የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ሊያደርግ ነው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዛሬው ዕለት በጁፒተር ሆቴል የተሰባሰበ ሲሆን ነገ የመጀመሪያ ልምምድ ያደርጋል፡፡

የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት ይደረጋል፡፡ በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ሀገራት አስቀድሞ በማጣሪያ ጨዋታዎች በሚያስመዘግቡት ውጤት መሠረት በመድረኩ ላይ ተካፋይ የሚሆኑ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ዳግም በውድድሩ ላይ ለመገኘት የማጣሪያ ጨዋታውን ከያዝነው ወር ጀምሮ ማከናወን ይጀምራል፡፡

ከማላዊ እና ከግብፅ ጋር የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታዎችን የሚከውነው ብሔራዊ ቡድኑ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ አማካኝነት ከቀናት በፊት ለሀያ ስምንት ተጫዋቾች ጥሪ ማድረግ የቻለ ሲሆን አባላቱ በዛሬው ዕለት ቦሌ በሚገኘው ጁፒተር ሆቴል ለዝግጅት ተሰባስበዋል፡፡

ጥሪ የደረሳቸው የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ከሽመልስ በቀለ በቀር ሪፖርት በማድረግ ወደ ሆቴል የገቡ ሲሆን ሲዳማ ቡና በፕሪምየር ሊጉ ባህር ዳርን 3-1 ሲረታ ጎል ከማስቆጠሩ ባሻገር ጉዳት አስተናግዶ ተቀይሮ ለመውጣት የተገደደው አጥቂው ይገዙ ቦጋለም በመልካም ጤንነት ላይ በመገኘቱ ቡድኑን መቀላቀል ችሏል። ከደቂቃዎች በፊት የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ከአሰልጣኝ ቡድን አባላት ጋር ትውውቅ እና መጠነኛ ስብሰባን አድርገዋል፡፡ በተጨማሪም የብሔራዊ ቡድኑ የህክምና ባለሙያ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት የሀዋሳ ከተማው ሂርፓ ፋኖ በፋሲል ከነማው የህክምና ባለሙያ ሽመልስ ደሳለኝ መተካታቸው ተሰምቷል።

ነገ ማለዳ ለብሔራዊ ቡድኑ አጠቃላይ አባላት የጤና ምርመራ ከተደረገ በኋላ የመጀመሪያ ልምምዳቸውን ሲ ኤም ሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ መስራት እንዲጀምሩ ይጠበቃል፡፡

ያጋሩ