ሊጉ ለአህጉራዊ ውድድሮች ቦታውን ከማስረከቡ ወዲህ የተደረጉ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ላይ ያተኮሩ ክለብ ነክ ጉዳዮች የመጀመሪያው ፅሁፋችን አካል ናቸው።
👉 የቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያ ሽንፈት እና የፋሲል ከነማ ድል አንድምታ
ወደ ፍፃሜው እየተቃረበ በሚገኘው ሊጉ የዋንጫውን መዳረሻ ይጠቁማል በሚል በከፍተኛ ጉጉት ሲጠበቅ በነበረው የውድድር ዘመኑ ትልቁ ጨዋታ ፋሲል ከነማ ቅዱስ ጊዮርጊስን በኦኪኪ አፎላቢ ብቸኛ ግብ በማሸነፍ አምስት ጨዋታዎች እየቀሩ በመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያላውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ማጥበብ ችሏል።
በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን 24ኛው የጨዋታ ሳምንት ግንቦት 10 2013 ላይ በሀዲያ ሆሳዕና ሽንፈት ካስተናገዱ ወዲህ ቅዱስ ጊዮርጊሶች እስከ ፋሲሉ ሽንፈት ድረስ በሊጉ 26 ጨዋታዎችን በድምሩ ያደረጉ ሲሆን 17 ጨዋታዎችን በድል ሲወጡ በተቀሩት 9 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ በመጋራት ተጉዘው በ27ኛው ጨዋታ ግን ለአምናው የሊጉ አሸናፊ እጃቸውን ሰጥተዋል። በጨዋታው እኪኪ አፎላቢ ያሰቆጠራት ግብም ቡድኑ በ16ኛ ሳምንት ሰበታን 3-1 ሲረታ በረከት ሳሙኤል ካስቆጠረበት ግብ በኋላ በዘጠኝ የጨዋታ ሳምንታት ያስተናገደው የመጀመሪያ ግብ ሆኖ ተመዝግቧል።
በጨዋታው ሌላው የታዘብነው ነገር እየሳሳ የመጣው የቡድኑ ከወገብ በላይ ያሉ የተጫዋቾች አማራጭ እና ዕድሎችን የመፍጠር አቅም መቀዛቀዝን ነው። በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ብቻ ያስቆጠረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በፋሲሉ ጨዋታ ላይ ግን ቢያንስ በጨዋታ አንድ ግብ ያገኝበት የነበረውን አካሄድ መድገም ባለመቻሉ ነጥብ ለመጋራትም ሳይችል ቀርቷል።
በአንፃሩ ከ22ኛ የጨዋታ ሳምንት መጠናቀቅ በኋላ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በሁለት አሀዝ (10 ነጥብ) ርቀው ይገኙ የነበሩት ፋሲል ከነማዎች በሦስት የጨዋታ ሳምንት ልዩነት ይህን የነጥብ ልዩነት በግማሽ መቀነስ ችለዋል።
እርግጥ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ትልቅ ትርጉም ያለውን ጨዋታ በድል መወጣት ቢችሉም አሁንም ቢሆን ፋሲል ከነማዎች ክብራቸውን ለማስጠበቅ የቀሯቸውን ጨዋታዎች በድል መወጣት እና የቅዱስ ጊዮርጊስን ነጥብ መጣል መጠበቅ የግድ ይላቸዋል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቀጣይ ባህር ዳር ፣ ወልቂጤ ፣ ሀዲያ ሆሳዕና ፣ አርባምንጭ እና አዲስ አበባ ከተማን የሚገጥሙ ሲሆን በአንፃሩ ፋሲል ከነማዎች ደግሞ ሰበታ ፣ አዳማ ፣ ሀዋሳ ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ እንደቅደም ተከተላቸው ቀሪ ተጋጣሚዎቻቸው ናቸው።
