ለሰባ አራት ደቂቃዎች በጎዶሎ ተጫዋቾች የተጫወተው አዳማ ከተማ ሶስት ነጥብ ካገኘበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ – አዳማ ከተማ
የመጀመሪያ ጨዋታን ስለማሸነፍ
“በጣም ነው ደስ የሚለው፣ አዳማ ነው ትልቅ ቡድን ነው የያዝኩት የመጀመሪያ ጨዋታን በድል መወጣት በጣም ነው ደስ የሚለው፡፡
ስለ ሁለቱ አርባ አምሰት
“መጀመሪያም አንድ ልጅ ጎዶሎ ሆኖብናል፡፡ ስለዚህ የግዴታ ተከላክለን ነው ማጥቃት ያለብን አስደንጋጭ ነበር የወጣበት፡፡ በፈለኩት ነገር ነው የሄደለኝ፡፡
ስለ ዳዋ ቀይ ካርድ
“የዳዋ መውጣት ምንም ጥርጥር የለውም ተፅዕኖ አለው፡፡ ዳዋ ግን አሁን በጣም ከመጨነቁ ቡድኑ ውጤት ከማምጣቱ አንፃር በጣም ተጨንቆ ነው የሚጫወተው ጉጉም ስለሆነ ይሄ ነገር ተከስቷል፡፡ ከፍተኛ ጫና ነው ያለው ያም ቢሆን ግን ባሉት ልጆች እንወጣለን፡፡ ጥሩ ጥሩ ልጆች አሉኝ፡፡
ስለ ነበሩ ካርዶች
“አዎ ይሄንን መነጋገር አለብን፡፡ ልጆቹ ጋም በጣም ስሜታዊ ዳዋ መውጣቱ የተወሰኑትን ኳሶች በጣም ሀይለኛ ሆኑና ትንሽ ከበድ አላቸው፡፡ ያሰጋኛል አሁን በጣም ብዙ ቢጫ ነው ያለው ይሄ በሚቀጥለው ይከሰታል ብዬ አላስብም፡፡
የደረጃ መሻሻሉ ለቀጣይ የሚሰጠው መነሳሳት
“ሀያ ቀን ከዚያ በላይ ጊዜ አለን፡፡ ልጆቹ ላይ ምንም የተለየ ነገር የለም ከበፊቱ ብዙ አልተሰራባቸውም ተረጋግተን ስንመጣ ፣ አርፈን ስንመጣ ደግሞ የተሻለ ነገር ይዘን እንመጣለን ብዬ አስባለሁ፡፡
አሰልጣኝ ብርሀን ደበሌ – ሰበታ ከተማ
አስቀድሞ ሶስት ነጥብ አስፈላጊ ነበር ስለማለታቸው
“ይዘን የመጣነውን እዚህ ሜዳ ላይ ማየት አልቻልንም፡፡ ይሄ የሆነበት ምክንያት ተዳክመን የታየንበትም ምክንያት በተለያየ ሁኔታ ማየት እንችላለን፡፡ ሽንፈቱን በፀጋ እንቀበላለን አዳማም ጥሩ ሲንቀሳቀሱ ነበር፡፡ የኔ ልጆች ተመልካች ነበሩ፡፡ ስለዚህ እንቅስቃሴው እንደነበረው የልጆች በጠበኩት ሁኔታ ያለ ማግኘት ሶስት ጎሎችን አስተናግደን ልንወጣ ችለናል፡፡
የቁጥር ብልጫን አለመጠቀም
“ይሄን የቁጥር ብልጫ ከእረፍት በኋላ ስንገባ ፣ ምን ማድረግ እንዳለብን ለተጫዋቾቼ በደንብ አድርጌ ነግሬያቸዋለሁ፡፡ ለማሸነፍ ደግሞ ጥሩ አጋጣሚ እንደነበር እና ኳሱን በትክክል ይዘን በመስመር እየተጫወትን ጎል የመፍጠር ሁኔታዎችን በተደጋጋሚ ካላገኘን ጎል እንደ ማናስቆጥር ነግሬያቸው ነበር፡፡ ተመልሰው መጀመሪያ የነበረውን እንቅስቃሴ ስለ ደገሙት የተሻለ ነገር ስላልታየ ጎል ማስቆጠር አልቻልንም፡፡ የተወሰነ ለማሸነፍ ብልጭ የምትል ነገር አሳይተዋል፡፡ አጥጋቢ ባለመሆኑ ተሸንፈናል፡፡
ስለ ቢጫ ካርድ እና የኃይል አጨዋወት
“በፍፁም አስፈላጊ አይደለም፡፡ እንደዚህ አይነት ጨዋታ ላይ በእውቀት በጭንቅላት ፣ በአዕምሮ በልጠህ የምትጫወትበት ጨዋታ መሆን ነበረበት እንጂ እንደዚህ አይነት አላስፈላጊ ናቸው ብዬ አላምንም፡፡
ስለ ቀጣይ ተስፋ እና ስጋት
“አምስት ጨዋታ ከፊታችን አሉ፡፡ በመሀል እረፍት አለ ለእዛ ደግሞ መዘጋጀት ነው እግር ኳስ ይሄኝ ይመስላል፡፡