የአሰልጣኞች አስተያየት | መከላከያ 0-0 ድሬዳዋ ከተማ

ወደ ዕረፍት ለማምራት የመጨረሻ ማሳረጊያ በሆነው እና ያለ ጎል ከተጠናቀቀው ጨዋታ ፍፃሜ በኋላ አሰልጣኞች ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡

ረዳት አሰልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ – መከላከያ

ስለ ጨዋታው

“በመጀመሪያ ደረጃ ለማሸነፍ ነው የገባነው ሁሉም ቡድን ለማሸነፍ ነው የሚገባው ፣ ግን የምታሸንፍበትን መንገዶች በጥንቃቄ የተሞሉ መሆን አለባቸው፡፡ ዝም ብሎ ጎል አታገኝም ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ አቋቋም ሁሉ ነገር መስተካከል አለበት፡፡ ወደ ፊት ለማግባት የምናደርገው ጥረታችን ጥሩ ነው፡፡ ግን ወደ ፊት ስትሄድ እንዴት ነው የምንሄደው ነው፡፡ ስለዚህ ለማግባት ለማሸነፍ ካለን ጉጉት ተቆጣጥረህ መውጣት አለብህ፡፡ ማለት ለማግባት የምትፈልገውን ነገር በጥንቃቄ ፣ መረጋጋት አለብህ ካልተረጋጋህ ጎል አታገባም፡፡ ትንሽ ልጆቹን አስጨንቋቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዛ በተረፈ ጥሩ ነው፡፡ ወደ ፊት እሄዳለን ፣ አንዳንዴ የተሻልኩ ነኝ ካልክ ሜዳ ላይ በተግባር ማሳየት አለብህ፡፡ እኛ ስም አንፈልግም፡፡ በህብረት ካልተጫወትን አናሸንፍም ስለዚህ ጨዋታው የህብረት ጨዋታ ነው የሚፈልገው፡፡ ለማጥቃት ያደረግነው እንቅስቃሴ ከእረፍት በፊትም በኋላም ጥሩ ነው፡፡ ያገኘናቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ መጠቀም እንችል ነበር አልተሳካም ስለዚህ ይሄን ስህተት ደግሞ ሌላ ጊዜ ማስተካከል አለብን፡፡

የቢኒያም በላይ ፣ ተሾመ በላቸው እና አዲሰ አቱላ ያልተጠበቀ ቅያሪ

“የምታስገባቸው ተጫዋቾች ሜዳ ላይ የሚፈለገውን ነገር አድርገው መውጣት አለባቸው፡፡ ከአሁን ከአሁን ያደርጋል ብለህ የምትጠብቀው አይደለም ጨዋታው ፣ ስለዚህ ያልተጠበቀ ቅያሪ ለእናንተ ነው፡፡ እንጂ ለእኛ ያልተጠበቀ ቅያሪ የምንለው የለም፡፡ ተጠባባቂ ላይ ያሉም ልጆች ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ገብተው የሚቻላቸውን ነገር ማድረግ ይችላሉ፡፡ በእናንተ በኩል እንጂ ያልተጠበቀው በእኛ በኩል አይደለም፡፡

ስለ መከላከሉ ድክመት

“በመከላከልም ፣ በማጥቃትም ብዙ ጊዜ እንሰራለን፡፡ ሰርተህም አንዳንዴ የምትፈልገውን ነገር ላታገኝ ትችላለህ፡፡ ስለዚህ ወደ ጎል ስትሄድ እንዴት ነው የምታጠቃው ፣ ስትከላከል እንዴት ነው አቋቋም ፣ ፖዝሽን ይሄን ሁሉ ነገር በልምምድ ላይ እንሰራለን፡፡ ሜዳ ላይ ደግሞ ካልተተገበረ ከእንደገና ሌላ ልምምድ ላይ እንሰራለን፡፡

ስለ ቀጣይ ዕረፍት

“እኔ በጥሩ ነው የማስበው፡፡”

አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ – ድሬዳዋ ከተማ

ስለ ጨዋታ ዕቅድ አተገባበር

“ባሰብነው ልክ አይደለም፡፡ ምንድነው በመከላከል ረገድ ባለን ነገር ላይ ጥሩ ነበርን፡፡ ከየትኛውም አቅጣጫ ረጃጅም ኳሶን እንደሚለቁ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን እነርሱ የሚለቋቸው ረጃጅም ኳሶች ሲመጡ ወደ እኛ ሜዳ ተበታትነው ነው የሚመጡት ፣ መሬት አስይዘን ግራ እና ቀኝ ብልጫ ወስደን በቀላሉ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመፍጠር የመጀመሪያው አርባ አምስት ላይ ጥሩ አልነበረም፡፡ ከመጀመሪያው አርባ አምስት ሁለተኛው አርባ አምስት የተሻልን ነን በእንቅስቃሴ ረገድ በሚፈለገው ልክ አልሄደም፡፡ ሌላው ኳሶች የመቆራረጥ ነገር ነበር ፣ ወጥነት አይታይም ብልጭ ይላል ተመልሶ ይጠፋል ፣ ይታያል ተመልሶ ይጠፋል፡፡ ይሄ ችግራችን ነው በቀጣይ የምንሰራበት ይሆናል፡፡

ስለ መስመር አጨዋወት ዕቅዳቸው

“መጥፎ አይደለም፡፡ ልጆቹ ጋር ካለው ኳሊቲ በመነሳት ነው ፈጣኖች ናቸው ፣ ልምዱም አላቸው ያንን የመስመር ስራውን በደንብ ማቀላጠፍ እና መስራት ይችላሉ፡፡ የኳስ አቅርቦቶች ደካማ ነበር፡፡ የሚመጡ ኳሶች አልነበሩም ፣ ኳስ ለመፈለግ ወደ ኋላ የሚመለሱበት ወቅት ነበር፡፡ ከተጋጣሚ የቁጥር ብልጫ እየተወሰደብን በቀላሉ ኳሶች ይበላሹ ነበር፡፡ በምፈልገው ልክ አልሄድም፡፡

ስለ ቀጣዩ ዕረፍት

“በበጎ ነው የምንወስደው፡፡ ምክንያቱም ያሉን ድክመቶች ላይ ጠንክረን ሰርተን፡፡ በቀጣይ ከእረፍቱ በኋላ የተሻለ የቡድን አቀራረብ ይዘን እንመጣለን፡፡”