በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አንደኛ እና ሁለተኛ ቦታ ላይ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማ የሚያደርጉትን ተጠባቂ ጨዋታ እንደሚከተለው ቃኝተነዋል።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ፋሲል ከነማ በዘንድሮ የውድድር ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ አምስት ተከታታይ ድሎችን አስመዝግቦ ወጥ ካልነበረው ጉዞ በማገገም ራሱን በዋንጫ ፉክክሩ ያከረመ ሲሆን የዘንድሮውን የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት እየተቃረበ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ የስምንት ነጥቡን ልዩነት ወደ አስራ አንድ በማሳደግ ጉዞውን ለማሳመር ጨዋታውን እንደሚጠቀሙበት ይታመናል። በቡድን ጥልቀት እና ተጫዋቾች ስብስብ እንዲሁም ጥራት ከሌሎቹ ክለቦች ራቅ ያሉ የሚመስሉት ፋሲል ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ነገ አስር ሰዓት በበርካታ ደጋፊዎች ታጅበው የሚያደርጉት ፍልሚያ እጅግ ከፍተኛ ፉክክር እንደሚደረግበት ቀድሞ መናገር ይቻላል።
በምርጥ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘው ፋሲል ከነማ በሁለቱም የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች የነበሩበትን ክፍተት በመጠኑ እያሻሻለ ተከታታይ ድሎችን በማስመዝገብ ነጥብ እና ደረጃውን ሽቅብ አሳድጓል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በተገኙት 15 ነጥቦች ሁለት ግብ ብቻ ማስተናገዱ ደግሞ ከወገብ በታች የነበረበት የመከላከል መዋቅር እንደተሻሻለ ይጠቁማል። ባሳለፍነው ሳምንት መከላከያን ሁለት ለአንድ ቡድኑ ቢያሸንፍም በመጠኑ ጠንከር ያለ ፍልሚያ አሳልፎ ነበር። በጨዋታው ቡድኑ ቢፈተንም ግን ከመመራት ተነስቶ ያሳካው ድል በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ የሚያመላክት ነው። በነገው ወሳኝ ፍልሚያ ቡድኑ የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን ወደ ራሱ በማድረግ ሊጫወት እንደሚችል ሲጠበቅ የመስመር ተጫዋቾቹ ብቃት ደግሞ ከጨዋታው አንዳች ነገር ይዞ እንዲወጣ እንደሚያስችሉት ይገመታል። እንዳልነው ከኳስ ጋር ለማሳለፍ ሊያስብ ቢችልም አልፎ አልፎ የሚከተለው የረጃጅም ኳሶች አጨዋወት ለጊዮርጊስ ተከላካዮች ፈተናን ይዞ ሊመጣ ይችላል። በተቃራኒው አራት ግቦች የተስተናገዱበትን የመጀመሪያ ጨዋታ ካስታወስን ግን ጊዮርጊስ ተመሳሳይ አቀራረብ ይዞ ሊመጣ እንደሚችል ልንገምት እንችላለን። በዚህም ከተከላካይ ጀርባ የሚጣሉ ኳሶችን የመከላከል ክፍተቱን ነገም ቡድኑ ካላረመ ራሱን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል።
እስካሁን በሊጉ አንድም ጨዋታ ያልተሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሚሌኒየሙ (2000) ያሳካውን በአንድ የውድድር ዓመት ሳይረቱ ዋንጫ የማንሳት ስኬት ለመድገም እየጣረ ይመስላል። ይህንን እንዳያሳካ ምናልባት ሊያደርገው የሚችለው ፍልሚያም የነገው ጠንካራ ጨዋታ ሊሆን እንደሚችል እየተገመተ ይገኛል። ያለፉትን ጨዋታዎች ቡድኑ ከበድ ያሉ ተጋጣሚዎችን ገጥሞ በአንፃራዊነት ተቸግሮ ቢታይም እጅ ሳይሰጥ መቀጠሉ ትክክለኛ የዋንጫ ቡድን እንደሆነ አስመስክሯል። በተለይ እንደ ድቻ አይነት ቡድኖችን በኳስ ቁጥጥር የበላይ ሆኖ በትዕግስት ለማጥቃት ሲጥር እንደ አዳማ እና ጅማ አይነቶቹን ደግሞ ቀጥተኝነት በበዛበት አቀራረብ ለማሸነፍ ታትሯል። ይህ እንደየተጋጣሚው የመለዋወጥ ነገር ደግሞ ከተገማችነት እና አማራጭን ከማግኘት አንፃር ያለው ጥቅም ከፍተኛ ነው። በሁለቱም የጨዋታ መንገድ ግን በላይኛው ሜዳ ያለው ፍጥነት የታከለበት አጨዋወት ለተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ምቾት የሚነፍግ ስለሆነ አዎንታዊ ጎኑ ብዙ ነው። ቡድኑ ላይ መጠቀስ ያለበት ነጥብ ግን በጅማው ጨዋታ ላይ የተስተዋለው የአማካይ መስመሩ ሚዛን በተወሰነ መልኩ መፋለስ ነው። ቡድኑ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በከፍተኛ ሀይል ይጀምርና ከዛ ግብ ካላገኘ ለማጥቃት የሚያደርገው ጥረት ትንሽ ጉልበት ያጥረዋል። በዚህ ሂደት አማካይ እና ተከላካይ ቦታ ላይ ትንሽ ክፍተት ይፈጠራል። ፋሲል በተቃራኒው በዛ ቦታ ካለው የተጫዋች ጥራት መነሻነት ደግሞ አደጋ እንዳይፈጥርበት መጠንቀቅ የግድ ይለዋል።
ሁሉቱም ቡድኖች የሚያመሳስላቸው ነገር ብዙ አለ። ዋነኛው ተመሳሳይ ጎናቸው ምርጥ፣ የተሟላ እና በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙ መሆናቸው ሲሆን በቅርብ ሳምንታት ከበድ ባሉ ጨዋታዎች ያለፉ መሆናቸው ደግሞ በተመሳሳይ ጎዳና ላይ እየተጓዙ እንደሆነ ይነግረናል። እነዚህን ፈተናዎች በተለያየ መንገድ ማለፋቸው የሚታይ ቢሆንም ቡድኖቹ ጨዋታዎቹን ከተለያዩ ተጫዋቾቻቸው በተገኙት ጎሎች (ፋሲል 11 ጊዮርጊስ 13 አጠቃላይ ግብ ያስቆጠሩ ተጫዋቾች እንዳሉዋቸው ልብ ይሏል) ማሸነፋቸው ሌላ የሚያመሳስላቸው ነገር ነው። በተጨማሪም በምርጥ ብቃት ላይ የሚገኙ እንደ ሔኖክ እና ዓለምብርሃን አይነት የመስመር ተጫዋቾቻቸውም የጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ ሊሆኑ ይችላሉ። በሊጉ ጥቂት ጨዋታዎችን የተረቱት እና እስካሁን በጋራ 78 ጎሎችን ተጋጣሚ ላይ ያስቆጠሩት ሁለቱ ቡድኖች እርስ በእርስ የሚያደርጉትን ጨዋታ በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች ለመከታተል ባህር ዳር ከተማ እየገቡ እንደሆነም አስተውለናል። ይህ ደግሞ ሜዳ ላይ ብቻ ሳይሆን ከሜዳም ውጪ ጨዋታው ውበት እንዲኖረው ሊያደርግ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።
ፋሲል ከነማ በቅጣት የሚያጣው ተጫዋች ባይኖርም በጉዳት ምክንያት አስቻለው ታመነ፣ ሳሙኤል ዮሐንስ እና ሀብታሙ ተከስተን ከነገው ጨዋታ ውጪ አድርጓል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ዘለግ ላለ ጊዜ ጉዳት ካስተናገዱት እስማኤል ኦሮ-አጎሮ እና አዲስ ግዳይ ውጪ ቡልቻ ሹራ እና ከነዓን ማርክነህን በጉዳት በነው ጨዋታ እንደማይጠቀም ሲታወቅ አቤል ያለው ደግሞ ከቡድኑ ጋር ልምምድ ቢጀምርም ለጨዋታው የመድረሱ ነገር እንዳለየለት ተነግሮናል።
የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ፣ ረዳቶች ካሣሁን ፍፁም እና አሸብር ታፈሰ ፣ አራተኛ ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ
ተጨማሪ ዳኞቸች ድሪባ ቀነኒሳ እና ተከተል በቀለ
እርስ በርስ ግንኙነት
– ቡድኖቹ አስር ጊዜ ተገናኝተው እኩል አራት ጊዜ ተሸናንፈዋል። በሁለቱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በግንኙነታቸው ጊዮርጊስ 15 ፋሲል ደግሞ 11 ግቦችን አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ፋሲል ከነማ (4-1-4-1)
ሚኬል ሳማኪ
ዓለምብርሃን ይግዛው – ከድር ኩሊባሊ – ሙጂብ ቃሲም – አምሳሉ ጥላሁን
ይሁን እንዳሻው
ሽመክት ጉግሳ – በዛብህ መለዮ – ሱራፌል ዳኛቸው – በረከት ደስታ
ኦኪኪ አፎላቢ
ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)
ቻርለስ ሉኩዋጎ
ሱሌይማን ሀሚድ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሄኖክ አዱኛ
ሀይደር ሸረፋ – ጋቶች ፓኖም
ተገኑ ተሾመ – የአብስራ ተስፋዬ – ቸርነት ጉግሳ
አማኑኤል ገብረሚካኤል