ሊጉ ለቀናት በአህጉራዊ ውድድሮች መቋረጥ በኋላ ሲመለስ ቀሪ አምስት ጨዋታዎች በጉጉት የሚጠበቁ ይሆናል። በዚህም ቅዱስ ጊዮርጊስ በእጁ ያለውን መሪነት አስጠብቆ ከ2009 በኋላ ዳግም ወደ ሊጉ አሸናፊት ይመለሳል ወይስ ፋሲል ከነማ ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት የሊጉን ክብር ይቀዳጃል የሚለው ጉዳይ በጉጉት ይጠበቃል።
👉 አዳማ ከተማ ወደ ድል ተመልሷል
እንደ ቡድን ጥሩ ሲንቀሳቀሱ ቢቆዩም ድል ካደረጉ ከ15 የጨዋታ ሰዓታት በላይ ያሳለፉት አዳማ ከተማዎች በ11ኛ ሙከራቸው ሙሉ ሦስት ነጥብ ማግኘት ችለዋል።
በ25ኛ የጨዋታ ሳምንት ሰበታ ከተማን ሲገጥሙ በአዲስ አሰልጣኝ የቀረቡት አዳማ ከተማዎች በእንቅስቃሴ ረገድ በተወሰነ መልኩ የተለወጠን ነገር ሜዳ ላይ አሳይተው ከጨዋታው ግን ወሳኝ ሦስት ነጥብ እና ሦስት ጎሎችን አስመዝግበው ወጥተዋል። በጨዋታው ገና በ10ኛው ደቂቃ አዲስ ተስፋዬ ባስቆጠራት ግብ ቀዳሚ መሆን የቻሉት አዳማ ከተማዎች በ17ኛው ደቂቃ ግን ሳይጠበቅ አምበላቸው ዳዋ ሆቴሳን በቀይ ካርድ ለማጣት ተገደዋል። ይህንን ተከትሎም ቀሪዎቹን 74 ያህል ደቂቃዎች በ10 ተጫዋቾች ለማሳለፍ ተገደዋል።
ታድያ በዚህ ሂደት እጅ ያልሰጡት አዳማ ከተማዎች በተወሰነ መልኩ መከላከል ላይ ተጠምደው የቆዩ ቢመስልም በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች ግን በተለይ በመልሶ ማጥቃቱ ረገድ በነበራቸው ድንቅ አፈፃፀም ሁለት ተጨማሪ ግቦችን በደስታ ዮሐንስ እና ዮናስ ገረመው አስቆጥረው ጨዋታውን 3-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።
በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የተመሩት አዳማ ከተማዎች በጨዋታው ከወትሮው በተለየ እንደ ቡድን በመጫወት ረገድ የተዋጣላቸው ነበሩ። በተለይም ከቀይ ካርዱ ወዲህ እንደ ቡድን ለመከላከል ያደረጉት ጥረት እንዲሁም በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች ደግሞ በማጥቃቱ ወቅት በተጋጣሚ ሜዳ በርከት ብለው ለማጥቃት የነበራቸው ፍላጎት ያልተጠነቀ ነበር።
ሌላኛው የተለየ የነበረው ሂደት ቡድኑ ግብ ለማስቆጠር በተቸገረባቸው ጨዋታዎች የማጥቃት ጫና ለመፍጠር በሚሞክርባቸው ወቅቶች ከአጥቂዎች ባለፈ በሌሎች ተጫዋቾች አይታገዝም የሚለው ጉዳይ ነበር። ነገር ግን በሰበታው ጨዋታ በተለይ ሁለቱ ስምንት ቁጥሮች ይበልጥ ለአጥቂዎቹ ቀርበው በመንቀሳቀስ በተደጋጋሚ ሳጥን ውስጥ በመገኘት ጭምር ማጥቃቱን ሲያግዙ ነበር። በዚህም ሂደት አማካዩ ዮናስ ገረመው የማሳረጊያዋን ግብ ማስቆጠር የቻለ ሲሆን በተመሳሳይ ሌላኛዋን ግብ ከፍፁም ቅጣት ምትም ቢሆን ያስቆጠረው ደስታ ዮሐንስ ከግራ ተከላካይ ቦታው በመነሳት በማጥቃቱ የነበረው አበርክቶ በሜዳ ላይ የነበረው የአዳማ ስብስብ በማጥቃት ሂደቱ ላይ ለመሳተፍ ለነበረው ተነሳሽነት ማሳያ ነው።
የአሰልጣኝ ለውጥ አድርገው ወደ ጨዋታው የመጡት አዳማ ከተማዎች ይህን በፍላጎት ረገድ የታየውን መሻሻል በምን መልኩ ዘላቂ አድርገው ማስቀጠል ይችላሉ የሚለው ጉዳይ በቀጣይ ሊጉ ከዕረፍት ሲመለስ ይጠበቃል።
