ሊጉ ለብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ከመቋረጡ አስቀድሞ የሚደረጉትን የነገ ጨዋታዎች እንደሚከተለው ዳሰናል።
ባህር ዳር ከተማ ከ ሲዳማ ቡና
የነገው የጨዋታ ቀን ከድል መልስ በሚገናኙት ባህር ዳር እና ሲዳማ ጨዋታ ይጀምራል። ከ11 ጨዋታዎች በኋላ አዳማን በማሸነፍ ሦስት ነጥቦችን ያሳኩት የጣና ሞገዶቹ ከወራጅ ቀጠናው አራት ነጥብ ርቀት ላይ ብቻ መገኘታቸው ከሰንጠረዡ ወገብ መሻገርን ከነገው ጨዋታ እንዲያልሙ ያደርጋቸዋል። ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ሲዳማ ቡና ደግሞ ዛሬ ካሸነፈው ፋሲል ከነማ ጋር ያለውን ልዩነት በዛው ማስቀጠል ጨርሶ ላልጠፋው ለሁለተኝነት ተስፋው አስፈላጊ ነው።
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ቡድኖቹ ሦስት ነጥብ ከማሳካት ባለፈ በሜዳ ላይ ተረጋግተው የታዩበት ነበር። በሜዳው ባደረጋቸው ጨዋታዎች እንኳን ከድል ጋር አለመታረቁ ከፍ ያለ ጫና ውስጥ የከተተው ባህር ዳር ከተማ በዚህ መነሻነት በቶሎ ግብ ባገኘበት የአዳማው ጨዋታ ውጤት በማስጠበቅ ውስጥ መጠነኛ መረበሽ ቢታይበትም የመጀመሪያ የተጫዋቾች ምርጫውን እየለየ የመጣው ቡድኑ በማጥቃቱ ረገድ የማያስከፋ እንቅስቃሴ አድርጓል። ወሳኝ ተጫዋቹ ፍፁም ዓለሙን በሚያገኝበት በነገው ጨዋታ ከማሽነፍ ሥነ ልቦና ጋር ወደ ሜዳ ሲመለስ ደግሞ የኳስ ምስረታ ሂደቱ በተሻለ ሁኔታ የግብ ዕድሎችን እንዲፈጥር ይጠበቃል።
አወዛጋቢ በነበረው ጨዋታ ወላይታ ድቻን 1-0 ያሸነፈው ሲዳማ ቡና ሙሉ የወገብ በታች ቡድኑን ቀይሮ በገባበት የወላይታ ድቻው ጨዋታ የመከላከል ጥንካሬውን መልሶ ማግኘት ችሎ ነበር። በአዲሱ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ስር በአዲስ የጨዋታ አደራደር የተመለከትነው ሲዳማ ይህን የመከላከል ብርታት በነገው ጨዋታ በማስቀጠል የባህር ዳር ከተማን የኳስ ቁጥጥር ስኬት ከአደጋ ዞኑ በማረቅ ከወትሮው በተለየ ለተጋጣሚ ሳጥን ቀርበው እንዲጫወቱ ከተደረጉት ፈጣሪ አማካዮቹ በሚነሱ ኳሶች ፈጣን ጥቃቶችን እንደሚሰነዝር ይጠበቃል።
በጨዋታው ባህር ዳር ከተማ ፍፁም ዓለሙን ከቅጣት መልስ ሲያገኝ በአንፃሩ ፉዓድ ፈረጃ በአምስተኛ ቢጫ ካርድ በረከት ጥጋቡ ደግሞ በግል ጉዳይ ለነገው ጨዋታ አይደርሱም። ሲዳማ ቡና ግን ያለጉዳት እና ቅጣት ዜና ጨዋታውን ያደርጋል።
የጨዋታ ዳኞች – ዋና ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ ፣ ረዳቶች ሰለሞን ተስፋዬ እና ኤፍሬም ሀይለማርያም ፣ አራተኛ ዳኛ ምስጋናው መላኩ ፣ ተጨማሪ ዳኞች አሸብር ታፈሰ እና እያሱ ፈንቴ
እርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በአምስት የሊግ ጨዋታዎች ሲገናኙ አንዱን አቻ ተለያይተው ሦስቱን ባህር ዳር ከተማ በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ሲችል ሲዳማ አንድ ጊዜ ድል አድርጓል። በጨዋታዎቹ ባህር ዳር ስምንት እንዲሁም ሲዳማ አምስት ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)
አቡበከር ኑራ
ሣለአምላክ ተገኘ – ፈቱዲን ጀማል – ሰለሞን ወዴሳ – አህመድ ረሺድ
ፍፁም ዓለሙ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – አለልኝ አዘነ
ተመስገን ደረሰ – ዓሊ ሱሌይማን – ግርማ ዲሳሳ
ሲዳማ ቡና (4-1-4-1)
