የሰበታ ተጫዋቾች ለፌዴሬሽኑ ደብዳቤ አስገብተዋል

21 የሰበታ ተጫዋቾች በጋራ በመሆን በዛሬው ዕለት ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ደብዳቤ ማስገባታቸው ታውቋል።

በዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በወራጅ ቀጠናው ቅርቃር እየዳከረ የሚገኘው ሰበታ ከተማ ከዓምና ጀምሮ ከደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጋር ተያይዞ በተጫዋቾቹ ጥያቄዎች ሲቀርቡበት የነበረ ሲሆን አሁንም በክለቡ የሚገኙ 21 ተጫዋቾች በዛሬው ዕለት ቅሬታቸውን አሰምተውበታል።

ተጫዋቾቹ በፃፉት ደብዳቤ “እየተገባደደ የሚገኘውን ወር ጨምሮ ያለፉትን ሁለት ተከታታይ ወራት ደሞዝ ሊከፈለን አልቻለም” በማለት ደሞዛቸው በቀጣዮቹ አምስት ተከታታይ ቀናት ካልተፈፀመላቸው ልምምድ እና ውድድር ላይ እንደማይሳተፉ ጠቅሰዋል።

ተጫዋቾቹ ስም እና ፊርማቸው ባረፈበት ደብዳቤ ላይ በ2013 ከ2 እስከ 4 ወር ደሞዝ እና ጥቅማጥቅም ያልተፈፀመላቸው ተጫዋቾችን እንደተካተቱም ገልፀዋል። ከሰዓታት በፊት ለፌዴሬሽኑ የገባው ደብዳቤ ለሰበታ ስፖርት ጽሕፈት ቤት ፣ ለኦሮሚያ ከተማ ስፖርት ኮሚሽን ፣ ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር እና ለኢትዮጵያ እግርኳስ ተጫዋቾች ማኅበር ግልባጭ እንደገባ እንደሆነ አውቀናል።