ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

መጨረሻው ፅሁፋችን በጨዋታ ሳምንቱ ሌሎች ትኩረት የሳቡ ጉዳዮች ቀርበውበታል።

👉 ፍፁም የተለየው የስታዲየም ድባብ

የውድድር ዘመኑ ትልቁ ጨዋታ ከአስደናቂ የደጋፊዎች ድባብ ጋር ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተጠናቋል።

ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በ2009 የውድድር ዘመን ከመጡ ወዲህ በተለየ የደጋፊ ድባብ የምናውቃቸው ፋሲላውያን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ የባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየምን የተለየ ድባብን አላብሰውት ተመልክተናል።

በጨዋታ ሳምንቱ እጅግ በጉጉት ይጠበቅ በነበረው ጨዋታ የሊጉን መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማን ያገናኘው ጨዋታ በባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም ታሪክ ምናልባት በክለብ እግርኳስ ጨዋታዎች ታሪክ ከተመለከትናቸው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደጋፊዎች ቁጥር ታጅቦ የተደረገ ነበር።

በተለይም ለባህር ዳር ከተማ 175ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መቀመጫቸውን ያደረጉት ፋሲል ከነማዎች በርካታ ደጋፊዎቹ ይህን ጨዋታ ለመታደም ወደ ባህር ዳር ያቀኑ ሲሆን በጥቅሉ ግን በባህር ዳር መቀመጫቸውን ካደረጉ የክለቡ ደጋፊዎች ጋር በመሆን በተለይ በባህር ዳር ስታዲየም አጠራር “በላይ ዘለቀ” በተሰኘው ከክብር እንግዶች መቀመጫ ትይዩ በሚገኘው የተመልካቾች መቀመጫ የነበረው በነጭ እና ቀይ ቀለም የተጥለቀለው የደጋፊዎች ህብረ ቀለም የተለየ መልክ ነበረው።

በጨዋታው በሜዳው ከነበሩት የፋሲል እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ባለፈ በርከት ያሉ የእግር ኳስ ተመልካቾች በስታዲየም ታድመው ተመልክተናል።

በጨዋታው እንደ እሳት የሚፋጅን ደማቅ የሆነ የደጋፊዎችን ድባብ መፍጠር የቻሉት የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በስታዲየም እየጣለ የነበረው ኃይለኛ ዝናብ ሳይበግራቸው ለደቂቃዎች ከፍ ባለ የደስታ ማዕበል ውስጥ ሆነው ተመልክተናል።

ጨዋታው በሰላም እንዲጠናቀቅ በማሰብ ከጨዋታ አንድ ቀን አስቀድሞ ባለ ድርሻ አካላት ከአንድ ሰዓት ለሚልቅ ጊዜ ከሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን በጨዋታው ዕለት ጨዋታው ያለ ምንም እንከን እንዲደረግ በጋራ ትብብር ከጠዋት አንስቶ ሲደረግ የነበረው ጥረት ምስጋና ሊቸረው የሚገባ ነው።

👉 የሊጉ መቋረጥ

25ኛ ሳምንቱ ላይ የደረሰው የሊግ ውድድር ከመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች አስቀድሞ ለአህጉራዊ ውድድሮች ሲባል ሊጉ ለቀጣዩቹ 18 ቀናት የሚቋረጥ ይሆናል።

ምንም እንኳን ቡድኖች የተወሰኑ ተጫዋቾቻቸውን በብሔራዊ ግዳጅ ቢያጡም ተጫዋቾች በተወሰነ መልኩ ኃይላቸውን ሊያድሱበት የሚችሉበትን እረፍት የሚያስገኝ ሲሆን ከዚህ ባለፈ ቡድኖች ለመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ይበልጥ ራሳቸውን በማዘጋጀት የሚቀርቡበትን ዕድል ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ሊጉ ከእረፍት ሲመለስ ወሳኝ አምስት ጨዋታዎች የሚጠብቋቸው ቡድኖች ይህን የዕረፍት ጊዜ ይበልጥ በአውንታዊነት ሊጠቀሙባቸው በሚችሉባቸው መንገዶች ላይ ጠንካራ ስራዎችን ሰርተው እንዲቀርቡ ይጠበቃል።