መክብብ ደገፉ
አማኑኤል እንዳለ – ጊት ጋትኩት – ያኩቡ መሐመድ – መሐሪ መና
ሙሉዓለም መስፍን
ሀብታሙ ገዛኸኝ – ዳዊት ተፈራ – ፍሬው ሰለሞን – ይገዙ ቦጋለ
ሳላዲን ሰዒድ
ሀዲያ ሆሳዕና ከ ወልቂጤ ከተማ
በመሀከላቸው የሦስት ነጥብ ልዩነት ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች በአምስት ደረጃዎች ርቀት ተቀምጠዋል። ይህ ጨዋታ ለነብሮቹ የደረጃ ለውጥ ባያመጣላቸውም ከበላያቸው ወዳሉት ቡድኖች በነጥብ ቀርበው ሰባተኝነታቸውን እንዲያስከብሩ ይረዳቸዋል። የነገው ውጤት ይበልጥ የሚያስፈልጉት ወልቂጤ ከተማ በበኩሉ ከአደጋ ዞኖ ያለውን የአራት ነጥቦች ርቀት ማስፋት በጣሙን ያስፈልገዋል።
ሀዲያ ሆሳዕና ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ ኢትዮጵያ ቡናን ባልተለመደ መልኩ በአራት ተከላካዮች በሚጀምር አደራደር የረታበት መንገድ ለነገው ጨዋታም የሚረዳው ነው። ጥንቃቄ የተሞላበት የቡድኑ የመከላከል አደረጃጀት በኳስ ቁጥጥር በቀላሉ ሳይታለፍ መቅረቱ የትኩረት መጠኑን በዛ ጨዋታ ልክ አድርጎ የወልቂጤውን ጨዋታ እንዲቀርብ ያደርገዋል። በእርግጥ ቡድኑ ከሌላው ጊዜ አንፃር ተገድቦ የነበረውን የመስመር ተከላካዮቹን የማጥቃት ድርሻ ነገ ከፍ አድርጎ እንደሚቀርብ ይጠበቃል። ሆኖም ከኳስ ቁጥጥር ፍልሚያው ይልቅ ለቀጥተኝነት የሚያደለ ቡድን ከነብሮቹ ይጠበቃል።
ከተጋጣሚው በተለየ የወልቂጤ ከተማ የኋላ መስመር በድጋሚ እርጋታውን ያጣ ይመስላል። ቡድኑ በንፅፅር ለክፉ በማይሰጥ የቁጥር መጠን የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን በተለይም በቀኝ ክንፍ በኩል አድልቶ የግብ ዕድሎችን እንዲፈጥር ከማድረግ ባለፈ ግቦችንም እያስቆጠረ ይገኛል። ሆኖም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ከመረብ ያገናኛቸው አምስት ግቦች ያስገኙለት አንድ ነጥብ ብቻ ነው። ከዚህ አንፃር በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች እየመራ ለሽንፈት የተዳረገው ወልቂጤ ከኳስ ቁጥጥር ባለፈ ጨዋታን ተቆጣጥሮ ውጤቱን አስጠብቆ መውጣት ከነገ ጨዋታው በፊት ዋና የቤት ሥራው ይመስላል።
በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የሀዲያ ሆሳዕናው ዑመድ ዑኩሪ ከቅጣት ሲመለስ አበባየሁ ዮሐንስ በጉዳት ለነገው ጨዋታ አይኖርም። በወልቂጤ በኩል ደግሞ ጨዋታው የሚያልፈው ጉዳት ላይ የሚገኘው አበባው ቡታቆ ብቻ ሆኗል።
የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ዮናስ ማርቆስ ፣ ረዳቶች ካሳሁን ፍፁም ፍሬዝጊ ተስፋዬ ፣ አራተኛ ዳኛ ተስፋዬ ጉሩሙ ፣ ተጨማሪ ዳኞች ማንደፍሮ አበበ እና ዮናስ ካሳሁን
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– እስካሁን ሦስት የግንኙነት ታሪክ ያላቸው ተጋጣሚዎቹ ሁለት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ ሀዲያ ሆሳዕና አንድ ጊዜ ድል አድርጓል። በጨዋታዎቹ ነብሮቹ አምስት ግቦችን ሲያስቆጥሩ ሰራተኞቹ በሦስት ግቦች አፀፋውን መልሰዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሀዲያ ሆሳዕና (4-3-3)
ሶሆሆ ሜንሳ
ብርሃኑ በቀለ – ግርማ በቀለ – ፍሬዘር ካሣ – እያሱ ታምሩ
