የአንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ዛሬ ሲቀጥል ቦዲቲ ከተማ እና መከላከያ ቢ ወደ ከፍተኛ ሊግ ማደጋቸውን አረጋግጠዋል።
ማለዳ 02:00 የጀመረው የቦዲቲ ከተማ እና የድሬዳዋ ፖሊስ ጨዋታ በቦዲቲ 2–0 አሸናፊነት ተጠናቋል
ድሬዳዋ ፖሊስ ደጋፊዎች በጂንካ ጨዋታ ወቅት ባሳዩት ያልተገባ ባህሪ ምክንያት አወዳዳሪው አካል ይህ ጨዋታ በዝግ እንዲካሄድ በወሰነው ውሳኔ መሠረት ጨዋታው በዝግ እንዲካሄድ ተደርጓል። የጨዋታው የመጀመርያ 15 ደቂቃ ድሬዳዋ ፖሊሶች በመጫወት ፍላጎት እና ኳሱን በሚገባ ተቆጣጥሮ ጫና በመፍጠር ረገድ የተሻሉ የነበረ ቢሆንም የጠራ የጎል ሙከራ ለማድረግ ተቸግረዋል። በጫና ውስጥ ሆነው በመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር የሞከሩት ቦዲቲዎች በመጀመርያ የጎል ዕደል በፈጠሩበት አጋጣሚ የመጀመርያውን ጎል ማስቆጠር ችለዋል። ጎሉንም ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በመጠቀም አማኑኤል አሊሳ በ16ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል።
በተመሳሳይ የጨዋታ መንገድ ጎል ፍለጋ ጥረት ያደረጉት ፖሊሶች ኳሱን ከመቀባበል ውጪ አሁንም አደጋ መፍጠር ሳይችሉ ቀርተው ሌላ ጎል ለማስተናገድ ተገደዋል። በፈጣን መልሶ ማጥቃት የፖሊሶች ሜዳ የደረሱት ቦዲቲዎች በ32ኛው በፍቃዱ ሕዝቄል አማካኝነት ሁለተኛ ጎላቸውን አግኝተው ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል በፍጥነት ያገኙት ድሬዳዋ ፖሊሶች ሄኖክ አበራ የግል ጥረት 49ኛው ደቂቃ ጎል አስገኝቷል። በዚህ ጎል የተነቃቁት ፖሊሶች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር ያደረጉት ጥረት ስኬታማ ሳያደርጋቸው ቀርቶ ቦዲቲዎች ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበትን ዕድል ለመፍጠር ከማሰብ ይልቅ ውጤቱን አሳልፎ ላለመስጠት በሙሉ አቅማቸው ያደረጉት መከላከል ስኬታማ አድርጓቸው ጨዋታውን ከዕረፍት በፊት ባስቆጠሩት ጎሎች 2–1 አሸንፈው ወጥተዋል።
ውጤቱን ተከትሎ ቦዲቲ ከተማ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ከፍተኛ ሊግ ማደጉን አረጋግጧል።
ረፋድ ላይ የተካሄደው የመከላከያ ቢ እና የንፋስ ስልክ ጨዋታ በመከላከያ ቢ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል
በሁለቱም ቡድኖች በኩል በክፍት ሜዳ ጎል
ለማስቆጠር ከማሰብ ይልቅ ጨዋታውን በጥንቃቄ በመጫወት በሚገኙ ዕድሎች ጎል ለማስቆጠር ማሰባቸው ጨዋታውን ቀዝቀዝ አድርጎታል። በ15ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ የንፋስ ስልኩ ግብ ጠባቂ በረከት ሳህሌ ለመቆጣጠር አስቦ የተፋውን ኢብራሒም መሐመድ አግኝቶ ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል። ኢብራሒም በዘንድሮ ዓመት በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ አማካኝነት በዋናው ቡድን የመጫወት ዕድል አግኝቶ እንደነበረ ይታወሳል።
የታላቁ የእግርኳስ ሰው ስዩም አባተ ልጅ በኤዝሮን የሚሰለጥኑት ንፋስ ስልኮች ጠንከር ያሉ አጥቂዎች በቡድኑ ውስጥ አለመኖራቸው እምብዛም የመከላከያን የመከላከል አጥርን አልፈው ጥቃት ለመፈፀም ተቸግረዋል።
ያም ቢሆን ከርቀት በረከት ከማ አክርሮ የመታው እና ግብጠባቂው እንደምንም ያወጣው ተጠቃሽ ነበር። ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት ጠንካራ መከላከልን ያደረጉት መከላከያዎች ውጥናቸው ተሳክቶ ጨዋታውን በመቆጣጠር አስቀድመው በአስቆጠሩት አንድ ጎል አሸንፈው ሊወጡ ችለዋል። ውጤቱን ተከትሎ መከላከያ ቢ ከዋናው ቡድን በመቀጠል ወደ ከፍተኛ ሊጉ አድጓል።