ሪፖርት | ሀዲያ እና ወልቂጤ ነጥብ ተጋርተዋል

በምሳ ሰዓቱ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማዎች ረዘም ላለ ደቂቃ ሲመሩ ቢቆዩም ሀዲያ ሆሳዕናዎች በመጨረሻ ደቂቃ ተስፋዬ አለባቸው ባስቆጠራት ግብ ነጥብ ተጋርተዋል።

ሀዲያ ሆሳዕናዎች በኩል ኢትዮጵያ ቡናን የረታው ስብስብ ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ የቀረቡ ሲሆን ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ በሰበታ ከተማ ከተረታው ስብስብ ሁለት ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዚህም ዮናታን ፍሰሃ እና አክሊሉ ዋለልኝ አስወጥተው በምትካቸው ዮናስ በርታ እና አዲ ኢማሞ ንጎይን ተክተው ቀርበዋል።

ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሁለቱም በተደጋጋሚ ወደ ሳጥን ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ ያስተዋልንበት ነበር። አንፃራዊ በኳስ ቁጥጥር ረገድ የተሻሉ የነበሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ፈጠን ባሉ ወደ ፊት በሚደረጉ ቅብብሎች ተደጋጋሚ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። በተለይም በ8ኛው እና 10ኛው ደቂቃ በግሩም የቅብብል ሂደት በተከታታይ የፈጠሯቸው ዕድሎች አስቆጭ ነበሩ። የመጀመሪያው አጋጣሚ ብርሃኑ በቀለ የሞከረው በግቡ አግዳሚ ሲመለስበት በመቀጠል በሀብታሙ ታደሰ አማካኝነት ያደረጉት ሙከራ ደግሞ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥታባቸዋለች። ነገር ግን በ18ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ጌታነህ ከበደ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ ያስቆጠራት ማራኪ ግብ ወልቂጤ ከተማን መሪ አድርጋለች።

ከግቧ ውጪ በነበረው አጠቃላይ የአጋማሹ እንቅስቃሴ በጨዋታው ከተለመደው የተጫዋቾች አደራደር በተለወጠ መልኩ በኋላ ሦስት ተከላካይ ጨዋታውን የጀመሩት ወልቂጤ ከተማዎች በብዙ መመዘኛዎች ረገድ ደካማ አጋማሽን አሳልፈዋል። በ3ዐኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻማን ኳስ ፍሬዘር ካሳ በግንባሩ በመግጨት የሞከራት ኳስ እንዲሁም በመጀመሪያ አጋማሽ መጠናቀቂያ አካባቢ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን በግራ መስመር በግሩም የአንድ ሁለት ቅብብል ሳጥን ውስጥ ከደረሰ በኋላ ያደረገው ሙከራ የግቡ ቋሚ የመለሰበት አጋጣሚን ጨምሮ በአጋማሹ ተደጋጋሚ ዕድሎችን በመፍጠር ረገድ የተሻሉ የነበሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች መጠቀም ባለመቻላቸው እየተመሩ ወደ መልበሻ ቤት ለማምራት ተገደዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ዑመድ ኡኩሪን እና ባዬ ገዛኸኝን በሚካኤል ጆርጅ እና ራምኬል ሎክ ምትክ ቀይረው በማስገባት የጀመሩት ሀዲያዎች ከጅምሩ ጫና ፈጥረው ለመጫወት ጥረት ያደረጉበት ነበር። ተደጋጋሚ ኢላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎችን ማድረግ የቀጠሉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በተለይም 53ኛው ደቂቃ ላይ ግርማ በቀለ ከተከላካይ ጀርባ የጣለለትን ኳስ ተጠቅሞ ባዬ ገዛኸኝ ግቡን ለቆ የወጣውን ሰዒድ ሀብታሙን አልፎ ያቀበለውን ዑመድ በደካማው እግሩ ያመከናት አስቆጭ አጋጣሚ ነበረች። በአንፃሩ ወልቂጤ ከተማዎች ደግሞ በመልሶ ማጥቃት በሚፈጠሩ አጋጣሚዎች ተጋጣሚያቸው ላይ ጉዳት ለማድረስ ሙከራ ሲያደርጉ ተመልክተናል። በተለይም በጌታነህ ከበደ እና አብዱልከሪም ወርቁ አማካኝነት ጥሩ ጥሩ ሙከራዎችን ፈጥረዋል።

በአጋማሹ እንደ መጀመሪያው ሁሉ በብልጫ መጫወታቸውን የቀጠሉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ጥራታቸውን የጠበቁ የግብ ዕድሎቾን እንደነበራቸው የበላይነት መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በመጨረሻም አቻ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ያደረጉት ሀዲያዎች 91ኛው ደቂቃ በሀብታሙ ታደሰ አማካኝነት ግሩም ሙከራ ቢያደርጉም ሰዒድ ሀብታሙ እና የግቡ አግዳሚ ተረዳድተው አድነውበታል። ነገር ግን በ94ኛው ደቂቃ አቻ መሆን ችለዋል። ከማዕዘን ምት መነሻውን ካደረገ ሙከራ ተስፋዬ አለባቸው ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር በስተመጨረሻም ከጨዋታው አንድ ነጥብ ተጋርተው እንዱወጡ አድርጓል።

ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ነጥባቸውን ወደ 33 ያሳደጉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በነበሩበት 7ኛ ደረጃ ሲቀጥሉ ወልቂጤ ከተማዎችም በ30 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ቀጥለዋል።

ያጋሩ