የፕሪምየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር የ25ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን መሰረት በማድረግ በተለያዩ ጥፋቶች ዙርያ የቅጣት ውሳኔ ወስኗል።
ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ሊጉ ከመቋረጡ አስቀድሞ 25ኛው ሳምንት ከቀናት በፊት መካሄዱ ይታወሳል። የውድድሩ የበላይ አካል የሊጉ አክሲዮን ማህበር በጨዋታ ታዛቢዎች እና በውድድሩ መሪዎች የቀረበለትን ሪፖርት ከተመለከተ በኋላ ግድፈት ታይቶባቸዋል ባላቸው ጉዳዮች ላይ የተለያዩ የዲሲፕሊን ውሳኔዎች ወስኗል። በዚህም ዳዋ ሆቴሳ እና ጌታነህ ከበደ የሦስት ጨዋታ እገዳ ሲጣልባቸው ባህር ዳር ከተማ እና ፋሲል ከነማ ጠንከር ያለ የገንዘብ ቅጣት ተላልፎባቸዋል።
የአደማ ከተማው አጥቂ ዳዋ ሆቴሳ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋችን አፀያፊ ስድብ በመሳድብ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ስለመሆኑ ሪፖርት የቀረበበት ሲሆን ሦስት ጨዋታ እንዲታገድና ብር 3,000.00 የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ተደርጓል። የወልቂጤው አጥቂ ጌታነህ ከበደ ደግሞ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የውድድር አመራሮችን ስለመዝለፉ ሪፖርት የቀረበበት ሲሆን በፈፀመው ጥፋት መሰረት ሦስት ጨዋታ እና ብር 3,000.00 እንዲቀጣ ተወስኖበታል።
በክለቦች በኩል ባህር ዳር ከተማ በሲዳማ ቡና በተረታበት ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች ጨዋታው ካለቀ በኋላ የክለቡን አመራሮችና ተጫዋቾች በተደጋጋሚ አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት ሲቀርብ ፣ ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ጥፋት አጥፍተው የተቀጡና በዚህም ከድርጊታቸው አለመማራቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ክለቡ ብር 75,000.00 እንዲቀጣ ተወስኖበታል። ሌላው የተቀጣው ክለብ ፋሲል ከነማ ቅዱስ ጊዮርጊስን ባሸነፈበት ጨዋታ ደጋፊዎች በዕረፍት ሰዓት ወቅት ፖለቲካዊ ይዘት ያለው መልዕክት ስለማስተላለፋቸው በተጨማሪም የዕለቱ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ሜዳ ዘለው ስለመግባታቸው ሪፖርት የቀረበባቸው በመሆኑ በዕለቱ ለፈፀሙት ጥፋት ክለቡ ብር 50,000.00 እንዲቀጣ ተወስኗል።
ከዚህ ባሻገር ወንድማገኝ ማርቆስ (ጅማ አባ ጅፋር) ፣ አንተነህ ጉግሳ (ወላይታ ድቻ) ፣ በኃይሉ ግርማ (ሰበታ ከተማ) እና አዲስዓለም ተስፋዬ (ሃዋሳ ከተማ) በተለያዩ ጨዋታዎች አምስተኛ ቢጫ ካርድ በማየታቸው 1 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ ብር 1,500.00 እንዲከፍሉ ሲደረግ ፍሬዘር ካሳ (ሀዲያ ሆሳዕና) ፣ ጊት ጋትኩት (ሲዳማ ቡና) ፣ በረከት ሳሙኤል (ሰበታ ከተማ) እና ሚሊዮን ሰለሞን (አዳማ ከተማ) አስረኛ ቢጫ ካርድ በመመልከታቸው ሁለት ጨዋታ እንዲታገዱና ብር 2,000.00 እንዲከፍሉ ውሳኔ ተላልፏል።