ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

ሦስተኛው ዓበይት ጉዳያችን በሳምንቱ ትኩረት በሳቡ አሰልጣኞች ላይ ያተኩራል።

👉 የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ አነጋጋሪ ሁኔታ

አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ከጫና ጋር በተያያዘ አጋጥሟቸዋል በተባለ የጤና እክል በሜዳ ተገኝተው በጨዋታ ዕለት ቡድናቸው መምራት ካቆሙ ሳምንታት ተቆጥረዋል። ቡድኑ በ20ኛው የጨዋታ ሳምንት ከባህር ዳር ከተማ ጋር ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ ቡድናቸው ከመሩ ወዲህ በህመም ምክንያት ሜዳ ላይ ያልታዩት አሰልጣኙ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች አለመኖራቸውን ተከትሎ ረዳታቸው የሆነው ዮርዳኖስ ዓባይ ቡድኑ ባህር ዳር ላይ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች መርቶ አጠናቋል።

ታድያ ይህን ነገር አስገራሚ የሚያደርገው ለወትሮውም ቢሆን በሜዳው ጠርዝ በጨዋታ ወቅት የማንመለከታቸው አሰልጣኙ በህመም ምክንያት በጨዋታ ላይ አይታደሙ እንጂ የቡድኑን ልምምድ የሚመሩት እሳቸው ስለመሆናቸው ረዳታቸው ከዚህ በፊት ሲናገር መደመጡ ነው። አሰልጣኙ ከቡድኑ ተለይተው ካረፉበት ሆቴል እስከ ፋሲል ከነማው ጨዋታ ድረስ በልልምድ ማዳ ላይ በመገኘት ሲያሰሩ የቆዩ ሲሆን የፋሲሉ ጨዋታ ዕለት በጤና ሁኔታቸው መነሻነት ወደ አዲስ አበባ አቅንተዋል።

አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ እንኳን በሚታይ መልኩ የጉልበት ጉዳት አስተናግደው በተጠባባቂ በወንበር ላይ ሆነው ቡድናቸውን ሲመሩ ብንመለከትም የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ለልምድ ወቅት ብቁ ሆነው በጨዋታ ወቅት የማይገኙበት ምክንያት እንቆቅልሽ ውስጥ ሆኖ ውድድሩ ተቋርጧል። ቡድኑ በባህር ዳር ቆይታው ያደረገው የመጨረሻው የድሬዳዋ ጨዋታ በፊት ግን በልምምድ ላይም አለመኖራቸው ጉዳዩ ይበልጥ ትኩረት እንዲስብ የሚያደርገው ሆኗል።

👉 ይታገሱ እንዳለ የመጀመሪያውን ጨዋታ በድል ተወጥቷል

ከቀናት በፊት ከአሰልጣኛቸው ፋሲል ተካልኝ ጋር የተለያዩት አዳማ ከተማዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በጊዜያው አሰልጣኛቸው ይታገሱ እንዳለ እየተመሩ ያደረጉትን ጨዋታ በድል ተወጥተዋል።

በአዳማ የዕድሜ እርከን ቡድን ከዚህ ቀደም በመስራት ያሳለፈው የቀድሞው የአዳማ ከተማ አማካይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የውበቱ አባተ ፣ አብርሃም መብራቱ እና ፋሲል ተካልኝ ረዳት በመሆን ራሱን ሲያዘጋጅ የነበረ ሲሆን ብዙዎች ከቡድኑ ጋር ካለው የስሜት ትስስር እና በረዳትነት ራሱን እያበቃ እንደመጠበቁ በመጨረሻም ለዓመታት ያጩት የነበረው ኃላፊነት ለመረከብ በቅቷል።

ታድያ በመጀመሪያው ጨዋታም ለ11 ሳምንታት ሳያሸንፍ የቆየውን ቡድንን ወደ ድል ሲመራ በጨዋታውም ቡድኑ በውድድር ዘመኑ ለሁለተኛ ጊዜ ሦስት ግቦችን አስቆጥሮ እንዲያሸንፍ በማድረግ የተሳካ አጀማመርን አድርጓል። በደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ቅቡልነት ያለው አሰልጣኙ በመጪዎቹ ጨዋታዎች የቡድን ስሜቱን በመመለስ አዳማ በሊጉ የተሻለ ቦታ ይዞ እንዲያጠናቅቅ ይረዳዋል በሚል በብዙዎች ዘንድ ተስፋ ተጥሎበታል።

👉 ለራስ ጉድለቶች ትኩረት መስጠት

ብዙ ጊዜ በእግርኳሳችን በተለይ ለሚመዘገቡ አሉታዊ ውጤቶች በአሰልጣኞች ዘንድ ተጠያቂ የሚሆን አካልን የመፈለግ ዝንባሌ በስፋት እንመለከታለን።

ታድያ ልክ እንደ “ትኩስ ድንቹ ምሳሌ” በአብዛኛው የዚህ የራስን መከላከያ መንገድ ሰለባ የሚሆኑት ደግሞ ዳኞች ሲሆኑ እንመለከታለን። በጨዋታ ሳምንቱ ወልቂጤ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረች ግብ ነጥብ የተጋሩት ወልቂጤ ከተማዎች በተለይ ግቧ በተቆጠረችበት ሂደት ብዙ ቅር ሊሰኙባቸው የሚችሉ ምክንያቶች አሉ ብሎ መውሰድ ቢቻልም አሰልጣኙ ግን ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ይህን ከማለት ተቆጥበዋል።

አሰልጣኝ ተመስገን ዳና በዚህ ጉዳይ ላይ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ፤ “ስለዳኝነት ብዙ ማውራት አያስፈልግም። እነርሱ ራሳቸውን ይገምግሙ ፣ እኛ ደግሞ የእኛን ስህተት እንገመግማለን።”የሚል አጭር እና ግሩም መልስ ሰጥተዋል።

በመሆኑም በመሰረታዊነት እነሱ ሊቆጣጠሯቸው እና ሊያስተካክሏቸው በሚችሉ መሰረታዊ የሜዳ ላይ ጉዳዮች ትኩረት መስጠት ግዴታቸው ሲሆን እንደተለመደው በብልጣብልጥነት ውጤቶችን የሆነ አካል ላይ ለማላከክ የሚደረጉ ጥረቶች ለአሰልጣኞች አሁን ላይ ፋሽኑ ያለፈ ይመስላል። በተለይም በሊጉ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ብቅ እያሉ የሚገኙ ወጣት አሰልጣኞች ይህን አስተሳሰብ በመስበር ረገድ ትልቅ ሚና እየተወጡ ይገኛሉ።