በጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ ዕለት የመጀመሪያ በነበረው ጨዋታ ሲዳማ ቡና ባህር ዳር ከተማን 3-1 በመርታት ሁለተኛ ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበዋል።
ባህር ዳር ከተማዎች በመጨረሻው ጨዋታ አዳማ ከተማን ከረታው ስብስብ ባደረጓቸው ሁለት ለውጦች ፉዓድ ፈረጃ እና ዓሊ ሱሌይማንን አስወጥተው በምትካቸው ፍፁም ዓለሙ እና ኦሲ ማውሊን በመጀመሪያ ተሰላፊነት ማስጀምር የቻሉ ሲሆን በአንፃሩ ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ ወላይታ ድቻን ረቶ ከመጣው ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ በግራ መስመር ተከላካይ ስፍራ ላይ መሀሪ መናን አስወጥተው በሰለሞን ሀብቴ በመተካት ለዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።
በተወሰነ መልኩ ብልጫ የተወሰደባቸው ሲዳማ ቡናዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ረጃጅም ኳሶችን ለሰልሀዲን ሰዒድ በማድረስ ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም ቀስ በቀስ ግን ወደ ጨዋታው መግባት ችለዋል። በተለይም ከ20ኛው ደቂቃ አንስቶ ይበልጥ በጨዋታው ራሳቸውን መግለፅ የጀመሩት ሲዳማዎች ተከታታይ ሙከራዎችን በተለይ ከሳጥን ውጭ በሚደረጉ ሙከራዎች መሰንዘር ጀምረዋል። በ21ኛው ዳዊት ተፈራ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ባደረገው እና ኢላማውን ሳይጠብቅ በቀረ ሙከራ አሀዱ ብለው የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች ፤ በ30ኛው ደቂቃ ሰለሞን ሀብቴ ከግራ መስመር ያሻማውን የማዕዘን ምት ኳስ ጊትጋት ጉት በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።
ጨዋታው ዳግም ሲጀምርም በሰከንዶች ልዩነት ሰልሀዲን ሰዒድ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ ተቆጣጥሮ የጠበቀውን ኳስ እየሮጠ ለመጣው ይገዙ ቦጋለ አሳልፎለት ከሳጥን ውጪ የሞከራት እና አቡበከር ኑራ ያዳነበት ኳስ እጅግ አደገኛ ሙከራ ነበር። ከግቧ መቆጠር ጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በጨዋታው ጉዳት ያስተናገደው የባህር ዳር ከተማው አምበል የሆነው ፍቅረሚካኤል ዓለሙ በአብዱልከሪም ኒኪማ ተቀይሮ ከሜዳ ለመውጣት ተገዷል።
በ43ኛው ደቂቃ ደግሞ ሲዳማ ቡናዎች መሪነታቸው ወደ ሁለት ከፍ አድርገዋል ፤ በፈጣን የፈጣን እንቅስቃሴ ከቀኝ መስመር ሀብታሙ ገዛኸኝ ያደረሰውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ይገዙ ቦጋለ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ በግራ እግሩ ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታው ወደ ዕረፍት ከማምራቱ በፊት በረጅሙ ወደ ፊት ከተላከ ኳስ መነሻውን ባደረገ የማጥቃት ሂደት የተገኘን ኳስ ኦሲ ማውሊ መጠቀም ሳይችል ጨዋታው ወደ እረፍት አምርቷል።
በሁለተኛው አጋማሽ 49ኛው ደቂቃ ላይ ባህር ዳር ከተማዎች ወደ ጨዋታው የተመለሱበት ግብ አስቆጥረዋል። ከቀኝ መስመር የተሳው የማጥቃት ሂደት በቁጥር በርክተው ሲዳማ ሳጥን የደረሱት ኳስ ፍፁም ዓለሙ ወደ ግብ ቢልክም በግቡ ቋሚ የተመለሰችውን ኳስ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ዓሊ ሱሌይማን በቀላሉ ደገፍ አድርጎ አስቆጥራል።
ታድያ በዚህች ግብ የተነቃቁት ባህር ዳር ከተማዎች ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ጥረት ቢያደርጉም ሲዳማ ቡናዎች ግን ሳይጠበቁ ሦስተኛ ግብ በማስቆጠር የባህር ዳር ከተማዎች ተነሳሽነት ላይ ውሀ የቸለሰች ግብ አግኝተዋል። 59ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ተፈራ ከተከላካዮች ጀርባ ያደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ሀብታሙ ገዛኸኝ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ በአስደናቂ አጨራረስ በማስቆጠር የቡድኑን መሪነት አሳድጓል።
በፍጥነት ምላሽ ለመስጠት መታተር የጀመሩት ባህር ዳር ከተማዎች በተለይ ከግራ መስመር በሚነሱ ኳሶች ተደጋጋሚ አጋጣሚዎችን በኦሲ ማውሊ አማካኝነት መፍጠር ችለዋል። በ60ኛው ደቂቃ ኦሲ ማውሊ በግራ መስመር ከተጠበበ አንግል ወደ ግብ የላከው ኳስ በግቡ ቋሚ ሲመለስበት በተመሳሳይ በ75ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት መነሻውን ባደረገ የማጥቃት ሂደት በተመሳሳይ የግቡ አግዳሚን ለትሞ ወደ ውጭ ወጥታበታለች።
ክፍት በነበረው አጋማሹ ሲዳማ ቡና በቁጥር በርከት ብለው ለማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ ከነበሩ የባህር ዳር ተጫዋቾች ጀርባ የሚገኘውን ሜዳ በተደጋጋሚ ለማጥቃት ጥረት ያደረጉ ሲሆን በዚህም በ76ኛው ደቂቃ ላይ የፈጠሩትን አጋጣሚ ሳልሀዲን ሰዒድ ወደ ግብ ቢልክም አቡበከር ኑሪ በግሩም ቅልጥፍና አድኗታል።
በጨዋታው 86ኛው ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡናው ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ ጉዳት ማስተናገዱን ተከትሎ በተክለማርያም ሻንቆ ተቀይሮ ከሜዳ የወጣ ሲሆን ባህር ዳር ከተማዎች ግቦችን ፍለጋ በቀሩት ደቂቃዎች በመሉ ኃይል ለማጥቃት ጥረት ቢያደርጉም ግብ ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል።
ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡናዎች ነጥባቸውን ወደ 40 በማሳደግ በ3ኛ ደረጃቸው ሲቀጥሉ በአንፃሩ ተሸናፊዎቹ ባህር ዳር ከተማዎች ደግሞ በ29 ነጥብ ወደ 11ኛ ደረጃ ተንሸራተዋል።