ሳምሶን ጥላሁን – ተስፋዬ አለባቸው – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን
ሚካኤል ጆርጅ – ዑመድ ዑኩሪ – ሀብታሙ ታደሠ
ወልቂጤ ከተማ (4-4-2 ዳይመንድ)
ሮበርት ኦዶንካራ
ተስፋዬ ነጋሽ – ዳግም ንጉሴ – ዋሀብ አዳምስ – ረመዳን የሱፍ
በኃይሉ ተሻገር – ዮናስ በርታ – ሀብታሙ ሸዋለም
አብዱልከሪም ወርቁ
ጫላ ተሺታ- ጌታነህ ከበደ
መከላከያ ከ ድሬዳዋ ከተማ
25ኛው ሳምንት በታችኛው የሰንጠረዡ ክፍል ባለፍ ፉክክር ላይ ተፅዕኖ በሚኖረው ጨዋታ ፍፃሜውን ያገኛል። ከዕረፍት መልስ በአምስት ጨዋታዎች በሚቀጥለው ውድድር መከላከያ ነገ ድል ማድረግ ከቻለ ከወራጅ ቀጠናው በስምንት ነጥቦች መራቅ መቻሉ ለጨዋታው ትልቅ ትርጉም እንዲሰጠው ያደርገዋል። ድሬዳዋ ከተማም ከበታቹ ያሉት ቡድኖች በዚህ ሳምንት ሙሉ ነጥብ አለመሳካታቸውን ተከትሎ ከአደጋው በስድስት ነጥቦች ከፍ ማለትን እያለመ ወደ ሜዳ ይገባል።
በሰሞኑ በጥሩ ንቃት ላይ ከሚገኙ ቡድኖች ውስጥ የሚጠቀሱት ሁለቱ ተጋጣሚዎች ባለፈው ሳምንት ቀላል ፈተና አልገጠማቸውም። ድንቅ ፍልሚያ በታየበት የፋሲል ከነማው ጨዋታ 2-1 የተረታው መከላከያ ሰሞንኛ ተከታታይ ድሉን አያስቀጥል እንጂ ጠንካራ ጎኖቹ በድጋሚ በእንቅስቃሴው ውስጥ ታይተዋል። በመሆኑም ከፍ ባለ ጉልበት ጨዋታውን የሚጀምር በሙሉ ኃይል የሚያጠቃ መከላከያ ነገም የሚጠበቅ ሲሆን ቡድኑ ተጋጣሚው ኳስ መስርቶ እንዲወጣ የመፍቀድ ዝንባሌ ሊኖረውም ይችላል። ከጦሩ ይልቅ ቢያንስ አንድ ነጥብ ማሳካት ችሎ የነበረው ድሬዳዋ ደግሞ በእንቅስቃሴ ደረጃ ደከም ብሎ ታይቶ ነበር። ቡድኑ በአሰላለፉ ውስጥ ያደረጋቸው ለውጦች አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደሩበት በሚያሳይ መልኩ የማጥቃት አቅሙ እጅግ ተዳክሞ በታየበት የአዲስ አበባው ጨዋታ ያለልዩነት ድንቅ ሆኖ የደመቀው ሄኖክ አየለ ብቻ ነበር። በእንደነገ ዓይነቱ ጨዋታ ግን ድሬዳዋ በፊት አጥቂው የግል ብቃት ላይ ከመመርኮዝ ይልቅ በቀደሙ ጨዋታዎች የነበረውን የማጥቃት ስትራቴጂዎች መልሶ ማግኘት አስፈላጊው ይሆናል።
የመከላከያው ኢብራሁም ሁሴን ይህ ጨዋታ በጉዳት ሲያልፈው የጉዳት ዜና የሌለበት ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ አቤል አሰበ ከቅጣት ተመልሶለታል።
የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ተከተል ተሾመ ፣ ረዳቶች ድሪባ ቀነኒሳ እና ተከተል በቀለ ፣ አራተኛ ዳኛ አለማየሁ ለገሰ ፣ ተጨማሪ ዳኞች አያሌው አሰፋ እና ክንዴ ሙሴ
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች በእስካሁኑ የሊጉ ቆይታቸው 17 ጊዜ ተገናኝተዋል። ዘጠኙ በመከላከያ አሸናፊነት ሲጠናቀቁ አምስቴ አቻ ተለያይተው ድሬዳዋ ሦስት ጊዜ ድል ቀንቶታል። በዚህም መከላከያ 26 ድሬዳዋ ከተማ 13 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
መከላከያ (4-2-3-1)
ክሌመንት ቦዬ
ገናናው ረጋሳ – አሌክስ ተሰማ – አሚን ነስሩ – ዳዊት ማሞ
ኢማኑኤል ላርዬ – ምንተስኖት አዳነ
ተሾመ በላቸው – አዲሱ አቱላ – ቢኒያም በላይ
እስራኤል እሸቱ
ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)
ፍሬው ጌታሁን
እንየው ካሣሁን – አውዱ ናፊዩ – መሳይ ጳውሎስ – አብዱለጢፍ መሐመድ
አቤል አሰበ – ብሩክ ቃልቦሬ
አብዱርሀማን ሙባረክ – ሱራፌል ጌታቸው – ጋዲሳ መብራቴ
ሄኖክ አየለ