👉 ሲዳማ ቡና ተከታታይ ድል አስመዝግቧል
በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ መጣላቸውን ተከትሎ ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ጋር የተለያዩት ሲዳማ ቡናዎች በአዲሱ አሰልጣኛቸው ወንድምአገኝ ተሾመ እየተመሩ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ተከታታይ ድል አስመዝግበዋል።
ባህር ዳር ከተማን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የገጠሙት ሲዳማዎች በጨዋታው በሁለቱም አጋማሾች በደጋፊያቸው እየተጋዙ ከፍ ያለ ጫና አሳድረው ጨዋታውን በተሻለ መንገድ ለመጀመር ጥረት ካደረጉት ባህር ዳሮች የተሰነዘረባቸውን የጫና ማዕበል ተቋቁመው በማለፍ ተጋጣሚያቸው ላይ ሳይጠበቁ በፈጣን ጥቃት ጉዳት በማድረስ ጨዋታቸውን 3-1 በሆነ ውጤት ተወጥተዋል።
የአፍሪካ ተሳትፎ የሚያስገኝላቸውን ደረጃ ይዘው ለማጠናቀቅ ውጥን የነበራቸው ሲዳማ ቡናዎች አሁን ላይ 3ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ በ2ኛ ደረጃ ከሚገኙት ፋሲል ከነማዎች በዘጠኝ ነጥብ ርቀው ይገኛሉ በዚህም መነሻነት አሁን ላይ ካለው ነባራዊ ሁኔታ መነሻነት ቡድኑ ይህን ስፍራ የማሳካቱ ነገር የጠበበ ቢመስልም ውድድር ዘመኑን በተሻለ ነጥብ እና ደረጃ ለማጠናቀቅ የተቻላቸውን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
👉 ወልቂጤ ከተማ አሁንም መሪነቱን አሳልፎ ሰጥቷል
ጥሩ እምርታ አሳይተዋል በሚል በስፋት ሲነገርላቸው የነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች በመጨረሻ አራት የሊግ ጨዋታዎች ውጤታቸው አስደሳች አልሆነም። በተለይ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ነጥብ የጣሉባቸው መንገዶች አሳማኝ አልነበሩም።
በ23ኛ የጨዋታ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡናን የገጠሙት ወልቂጤዎች በመጀመሪያው አጋማሽ 3-1 እየመሩ ያጠናቀቁትን ጨዋታ በመጨረሻዎቹ 12 ደቂቃዎች ባስተናገዷቸው ሦስት ግቦች መነሻነት 4-3 በሆነ ውጤት ሦስት ነጥቡን ለተጋጣሚያቸው አተስረክተበው ወጥተዋል። በ24ኛ ሳምንትም እንዲሁ ሰበታን ሲገጥሙ በጨዋታው ፍፁም የተሻሉ የነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች በ62ኛው ደቂቃ በጌታነህ ከበደ አማካኝነት ባስቆጠሩት ግብ ቀዳሚ መሆን ቢችሉም በስተመጨረሻም 2-1 በሆነ ውጤት የተሸነፉ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንትም እርግጥ በተጋጣሚያቸው በብዙ መመዘኛዎች ብልጫ ተወስዶባቸው ባሳለፉት ጨዋታ በ18ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ ባስቆጠራት ግብ ጨዋታውን ሲመሩ ቢቆዩም በ93ኛው ደቂቃ በተቆጠረባቸው ግብ ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ተገደዋል።
