐርሰንት አይቻለሁ ቡድኑን ብዙ መስተካከል ያለበት ቡድን እንደሆነ ነው የሚሰማኝ፡፡

ተደጋጋሚ ነጥብ መጣል እና ተፅዕኖው

“ጥሩነቱ መጀመሪያ የያዝናቸው ነጥቦች ትንሽ ጠቀሙን እንጂ አሁን እያደረግን ያለነው እንቅስቃሴ በተለይ ቋሚ ተሰላፊዎች በጉዳት ከወጡ በኋላ ዋጋ እየከፈልን ነው፡፡ የሚተኩ ልጆች እየታዩ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ያሉትን አምስት ጨዋታዎች ጠንክሮ መስራትን የሚጠይቅ ነው የተጎዱ ልጆቻችን እስከዛ ይደርሳሉ፡፡ በቀሪ ጨዋታዎች ውጤት ይዘን ደረጃውን ለማስጠበቅ እንሞክራለን ብዬ ነው የማስበው፡፡”