ለሴካፋ ዋንጫ ሦስት ኢትዮጵያዊያን ሴት ዳኞች ጥሪ ደርሷቸዋል፡፡
የሴካፋ ሴቶች ዋንጫ በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ከቀናት በፊት በተራዘመው ቀን መሠረት ግንቦት 24 ካምፓላ ላይ ጅምሩን ያደርግ እና ለአስር ተከታታይ ቀናት ቆይታ ይኖረዋል፡፡
በሁለት ምድብ ተከፍሎ በስምንት ሀገራት መካከል ውድድሩ የሚከናወን ሲሆን ሀገራችን ኢትዮጵያ ከብሔራዊ ቡድን ተሳትፎዋ ባሻገር ሦስት ሴት ዓለም አቀፍ ዳኞችን ለውድድሩ ማስመረጧን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች፡፡
ከዚህ ቀደም በተከታታይ አህጉራዊ እና ክፍለ አህጉራዊ ውድድሮችን ስትመራ የምናውቃት ፀሀይነሽ አበበ ፣ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢንተርናሽናል ባጅ ያገኘችው ምስጋና ጥላሁን በዋና ዳኝነት ሲመረጡ ረዘም ያለ ልምድ ያላት ወይንሸት አበራ በበኩሏ በረዳት ዳኝነት በውድድሩ ላይ ተሳትፎ እንድታደርግ ጥሪው ደርሷታል፡፡