ታድያ በሦስቱ ጨዋታዎች በዋነኝነት ቡድኑ መሪነቱን ማስጠበቅ አለመቻሉ “ዕድለ ቢስ” ቢያሰኘውም በሦስቱም ጨዋታዎች ወቅት የነበረው የጨዋታ አስተዳደር ላይ ግን ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው።
‘የጨዋታ ቁጥጥር በመሰረታዊነት ቡድኖች በራሳቸው የጨዋታ ሀሳብ ውስጥ ተጋጣሚ የሚፈልገውን ነገር እንዳያደርግ ሁኔታዎችን አስቸጋሪ ማድረግ ነው’ በሚለው ትርጉሙ እንኳን ብንወስደው ቡድኑ ከማጥቃት ፍላጎቱ ወጥቶ ለመጠንቀቅ በሚያደርጋቸው እንዲሁም ጨዋታውን ይበልጥ ተጋጣሚው ሊደርስበት በማይችለው የግብ ልዩነት ማድረስ የሚችልባቸውን የማግባት አጋጣሚዎች መጠቀም አለመቻሉ እና ሌሎች ምክንያቶች ተጋጣሚዎች ዳግም ከጨዋታው የሆነ ነገር ይዘው እንዲወጡ እየረዳቸው ይገኛል።
በመሆኑም በጨዋታዎች አዎንታዊ ሆኖ ከመቅረብ ባለፈ በአንዳንድ ወቅቶች ጨዋታው የሚጠይቀውን ነገር ሁሉ ለመስጠት የተዘጋጀ ቡድን መሆን ካልቻሉ በቀር ተፎካካሪ ለመሆን የሚቸገሩ ይመስላል።
👉 ጅማ እና ሰበታ የመትረፍ ተስፋቸው እየራቀ ይገኛል
አምስት ጨዋታ በቀረው ሊጉ በሂሳባዊ ስሌት በሊጉ የመቆየት ተስፋቸው እስካሁን ያልተሟጠጠው ሰበታ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር በሊጉ የመቆየታቸው ነገር እያበቃለት ያለ ይመስላል።
በጨዋታው ሳምንቱ ሰበታ ከተማ በአዳማ ከተማ 3-0 ሲረታ በአንፃሩ ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር አንድ አቻ መለያየታቸውን ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች ነጥባቸውን 20 በማድረስ በሊጉ ግርጌ የመጨረሻዎቹን ሁለት ቦታዎች ይዘው ይገኛሉ።
ይህም ማለት በሌሎች ክለቦች ውጤት ማጣት ላይ በተንጠለጠለው የሊጉ ቆይታቸው አሁን ላይ በዕኩል 29 ነጥብ 13ኛ እና 12ኛ ደረጃ ከሚገኙት ድሬዳዋ ከተማ እና ባህር ዳር ከተማ ጋር ያላቸው የነጥብ ልዩነት ዘጠኝ ነው። ይህም ማለት ጅማ እና ሰበታ የቀራቸውን አምስት ጨዋታዎች በሙሉ ቢያሸንፉ እንኳን ነጥባቸውን ወደ 35 ማድረስ የሚችሉ ሲሆን በአንፃሩ ድሬዳዋ እና ባህር ዳር ከቀሪ አምስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚችሉት የነጥብ ብዛት ግማሹን እንኳን ማሳካት ቢችሉ ነጥባቸው 36 ማድረስ የመቻላቸውን ነገር ከግምት ውስጥ ስናስገባ በሊጉ የመቆየታቸው ነገር እያበቃለት ያለ ይመስላል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ጅማ አባ ጅፋር እና ሰበታ ከተማ ከቀራቸው መርሐግብሮች ክብደት እና ቅለት ባለፈ ሁለቱም ቡድኖች የራሳቸውን የቤት ሥራ የመወጣታቸው ነገር እንኳን በጣም አጠራጣሪ ነው። ከዚህ ባለፈ አዲስ አበባ ከተማዎችም ከሁለቱ ቡድኖች የተሻለ የአምስት ነጥብ ብልጫ ቢኖራቸውም የእነሱም የመቆየት ተስፋ ወደ 11ኛው ሰዓት ላይ እየደረሰ ይመስላል።
በቀጣይ የውድድር ዘመን ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ ኢትዮጵያ መድን እና ለገጣፎ ለገዳዲ ሦስቱ አዲሶቹ የሊጉ አዳጊ ቡድኖች በመሆን እየተጠባበቁ ሲገኝ ጅማ አባ ጅፋር እና ሰበታ ከተማ ደግሞ ቦታቸውን ለማስረከብ እየተንደረደሩ የሚገኝበት ወቅት ላይ እንገኛለን።