ሪፖርት | ፋሲል ከነማ የቅዱስ ጊዮርጊስን ያለመሸነፍ ጉዞ ገቷል

እጅግ ተጠባቂ በነበረው የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ፋሲል ከነማ በኦኪኪ አፎላቢ ጎል ቅዱስ ጊዮርጊስን 1-0 በማሸነፍ የነጥብ ልዩነቱን ወደ አምስት ቀንሷል።

ፋሲል ከነማ ዛሬ ያሬድ ባየህ እና ይሁን እንዳሻውን
በመከላከያው ጨዋታ በተሰለፉት ከድር ኩሊባሊ እና ሀብታሙ ተከስተ ምትክ ወደ ሜዳ አስገብቷል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጅማው ድል ባደረገው ብቸኛ ለውጥ ደግሞ ተገኑ ተሾመ በቡልቻ ሹራ ቦታ ተሰልፏል።

ተጠባቂነቱን በሚመጥን ግለት የጀመረው ጨዋታ በጊዜ ግብ ተስተናግዶበታል። 3ኛው ደቂቃ ላይ አምሳሉ ጥላሁን ከበረከት ደስታ ጋር አንድ ሁለት በመቀባበል ከፋሲል ሜዳ ግራ መስመር ያሳለፈውን ኳስ በዛብህ መለዮ ተቆጣጥሮ ያደረሰውን ኦኪኪ አፎላቢ በጊዮርጊስ ተከላካዮች መሀል በመቆጣጠር ግብ አድርጎታል።

ከግቡ በኋላ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የነበራቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች የተረጋጉ ቅብብሎችን መከወን አለመቻላቸው ከኳስ ውጪ ለመልሶ ማጥቃት ዝግጁ የሆነ አቋቋም የነበራቸው ፋሲሎችን ለማለፍ አላስቻላቸውም። የቡድኑ የተሻለ ሙከራ 17ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አደኛ ከቀኝ ሳጥን ጠርዝ ላይ ከተገኘ ቅጣት ምት በቀጥታ ሞክሮ ወደ ላይ የወጣበት ኳስ ነበር።

ፋሲል ከነማዎች ቀስ በቀስ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን በመያዝ ከግብ ክልላቸው መውጣት ቢጀምሩም እንደተጋጣሚያቸው ሁሉ አደገኛ ዕድሎችን መፍጠር አልቻሉም። ይልቁኑም 30ኛው ደቂቃ ላይ ሱለይማን ሀሙድ ከግራ መስመር ያሻማው ኳስ ከሚኬል ሳማኬ ግምት ውጪ ወደ ግብ አምርቶ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል። የጀመረበትን ግለት ያጣው ጨዋታ በተቆራረጡ የማጥቃት ጥረቶች ሲቀጥል በተለይም ዐፄዎቹ ከሜዳቸው ሰብረው ሊወጡ የሚችሉባቸውን የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶች በመጨረሻ ቅብብሎች ጥራት ምክንያት ሲያሳልፉ ተመልክተናል።

አጋማሹ ወደ ፍፃሜው ሲቀርብ ጊዮርጊሶች በተሻለ መረጋጋት ላይ ሆነው ቢታዩም በፈጠሩት የተሻለ የ37ኛ ደቂቃ ዕድል አማኑኤል ገብረሚካኤል ቸርነት ጉግሳ ያሳለፈለትን ኳስ መጂብ ቃሲምን ታግሎ በመግባት ከግራ ሩቁ ቋሚ ላይ ጠቅልሎ ለማስቆጠር ያደረገው ሙከራ ሳይሳካለት ቀርቷል። ቀሪዎቹ ደቂቃዎች የፋሲል ከነማዎች ፈጣን ጥቃት ፍሬ ሊያፈራ የተቃረቡባቸው ነበሩ። በሁለት አጋጣሚዎች ኦኪኪ አፎላቢ ቀጥሎም ሽመክት ጉግሳ ከተከላካይ መስመር ጀርባ የመሮጥ ዕድሎችን ቢያገኙም ከተጋጣሚ ተከላካዮች ጋር ታግለው ለማስቆጠር ያደረጓቸው ጥረቶች በፍፁም ቅጣት ምት ጥያቄዎች ከመጠናቀቅ ባለፍ ወደ ሙከራነት እንኳን ሳይቀየሩ ቀርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ቀዝቀዝ ያለ አጀማመር ነበረው። ከነዓን ማርክነህ እና አቤል ያለውን ቀይረው ያስገቡት ቅዱስ ጊዮርጉሶች የማጥቃት ኃይላቸውን አጠናክረው ቢታዩም ቀዳሚው ዕድል በፋሲል በኩል የታየ ነበር። በዚህም 51ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት ተጨራርፎ በተገኘ ኳስ በዛብህ ያደረገውን ሙከራ ቻርለስ ሉኩዋጎ እምብዛም ሳይቸገር አድኖበታል። ከደቂቃ በኋላ በተመሳሳይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከማዕዘን ምት በተነሳ ኳስ ሳጥን ውስጥ የተነካካ አጋጣሚ አግኝተው አልተጠቀሙም። የጨዋታው ቀጣይ ደቂቃዎች ሀይደር ሸረፋን ከጊዮርጊስ ኦኪኪ አፎላቢን ከፋሲል በጉዳት ያስወጡ አጋጣሚዎች ተፈጥረውበታል። ሆኖም ከእንቅስቃሴ ይልቅ ከቆመ ኳስ መነሻነት ቡድኖቹ የተሻለ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቃረቡ ይታይ ነበር።

ከ75ኛው ደቂቃ በኋላ ፋሲሎች ከኳስ ጀርባ ሆነው ሲታዩ የኳስ ቁጥጥር ነፃነት ያገኙት ጊዮርጊሶች የማጥቃት ጥረቶች በተደጋጋሚ በሚገኙ የቆመ ኳስ ዕድሎች ታጅቦ መታየት ጀምሯል። ነገር ግን ፋሲሎች 80ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ጉግሳ የሜዳውን ረጅም ክፍል ኳስ እየነዳ ሳጥኑ ጋር በደረሰበት አጋጣሚ ተፈላጊውን የመልሶ ማጥቃት ዕድል ቢያገኙም ኳሱን የተቀበለው ፍቃዱ ዓለሙ ከጨዋታ ውጪ በመሆኑ ሳይጠቀሙበት ቀርቷል። ጨዋታው ወደ ፍፃሜው ሲቀርብ በመከላከል ውስጥ ለተጋጣሚያቸው የቆመ ኳስ ዕድል ደጋግመው የሰጡት ፋሲሎችም ከኳስ ጋር ከሜዳቸው ወደ መውጣቱ ተመልሰዋል። በዚህም የጊዮርጊስን የማጥቃት ጫና ተቋቁመው እስከመጨረሻው በመዝለቅ ወሳኝ ሦስት ነጥብ ለማሳካት ችለዋል።

ውጤቱን ተከትሎ በሰንጠረዡ አናት በሁለቱ ቡድኖች መካከል የነበረው የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ዝቅ ሊል ችሏል።

ያጋሩ