የቀትሩ ጨዋታ አንድ አቻ ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ተመስገን ዳና – ወልቂጤ ከተማ
ስለጨዋታው
“ከዚህ በፊት ከነበረን አጨዋወት ታክቲካሊ ለውጥ አድርገናል ፤ በተወሰነ ጨዋታውን ገፍተንበታል። ነገር ግን በመጨረሻው ደቂቃ ያስተናገድነው ጎል ነጥብ እንድንጥል አድርጎናል።
ተጨማሪ ጎል ስለማስቆጠር
“እንግዲህ የዛሬው ጨዋታ ቁልፍ ጨዋታ ነው። ምን አልባት ቀድመን ጎል አግብተን ለማስጠበቅ የሄድንበት መንገድ በተወሰነ መልኩ ከሜዳ እንድንሸሽ አድርጎናል። ተደጋጋሚም ጥቃቶችን እንድናስተናግድ አድርጎናል። የዚህ መጨረሻው ደግሞ ጎል እንዲቆጠርብን አድርጎናል።
ስለዳኝነት
“ስለዳኝነት ብዙ ማውራት አያስፈልግም። እነርሱ ራሳቸውን ይገምግሙ፣ እኛ ደግሞ የእኛን ስህተት እንገመግማለን።”
አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዲያ ሆሳዕና
ስለጨዋታው
“ጨዋታው ጥሩ ፉክክር ነበረው። የመጀመርያው አጋማሽ ትንሽ ተቀዛቅዘን ነበር። በሁለተኛው የተሻለ ኳስን ለመያዝ፣ ወደ ጎልም በመሄድ ሙከራዎች አድርገናል። እነርሱ ቀድመው ስላገቡብን ውጤቱ ለሁለታችንም አስፈላጊ ስለነበር ጨዋታው ከበድ ያለ ነበር።
ስላልተጠቀሙበት ዕድል
“መጓጓት ፤ መቸኮል ነው። የመጨረሻው ቦታ ደርሰናል ፣ መረጋጋት ነው የሚጠበቅብን ሆኖም ውጤቱን ለማምጣት ስላስፈለገ እንጂ እነርሱ ቀድመው አገቡ እኛ መጨረሻ አገባን። ጨዋታውን ወጠር ያደረገው ደግሞ ተመስገን ወጣት አሰልጣኝ ነው። ጠንካራ ፉክክር እንዲኖረውም ያደረገው ያ ነው ፣ ጓደኛዬም ስለሆነ ምርጥ ቡድኖች ጥሩ ጨዋታ ተካሂዷል ብዬ ነው የማስበው።”